ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከአሜሪካ ቤተ መጻሕፍት እየጠፉ ያሉ እና ሳንሱር የሚደረግባቸው መጻሕፍት
ከአምስት ዓመታት በፊት፣ በዩናይትድ ስቴትስ ፍሎሪዳ፣ ፒኔላስ ካውንቲ የምትኖር ኒኮል የምትባል እናት የተወሰኑ መጻሕፍት ከልጆቿ ትምህርት ቤቶች እየተወገዱ መሆኑን አስተዋለች።
ልጆቿ ራሳቸው አንዳንድ መጻሕፍት እንደማይገኙ አስተዋሉ፣ እናም ከመምህራን እና ከቤተ መጻሕፍት ባለሙያዎች ጋር በመነጋገር ይህንን እውነታ አረጋገጠች።
ስለዚህ ኒኮል አራት ልጆቿን በትምህርት ቤት ማግኘት የማይችሏቸውን መጻሕፍት ለመግዛት ወሰነች። ይህ ግን ለሁሉም ቤተሰብ አማራጭ አለመሆኑን ታውቃለች።
"እኔ በምኖርበት ስፍራ ለመጻሕፍት መግዣ የሚሆን ተጨማሪ ገቢ የሌላቸው ቤተሰቦች አሉ" ትላለች።
"ወላጆች፣ የልጅ ልጃቸውን የሚንከባከቡ አያቶች በሥራ ባህሪያቸው ምክንያት ወደ ቤተ መጻሕፍት ሊወስዷቸው አይችሉም" ስትል አክላለች።
በአሜሪካ የሚገኙ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ወላጆችን፣ መምህራንን፣ የቤተ መጻሕፍት ባለሙያዎችን፣ አክቲቪስቶችን እና ፖለቲከኞችን ያካተተ ከፍተኛ የርዕዮተ ዓለም ክርክር የሚካሄድባቸው የጦርነት መድረክ ሆነዋል።
የአሜሪካ ቤተ መጻሕፍት ማኅበር በ2025 ብቻ፣ በሕዝብ እና በትምህርት ቤት ቤተ መጻሕፍት ውስጥ 6,588 መጻሕፍት ቅድመ ምርመራ (ሳንሱር) እንደተደረገባቸው አስታውቋል። በዚህም የተነሳ መጻሕፍቱ ከመደርደሪያዎች ሙሉ በሙሉ እንዲወርዱ ወይም ልዩ ክትትል ወደ ሚደረግባቸው ክፍሎች እንዲዛወሩ አድርጓል።
በዚህ ውሳኔ ምክንያት 4,235 መጻሕፍት ሰለባ ሆነዋል።
ይህ ከአውሮፓውያኑ 2001 እስከ 2020 ባሉት ጊዜያት ውስጥ በየዓመቱ በአማካይ 70 መጻሕፍት ቅድመ ምርመራ እንደሚደረግባቸው በተነጻጻሪነት የቀረበ ነው።
ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ድርጅቶች ትክክለኛው ቁጥር በጣም ከፍ ሊል እንደሚችል ያምናሉ። ምክንያቱም አብዛኞቹ መጽሐፍት ከመደርደሪያዎች ላይ እንዲወርዱ የሚደረጉት በዝምታ ነው።
ሀሳብን የመግለጽ ነፃነትን ለማስጠበቅ እና የመጽሐፍ ቅድመ ምርመራን ለመቆጣጠር የተቋቋመው ፔን አሜሪካ የቅርብ ጊዜ ሪፖርት "ከዚህ በፊት ብዙ ልጆች መጻሕፍትን እንዳያገኙ ተደርገው አያውቁም" ይላል።
ይህ እርምጃ በርካታ ግዛቶች ሕጎችን ካወጡበት እና በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተገቢ ያልሆኑ ያሏቸውን መጻሕፍት ተደራሽነት ለመገደብ ያለሙ እርምጃዎችን ካጸደቁበት ጊዜ ጋር ተገጣጥሟል።
"ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ እያየነው የመጣነው በጣም የተለየ ዓይነት እርምጃ ነው" ሲሉ የብሔራዊ ፀረ ሳንሱር ጥምረት አባል የሆኑት ጂያንማርኮ አንቶስካ ያስረዳሉ።
"ከትምህርት ቤቶች ውጭ ወጥቷል፤ ብዙ ግዛቶችን እና በፌዴራል ደረጃም ቢሆን መጻሕፍትን የሚከለክሉ ሕጎችን አይተናል።"
እገዳዎቹን የሚደግፉ ድርጅቶች እና እነዚህን ገደቦች የሚያመቻቹ ባለሥልጣናት ግን ብቸኛ ግባቸው ልጆች ከዕድሜያቸው ጋር የማይጣጣሙ ቁሳቁሶችን እንዳያገኙ መከላከል ነው ይላሉ።
እነዚህ ገደቦች ወላጆች የልጆቻቸውን ትምህርት በተመለከተ ውሳኔ የማድረግ መብታቸውን ለማስከበር የተነደፉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
"ማምስ ፎር ሊበርቲ" የተሰኘው ድርጅት የመጻሕፍትን ይዘት በመቃወም ረገድ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ካላቸው ቡድኖች አንዱ ነው። ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ወቅት ቢያስተባብሉም የድርጅቱ ሥራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር ቲና ዴስኮቪች በሰጡት መግለጫ ግን "ልጆችን በትምህርት ቤት በሚገኙ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ካሉ ከዕድሜ ጋር የማይጣጣሙ ግልጽ ከሆኑ ወሲባዊ ይዘቶች እና ርዕዮተ ዓለማዊ ይዘቶች ለመጠበቅ እንታገላለን" ብለዋል።
ግን የትኞቹ መጻሕፍት ለትምህርት ቤት ቤተ መጻሕፍት ተስማሚ እንደሆኑ መወሰን ያለበት ማን ነው? ውሳኔው የሚተላለፈውስ እንዴት ነው?
