ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአርሲ ሮቤ ወረዳ በታጣቂዎች በተፈፀመ ጥቃት 38 ሰዎች መገደላቸውን የተጎጂ ቤተሰቦች እና ነዋሪዎች ተናገሩ
በኦሮሚያ ክልል ሮቤ ወረዳ ውስጥ በምትገኝ እንደቶ የተባለች መለስተኛ ከተማ ውስጥ ታጣቂዎች በፈፀሙት ጥቃት የ38 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገለፁ።
በጥቃቱ ከተገደሉት መካከል 10 ሰዎች ሲቪሎች ሲሆኑ የተቀሩት የእንደቶ ከተማ ሚሊሻዎች እና የፖሊስ አባላት መሆናቸውን ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ እማኞች ተናግረዋል።
ከጥቃቱ ሰለባዎች መካከል 37 ያህሉ ትናንት ሐሙስ ጥቅምት 26/2019 ዓ.ም. ከንጋት 11 ሰዓት አካባቢ ጀምሮ እስከ ረፋድ 5፡30 ድረስ በቀጠለው ጥቃት የተገደሉ ሲሆኑ የተቀረው አንድ ግለሰብ ትናንት ጉዳት ደርሶበት ዛሬ ወደ ሕክምና ማዕከል እየተወሰደ ሳለ ሕይወቱ ያለፈ ነው።
የኦሮሚያ መንግሥት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ ማምሻውን ለቢቢሲ ኦሮምኛ በሰጡት ምላሽ የትናንቱን የሮቤ ወረዳ ጥቃት የፈጸሙት "ሸኔዎች ናቸው" ሲሉ በክልሉ የሚንቀሳቀሰውን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ተጠያቂ አድርገዋል።
"መንግሥትን መጋፈጥ ስላልቻሉ የሽብር ሥራ እየሠሩ ነው። መንግሥት አስፈላጊውን እርምጃ እየወሰደ ይገኛል" ሲሉም ተናግረዋል። "በአርሲም ሆነ በወለጋ ከሰሞኑ የተፈፀሙ ጥቃቶች ሃይማኖትን ከሃይማኖት፣ ብሔርን ከብሔር ለመጋጨት ተልዕኮ የያዙ ኃይሎች የፈፀሙት ነው" ያሉት ኃይሉ፣ መንግሥት "እርምጃ እየወሰደ" መሆኑን አክለዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ በጥቃቱ 34 ሰዎች ስለመገደላቸው ከአካባቢው ነዋሪዎች ማረጋገጡን ክስተቱን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
ጥቃቱ የተፈፀመበት አካባቢ በአዲሱ አደረጃጀት በደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ ዞን ሥር በተካተተው የቀድሞው አርሲ ዞን ውስጥ የሚገኝ ነው።
በቅርቡ በርካታ ሲቪሎች የተገደሉበት የሽርካ ወረዳም በዚሁ ዞን ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ አካባቢው ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የብዙ ሲቪሎች እና የፀጥታ አካላት ሕይወት ያለፈባቸውን ተደጋጋሚ ጥቃቶች አስተናግዷል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል ሽርካ ወረዳ ጥቅምት 14/2019 ዓ.ም. በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና ኢመደበኛ ታጣቂዎች በተፈጸሙ የተለያዩ ጥቃቶች 48 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።
ኮሚሽኑ፣ መንግሥት በአካባቢው ስለተፈጸመው ጥቃት "ፈጣን ገለልተኛ እና ውጤታማ ምርመራ" እንዲያደርግም ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በበኩሏ በሽርካ ወረዳ በጥቃቱ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ብዛት 46 እንደሆነ አስታውቃለች።
አጎራባች በሆነው መርቲ ወረዳ በደረሰ ጥቃት 14 ሰዎች መገደላቸውን የገለጸችው ቤተ ክርስቲያኗ፣ በአንድ ሳምንት ውስጥ በድምሩ 60 ምዕመኖቿ መገደላቸውን ገልጻለች።
የኦሮሚያ ክልል በተመሳሳይ የሽርካውን ጥቃት አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ለነዋሪዎች ግድያ ተጠያቂ ያደረገው "ሸኔ" ሲል የገለጸውን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ነው። በተጨማሪም በአካባቢው "የፋኖ" አባላት እንደሚንቀሳቀሱ የክልሉ ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ ተናግረዋል።
ከዚህ ጥቃት ጋር በተያያዘ 73 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የገለጹት አቶ ኃይሉ፣ የተያዙት ተጠርጣሪዎች "የፋኖ እና የሸኔ" አባላት መሆናቸውንም ገልጸዋል።
መስከረም 26/2019 ዓ.ም. ሐሙስ ዕለት ስለተፈጸመው ጥቃት ዛሬ ዓርብ ረፋድ 5፡30 አካባቢ ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ የዓይን እማኝ፣ ትናንት ከተገደሉት ውስጥ 34ቱን ሰዎች በጅምላ ለመቅበር ከሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ቤተክርስቲያን በዝግጅት ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል ።
