ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቡልዲግሉ ወረዳ በታጣቂዎች ጥቃት ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ፖሊስ ገለፀ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን ቡልዲግሉ ወረዳ በምትገኘው ዳለቲ ቀበሌ ውስጥ ታጣቂዎች በፈፀሙት ጥቃት 52 ሰዎች መገደላቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ለቢቢሲ ገለፀ።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ እድሪስ መሐመድ ለቢቢሲ በሰጡት አጭር ማብራሪያ፣ በስፍራው ጥቀቱ የተከፈተው ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ጥቅምት 26/2019 ዓ. ም. ንጋት 11 ሰዓት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ጥቃቱን የፈፀሙት "የሸኔ ታጣቂዎች ናቸው" ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ሲቪሎች እና የክልሉ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ሰለባ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚህ ጥቃት ባጠቃላይ ተገደሉ ካሏቸው 52 ሰዎች መካከል 21 ሰዎች ሲቪሎች ሲሆኑ፣ 18 የሚሆኑት የክልሉ አድማ ብተና አባላት፣ የተቀሩት 13 ሰዎች ደግሞ የአካባቢው ሚሊሻ አባላት መሆናቸውን በዝርዝር ገልፀዋል።
ጥቃቱ የተፈፀመባት ዳለቲ ቀበሌ ከኦሮሚያ ክልል ጋር እንደምትዋሰን እና በአካባቢው "ሸኔ" ሲሉ የጠቀሷቸው ታጣቂዎች እንደሚንቀሳቀሱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ እድሪስ መሐመድ አስረድዋል።
ታጣቂዎቹ ጥቃቱን የፈፀሙት "ድንገት ገብተው በመሆኑ ብዙ ጉዳት ሊደርስ ችሏል" ብለዋል።
ከጥቃቱ በኋላ የመከላከያ ሠራዊት እና ተጨማሪ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች በአካባቢው መሰማራታቸውን የገለፁት ኮሚሽነሩ፣ በመሆኑም መረጋጋት መስፈኑን ተናግረዋል። ታጣቂዎቹ ጥቃቱን ከፈፀሙ በኋላ "ወዲያው ተሰውረዋል" ሲሉም አክለዋል።
አቶ እድሪስ "ሸኔ" ያሉት እና በኢትዮጵያ መንግሥት በሽብርተኝነት የተፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ስለተፈፀመው ጥቃት እስካሁን ያለው ነገር የለም።
ቢቢሲ የታጣቂ ቡድኑ ቃል አቀባይ ምላሽ እንዲሰጡ ጠይቋል። የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እስካሁን ድረስ የቀረበበትን ክስ በተመለከተ ይፋዊ ምላሽ አልሰጠም።
በሌላ በኩል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ባወጣው መግለጫ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዳለቲ ቀበሌ የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ፣ በዚያው ቀን በተመሳሳይ ስፍራ "43 ሲቪሎች" በመንግሥት ኃይሎች ተገድለዋል ሲል አመልክቷል።
የኦነግ ቃል አቀባይ ለሚ ገመቹ በፌስቡክ ገጻቸው ያጋሩት የድርጅታቸው መግለጫ፣ ጥቅምት 26 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዳላቲ በተባለ ቦታ፣ "ሸኔን ትደግፋላችሁ" በሚል ክስ "የክልሉ ፖሊስ ሴቶችን እና ሕፃናትን ጨምሮ ከ43 በላይ የሆኑ የኦሮሞ ሲቪሎችን በጅምላ ገድሏል" ሲል ከሷል።
ቢቢሲ በሥፍራው ስለተፈፀመው ጥቃት እና ስለደረሰው ጉዳት ከገለልተኛ አካል ማጣራት አልቻለም።
የአካባቢውን ነዋሪዎች እና እማኞች ለማነጋገር ያደረግናቸው ጥረቶች እስካሁን አልተሳኩልንም።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ማብራሪያ የሰጡበት እና ኦነግ መግለጫ ያወጣበት ጥቃት ተመሳሳይ አልያም ትስስር ያላቸው ስለመሆኑም ቢቢሲ በገለልተኛ ወገን አላጣራም።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ እድሪስ መሐመድ፣ በዳለቲ በተፈፀመው የታጣቂዎች ጥቃት ጉዳት ደርሶባቸው በሕክምና ላይ የሚገኙ ሰዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።
ከጥቃቱ በኋላ "ሕዝቡን አወያይተን የተበተነውን ማኅበረሰብ ወደቦታው መልሰናል" ሲሉም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተደጋጋሚ በታጣቂዎች ጥቃት ከሚፈፀምባቸው ክልሎች አንዱ ነው። በክልሉ የሐሙሱ ጥቃት የተፈፀመው በኦሮሚያ ክልል አርሲ በሚገኘው ሮቤ ወረዳ የ"38" ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ጥቃት በተፈፀመበት ተመሳሳይ ቀን እና ሰዓት ነው።