መጽሐፍት እንዴት ነው የሚታገዱት
በአሜሪካ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች መጽሐፍት በተመሳሳይ መንገድ ወይንም ሂደት አይታገዱም።
ለምሳሌ በፍሎሪዳ እና ቴክሳስ ግዛቶች ከ2024 እስከ 2025 ባለው ጊዜ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ መጽሐፍትን አግደዋል።
የፔን አሜሪካ አሃዞች እንደሚያሳዩት እንደ ኦክላሆማ እና ኒው ሜክሲኮ ያሉ ግዛቶች ግን ምንም መጽሐፍ ስለማገዳቸው ይፋ አላደረጉም።
አንድን መጽሐፍ ከሕዝብ ትምህርት ቤት የማስወገድ ሂደቱ ብዙውን ጊዜ የሚጀምረው ወላጅ ወይም ሌላ የማኅበረሰብ አባል ተገቢ እንዳልሆነ ሲሰማው እና ለአካባቢው የትምህርት ባለሥልጣን ቅሬታ ሲያቀርብ ነው።
በአውሮፓውያኑ 2024 አጋማሽ ላይ ሁለት በፍሎሪዳ የምትገኘው ታምፓ ከተማ ባለሥልጣናት የሂልስቦሮው ሱፐርኢንቴንደንት "ልቅ ወሲብን ያሳያሉ" ብለው የሚቆጥሯቸውን መጽሐፍት ከአካባቢው ትምህርት ቤቶች እንዲያስወግዱ ጫና የሚያሳድሩ ደብዳቤዎችን ጽፈዋል።
ከመደርደሪያዎች ከተወገዱት 59 መጻሕፍት መካከል 'ኮል ሚ ባይ ዩር ኔም'፣ 'ሆም ጎይንግ' እና 'ኤ ክላሽ ኦፍ ኪንግስ' ይገኙበታል።
የፔን አሜሪካ የፍሎሪዳ ቢሮ ዳይሬክተር የሆኑት ዊሊያም ጆንሰን እንደገለጹት፣ የጉዳዩ መዘዝ ከሂልስቦሮ ካውንቲ አልፎ ሄዷል።
የባለሥልጣናቱን ደብዳቤዎችና ጥያቄ ተከትሎ፣ "ፔን አሜሪካ ቢያንስ ዘጠኝ የፍሎሪዳ አውራጃዎች የትምህርት ዓመቱ ከመጀመሩ በፊት በመቶዎች የሚቆጠሩ መጻሕፍትን ከመማሪያ ክፍሎች እና ከቤተ-መጻሕፍት እንዳስወገዱ ዘግቧል።"
ስለወላጆች መብት የሚነሳው ክርክር
ወግ አጥባቂ ድርጅቶች ወላጆች የልጆቻቸውን ትምህርት በተመለከተ እንዲወስኑ፣ መጽሐፍት መወገዳቸውን እንዲደግፉ የተቀናጀ እርምጃ ወስደዋል።
በንቅናቄው ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ካለው 'ሲትዝንስ ፎር ፍሪደም' ከተባለው ቡድን የተገኘ አንድ ሰነድ እንደሚያሳየው ወላጆች "ልጆቻቸውን ለማሳደግ፣ ለማስተማር እና በሥነ ምግባር ለማነጽ" ሥልጣኑን "እግዚአብሔር የሰጣቸው" መሆኑን በመግለጽ በዚህ ረገድ መንግሥት ወይም ትምህርት ቤቶች እንደማይመለከታቸው ይሞግታል።
ነገር ግን መጽሐፍትን ከትምህርት ቤት እና ከቤተ መጽሐፍት መደርደሪያዎች ለማስወገድ ከሚደረገው ጥረት ጀርባ ወላጆች አሉ ወይ? የሚለው ክርክር እንደቀጠለ ነው
እንደ አሜሪካ ቤተ መጻሕፍት ማኅበር የአእምሯዊ ነጻነት ቢሮ መረጃ፣ በ2025 ከቀረቡት የመጻሕፍት ይታገድልን ጥያቄዎች መካከል 92 በመቶ የሚሆኑት የተጀመሩት በተሟጋች ቡድኖች እና በመንግሥት ባለሥልጣናት አማካኝነት ነው።
