የአውሮፓ አየር መንገዶች በአንድ ሳምንት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ የቦምብ ጥቃት ዛቻ ደረሳቸው

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአውሮፓ አየር መንገዶች ትናንት አርብ በድጋሚ የቦምብ ጥቃት ዛቻ ደረሳቸው። ይህም በአንድ ሳምንት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ የደረሰ ዛቻ ነው።

የሊዝበን፣ ሮም፣ ፕራግ እና ሶፊያ በረራዎች ላይ የቦምብ ጥቃት ዛቻ መሰንዘሩን ተከትሎ ሦስት የሀንጋሪ አውሮፕላኖች በፀጥታ ኃይሎች ታጅበዋል።

ከአየር መንገዶቹ በተጨማሪ የአየርላንድ ብሔራዊ ጣቢያ አርቲኢ ላይም የቦምብ ጥቃት ዛቻ በመድረሱ ሠራተኞቹ ሕንጻውን ለቅቀው ወጥተዋል። በሁለቱ ዛቻዎች መካከል ትስስር ስለመኖሩ ግልጽ አይደለም።

ባለፈው ሳምንት መባቻ ወደ 30 የሚጠጉ በአውሮፓ አገራት የሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎች እና አውሮፕላኖች ላይ ዛቻ መሰንዘሩ ይታወሳል።

ዩናይትድ ኪንግደም "ሐሰተኛ ማስፈራሪያ" ስትል ገልጻዋለች።

ትናንት ከሊዝበን ወደ ሮም ሊጓዝ የነበረ አውሮፕላን ዛቻ እንደተሰነዘረበት ራየንኤር አየር መንገድ ገልጿል።

ኤኤፍፒ እንደዘገበው ቢያንስ 11 የሚሆኑ የቼክ ሪፐብሊክ እና ቡልጋሪያ በረራዎች ላይ ዛቻ ደርሷል።

ፈረንሳይ ቢያንስ አራት አውሮፕላኖች ላይ ዛቻ ቢደረግም ሁሉም በሰላም ማረፋቸውን አስታውቃለች።

ትናንት በየትኛውም አውሮፕላን ላይ ቦምብ አልተገኘም።

የአየርላንድ ገለልተኛ ጋዜጣ አርቲኢ እንዲሁም ኒውስቶክኤፍኤም እና ቱደይኤፍኤም የተባሉ የራድዮ ጣቢያ ሠራተኞች ሕንጻቸውን ለቅቀው ወጥተዋል።

የዩኬው ስካይ ሚዲያም ተመሳሳይ የቦምብ ጥቃት ዛቻ ደርሶታል።

የአየርላንድ ፖሊስ በመገናኛ ብዙኃኑ ላይ ስለተሰነዘረው ዛቻ መረጃ እንደደረሰው ገልጿል።

በአየር መንገዶቹ እና በመገናኛ ብዙኃኑ ላይ የደረሱ ዛቻዎች መካከል ትስስር መኖሩ ግልጽ ባይሆንም "የተቀናጀ የማወክ ዘመቻ ሊሆን ይችላል" ብሏል።

"እንዲህ ያሉ ሐሰተኛ ዛቻዎች ፍርሃት፣ ጭንቀት እና በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ መስተጓጎል ይፈጥራሉ። ዛቻውን የሚያደርሰው ማን እንደሆነ እስካሁን አልታወቀም። ግለሰቦች አልያም የተቀናጁ አካላት መሆናቸው አልተለየም" ሲል ፖሊስ መገልጫ አውጥቷል።

የአየርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚኬል ማርቲን ክስተቱን "አሳሳቢ" ብለውታል። መንግሥታቸው ቅድሚያ የሚሰጠው ለዜጎች ደኅንነት መሆኑንም ተናግረዋል።

"ትናንት የአየር ጉዞን ለማወክ የተቀናጀ ጥረት ነበር" ብለዋል።

በሚቀጥለው ሳምንት በአየርላንድ ደብሊን የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ ውይይቶች ይካሄዳሉ።

የዩኬው ሚዲያ ስካይ "የደኅንነት ፍተሻ" እንዳደረገ እና ጉዳዩን ለሚመለከታቸው አካላት እንዳሳወቀ ገልጿል።

"ቅድሚያ የምንሰጠው ለሠራተኞቻችን ደኅንነት ነው። ሥራችንም በሰላም እንዲቀጥል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እየተነጋገርን ነው" ሲልም መግለጫ አውጥቷል።

በሳምንቱ መባቻ ላይ ለደረሰው የቦምብ ጥቃት ዛቻ ተጠያቂ የተደረገው የሩሲያው አክራሪ ቡድን 'ሜል ስቴት' ነበር።

ቡድኑ የጣልያን አየር መንገዶች ላይ ዛቻ በመሰንዘር ቢከሰስም አስተባብሏል።

የቡድኑ መሥራች ቫዲስላቭ ፖዚንያኮቭ ከቢቢሲ የሩሲያ ቋንቋ አገልግሎት በቴሌግራም ለቀረበለት ጥያቄ በስላቅ በሰጠው ምላሽ ቡድኑ ዛቻ አለማድረሱን ገልጿል።

"የምን 'ሜል ስቴት' ነው? የት ነው ያያችሁት? ቡድኑ ለዓመታት እንቅስቃሴ ማድረግ አቁሟል" ብሏል።

"ነገ የጥቃት ዛቻው ላይ የፑቲንን ስም ብታዩ ይሄንን ቀሽም ጥያቄያችሁን ለፕሬዝዳንቱ ታቀርባላችሁ?" ሲልም አክሏል።