ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ በስደተኞች ላይ የሚወሰደው እርምጃ "በጣም ጠንካራ" እንደነበር እና በምርጫው ለመሸነፋቸው የራሱ ድርሻ እንደነበረው አመኑ
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሕገ ወጥ ስደተኞች ላይ የተወሰደው ጥብቅ እርምጃ "ከመጠን በላይ ጠንካራ" እንደነበር ገልፁ።
ይህም ፕሬዚዳንቱ ከአጋማሽ ዘመን ምርጫ በኋላ ከዋና ዋና የፖለቲካ አጀንዳዎቻቸው በአንዱ ላይ ያሳዩት በጣም ግልጽ የአቋም ለውጥ ተደርጎ ተወስዷል።
ትራምፕ ለሲቢኤስ የ"60 Minutes" ፕሮግራም በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ ሕገ-ወጥ የድንበር ማቋረጦችን በእጅጉ በመቀነሳቸው "ኤ+" ሊሰጣቸው እንደሚገባ እንደሚያምኑ ገልጸዋል።
ሆኖም በስፋት በተካሄዱ የስደተኞች ማባረር ዘመቻዎች ምክንያት በፖለቲካ ዋጋ እንደከፈሉ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ ይህንን ያመኑት የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደህንነት መሥሪያ ቤት ሕገወጥ ስደተኞችን ከማባረር ወደ ኋላ እንደማይል አጽንኦት በሰጠበት ወቅት ነው።
በምርጫ ቀን የተሰበሰቡ የሕዝብ አስተያየቶች እንዳመለከቱት፣ ከኢኮኖሚ እና ከዴሞክራሲ ቀጥሎ የስደተኞች ጉዳይ ለመራጮች ሦስተኛው ከፍተኛ አሳሳቢ ጉዳይ ነበር።
በታሪክ ጠንካራ የወግ አጥባቂው ፓርቲ ደጋፊዎች በሚገኙበት ቴክሳስ የላቲን ዝርያ ያላቸው መራጮች ድምጻቸውን ለዴሞክራቶች በመስጠታቸው ፓርቲው በኮንግረስ አብላጫውን መቀመጫ እንዲያሸንፍ አድርጎታል።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሲቢኤስ የ"60 Minutes" ፕሮግራም እንደተናገሩት፣ የስደት ፖሊሲያቸው ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ በተደረገው የአጋማሽ ጊዜ ምርጫ ለሪፐብሊካኖች "ጠቅሟልም፣ ጎድቷልም"።
"ድንበሩን በመቆጣጠር ረገድ ኤ+ ይገባኛል ብዬ አስባለሁ" ሲሉ በእሁድ ምሽት በተላለፈው ፕሮግራም ላይ ተናግረዋል።
"አደገኛ የሆኑትን ሰዎች በማስወጣት ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቤያለሁ" ሲሉም አክለዋል።
ነገር ግን "ጥሩ ሥራ የነበራቸውን እና አንድ ብቻ የሕግ ጥሰት የፈጸሙ ሰዎችንም አስወጥተናል፤ ያ ጥሰታቸውም አገር ውስጥ በሕገ-ወጥ መንገድ መግባታቸው ብቻ ነበር። በዚህ ምክንያት የፖለቲካ ዋጋ ከፍያለሁ" ብለዋል።
"ከመጠን በላይ ጥብቅ ነበር" ሲሉ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስለ አስተዳደራቸው የስደተኞች ፖሊሲ ተናግረዋል።
ትራምፕ በተጨማሪም ከዴሞክራቶች ጋር በስደተኞች ጉዳይ ላይ ለመስራት "በጣም እፈልጋለሁ" ብለው ቢናገሩም ዕቅዳቸውን በዝርዝር አላቀረቡም።
ከአንድ ዓመት በፊት ለ"60 Minutes" በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ ትራምፕ የአስተዳደራቸው የስደተኞች ዘመቻ "በቂ ርቀት አልሄደም" ሲሉ ተከራክረው ነበር።
ፕሬዚዳንቱ እሁድ ዕለት ያሳዩት የተለሳለሰ አቋም ግን፣ ዋይት ሐውስ በዚያው ቀን ለቢቢሲ ከሰጠው መግለጫ በእጅጉ የተለየ ነው።
የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ በሰጡት መግለጫ፣ "አስተዳደሩ ማኅበረሰቦቻችንን የሚያሸብሩ ወንጀለኛ ሕገ ወጥ ስደተኞችን በመያዝና ከአገር በማስወጣት የሚደረገውን ጥረት አይቀንስም" ሲሉ ተናግረዋል።
የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደህንነት መሥሪያ ቤትም እሁድ ዕለት ከዚህ አቋሙ ወደ ኋላ እንደማይል ተናግሯል።
"አይስ ወደ ኋላ አይመለስም፣ ፍጥነቱንም አይቀንስም" ሲሉ የአገር ውስጥ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከማክሰኞው የምርጫ ሽንፈት በኋላ፣ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ የስደተኞች ፖሊሲን ለማስተካከል ዝግጁ መሆናቸውን የሚጠቁም አቋም አሳይተዋል።
ቫንስ በአንድ ረዥም የማኅበራዊ ሚዲያ ጽሑፋቸው ላይ "ሕገ ወጥ ሠራተኞችን የሚቀጥሩ የንግድ ተቋማት ላይ በበለጠ ማተኮርን ጨምሮ የአፈጻጸም ስልታችንን መቀየር አለብን የሚለውን ሀሳብ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ" ብለዋል።
ሆኖም፣ ትራምፕ በአርብ ዕለት ጠንካራ የስደተኞች ፖሊሲ ደጋፊ የሆኑትን ስቲፈን ሚለርን የዋይት ሐውስ ዋና የሥራ አስፈጻሚ አድርገው መሾማቸው፣ አስተዳደሩ ከእስካሁኑ የስደተኞች አቋም ወደ ኋላ እንደማይመለስ የሚያሳይ ምልክት ተደርጎ ተወስዷል።
ስቲፈን ሚለር በትራምፕ የመጀመሪያና ሁለተኛ የፕሬዚዳንትነት ዘመን የተተገበረውን ጥብቅ የስደተኞች ፖሊሲ ዋና አጋፋሪ ተደርገው በስፋት ይታያሉ።
ከኢሚግሬሽንና ጉምሩክ ማስፈጸሚያ ተቋም (አይስ) የወጡ ምንጮች ለሲቢኤስ እንደተናገሩት፣ ባለፉት ሳምንታት የተቋሙ ኃላፊዎች በቀን 2,700 ያህል ሕገ-ወጥ ስደተኞችን በቁጥጥር ሥር ማዋል ላይ እንዲያተኩሩ መመሪያ ተሰጥቷቸዋል። ይህም ቀደም ሲል ከተቀመጠው በቀን 2,000 ስደተኞችን የማሰር ዒላማ ከፍ ያለ ነው።
በዚህ ዓመት የተካሄዱት የማስፈጸሚያ ዘመቻዎች በቺካጎ፣ በሚኒያፖሊስ እና በሎስ አንጀለስን ጨምሮ በበርካታ ከተሞች የፀረ-አይስ ሠልፎችን ተካሄደዋል።
በሚኒያፖሊስ፣ ሬኔ ጉድ እና አሌክስ ፕሬቲ የተባሉ ሁለት አሜሪካውያን ተቃዋሚዎች በኢሚግሬሽን ፖሊሶች በተተኮሱ ጥይቶች መገደላቸው ተዘግቧል።