የሁለት ልጆች እናት የሆነችው እና የፍሎሪዳ 'ፍሪደም ቱ ሪድ' ፕሮጀክት ዳይሬክተር ስቴፋና ፌሬል "ይህ ጥረት ከመንግሥት ትምህርት ቤት ወላጆች የመጣ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ እስካሁን አልተገኘም" ትላለች።
"ከጅምሩ አንስቶ ንቅናቄው የሚመራው ከሕዝብ ትምህርት ቤቶቻችን ጋር ብዙም ግንኙነት በሌላቸው ልዩ ፍላጎት ባላቸው ቡድኖች ነው" ስትል አክላ ተናግራለች።
መጻሕፍትን ማገድ ምን ያህል ኪሳራ ያስከትላል?
በፒኔላስ ካውንቲ የምትኖረው እና የአራት ልጆች እናት የሆነችው ኒኮል ለቢቢሲ በትምህርት ቤቶች ውስጥ መጻሕፍትን መከልከልን የምትቃወመው በወላጆች መብት ላይ ባላት እምነት የተነሳ መሆኑን ተናግራለች።
"መጽሐፍን በማገድ፣ ለሌሎች ልጆች የሚበጀውን እንጂ ለልጅህ የሚጠቅመውን እየተናገርክ አይደለም።"
ኒኮል እንደ አንባቢም ሆነ እንደ እናት በትምህርት ቤቶች ውስጥ መጽሐፍት ሲታገዱ "የአንድን ሰው መነጽር እየነጠቅን ነው፣ የአንድን ሰው መስኮት እየነቀልን ነው፣ አንድ ሰው ስለሚኖርበት ዓለም በጥልቀት የማሰብ ችሎታውን እያሳጣን ነው" ትላለች።
በአውሮፓውያኑ 2023 የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በሕዝብ ትምህርት ቤቶች ውስጥ እየጨመረ የመጣውን የመጽሐፍ እገዳ አዝማሚያ ለመመርመር እና የአካባቢ አስተዳደሮች አወዛጋቢ የሆኑ መጻሕፍትን እንዳይከለክሉ የሚያደርግ እርምጃ ወስዷል።
ነገር ግን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን እንደተመለሱ በትምህርት ሚኒስቴር የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ውድቅ በማድረግ ክስተቱን እንደ ማጭበርበር ጠቅሰው፣ የተወገዱት መጻሕፍት "ለዕድሜ ተገቢ ያልሆኑ፣ ግልጽ የሆኑ ወሲባዊ ድርጊቶችን የሚገልጹ ወይም ጸያፍ ድርጊቶችን የሚያበረታቱ" ናቸው ብሏል።
በሪፐብሊካን ሕግ አውጪዎች የቀረበ አንድ ረቂቅ ሕግ "ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ ሕጻናት ወሲባዊ ይዘቶች ያላቸው መጻሕፍትን ወይም ሌሎች ቁሳቁሶችን የሚያቀርቡ ወይም የሚያስተዋውቁ" ትምህርት ቤቶች የገንዘብ ድጋፍ እንዳያገኙ ያደርጋል።
የፍሎሪዳ ፍሪደም ቱ ሪድ ፕሮጀክት አባል ለሆነችው ስቴፋና ፌሬል፣ በአሜሪካ ውስጥ የመጻሕፍት እገዳ መጨመር ያስከተለው ትልቁ መዘዝ "ቤተ መጻሕፍትን፣ ሥነ ጽሑፍን እና የማንበብ ነፃነትን ከእንግዲህ መከላከል አይገባም የሚለውን በዝምታ መቀበል ነው" ትላለች።
አክላም "እነዚያን ነፃነቶች የመጠበቅ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች ከእነሱ ፊታቸውን ማዞር ሲመርጡ፣ ኪሳራው ከመጽሐፎቹ በላይ ይዘልቃል።"