"ቀብር ልንፈፅም የጉድጓድ ቁፋሮ እየተጠናቀቀ ነው። አሁን የፍትሓት ፀሎት እየተደረገ ነው ያለው" ብለዋል።
በቤተክርስቲያን ለቀብር የተዘጋጁትን 34 ሰዎች አስክሬን በአካል ተገኝተው ቆጥረው ማረጋገጣቸውን የተናገሩት እማኙ፣ የተገደሉት ሰዎች ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት እስከ 80 ባለው ውስጥ እንደሆነ አክለዋል።
ከሟቾቹ መካከል አንዷ የ70 ዓመት አዛውንት ሴት ሲሆኑ፣ የተቀሩት ሁሉም ወንዶች መሆናቸውን ጨምረው አስረድተዋል።
ጥቃቱን የፈፀሙት ታጣቂዎች ከሌሎች አጎራባች ወረዳዎች የመጡ መሆናቸውን የተናገሩት እኚህ ግለሰብ፣ በርካታ ሰዎች የተገደሉት በእንደቶ 01 ቀበሌ ከሚገኙ 3 የፀጥታ አካላት ካምፖች ውስጥ በሁለቱ ላይ በተፈፀመ ጥቃት እንደሆነ ተናግረዋል።
ስለታጣቂዎቹ ማንነት በግልፅ ባያውቁም "ከመንግሥት ታጣቂዎች ያልተናነሰ ወይም የሚበልጥ ትላልቅ መሳሪያ ያላቸው" እንደሆኑ ገልፀዋል።
ከሟቾቹ መካከል 10 ሰዎች "ምንም ዓይነት የሕግ ማስከበር ሥራ ውስጥ የሌሉ ንፁኃን ናቸው" ያሉት እኚህ የቢቢሲ ምንጭ፣ ሌሎቹ ግን ሁሉም የፀጥታ አስከባሪ ሚሊሻዎች ናቸው፤ ፖሊሶችም አሉ" ሲሉ ስለተገደሉት ሰዎች አስረድተዋል።
ንፁኃኖች ናቸው ያሏቸው አስሩ ሰዎች፣ ታጣቂዎቹ በየመንደሩ "ውስጥ ለውስጥ እየሔዱ የገደሏቸው" እንዲሁም ከጥቃቱ "ለማምለጥ ሲሯሯጡ ተተኩሶባቸው" የተገደሉ እንደሆኑም ገልፀዋል።
ሌላ ምንጭም ዛሬ የሞተውን ግለሰብ ጨምሮ በጥቃቱ የ38 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ተናግረዋል።
ወንድማቸውን ጨምሮ ሌሎችም ዘመዶቻቸው በጥቃቱ እንደተገደሉባቸው የተናገሩ ሌላ እማኝ ደግሞ፣ ትናንት ከጥቃቱ በኋላ ስለተፈጠረው ለቢቢሲ ሲያስረዱ ወንድማቸው ከመገደሉ በፊት በስልክ ስለሁኔታው እያወሩ እንደነበረ ተናግረዋል።
"ወንድሜ ገበሬ ነው። ወጣት ነው። ገና 27 ዓመት ሊሆነው ነው። ሌላ ምንም በደል የለበትም። ከእሱ ጋር ራሱ እየተደዋወልን ነበረ፤ ከፍተኛ ተኩስ ነበረ። በመሀል ስልኩ ተዘጋ" ብለዋል።
ስልኩ ከተቋረጠ በኋላ ግን ወንድማቸው ስለመገደሉ መርዶ የደረሳቸው እኚህ ተጎጂ፣ የአጎታቸውን ልጅ ጨምሮ ሌሎች ዘመዶቻቸውም የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
"ሰው አለቀ እንግዲህ። . . . ሰሚ የለም፤ ለእውነት የቆመ የለ። አይናችን እያየ አለቁ። . . . የሽርካውንም ሰምታችኋል። በተለይ አርሲ ክርስቲያኑ ምን እንደሚያደረግ አላውቅም" ሲሉ በተስፋ መቁረጥ ስሜታቸውን አጋርተዋል።
በትናንትናው ዕለት ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሌላ የአካባቢው ነዋሪ፣ ከሮቤ ከተማ 60 ኪሎ ሜትር ገደማ እንደምትርቅ በገለጿት እንደቶ አነስተኛ ከተማ ላይ ላይ ንጋት 11፡00 ላይ ከተጀመረው ጥቃት በፊት ሌሊት ከ10፡00 ጀምሮ በዙሪያው ተኩስ ይሰማ እንደነበር ተናግረዋል።
እንደቶ ላይ ጥቃቱ ሲጀመር ቤተክርስቲያን እየሔዱ እያለ ቀሲስ መላኩ የተባሉ ካህን የመጀመሪያው የጥቃቱ ዒላማ እንደነበሩ እና ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው በሕይወት መትረፋቸውን ገልፀዋል።
ከዚያ በኋላ እስከ ረፋድ 5፡30 በቀጠለው ጥቃት "ብዙ ምዕመናን ተገድለዋል" ሲሉ ሁኔታውን አስረድተዋል።
በጥቃቱ "ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው 6 ሰዎች" ትናንት በነበረው ሁኔታ ሕክምና ሳያገኙ ቆይተው ዛሬ ረፋድ ወደ ሕክምና ማዕከል እንደተወሰዱ ያነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል። ሆኖም ከመካከላቸው አንዱ ሀኪም ቤት ሳይደርሱ ሕይወታቸው ማለፉን ሁለት ምንጮች አስረድተዋል።
ቢቢሲ ካነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች አንዱ 4 ሰዎች መጥፋታቸውን ሲገልፁ ሌላ እማኝ ደግሞ የጠፉ ሰዎች ቁጥር 6 እንደሆነ ጠቅሰዋል። በመሆኑም የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል እማኞቹ ተናግረዋል።
በሥፍራው በምትገኘው እንደቶ ደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ሁለት የግቢ በሮች ላይም ተኩስ መፈፀሙን የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅት የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ አባላት ወደ አካባቢው ገብተው ጥበቃ እያደረጉ እንደሚገኙ የገለፁት እማኞቹ፣ ሆኖም ማኅበረሰቡ በከፍተኛ የደኅንነት ስጋት ውስጥ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
እስካሁን ድረስ ለጥቃቱ ኃላፊነቱን የወሰደ አካል የለም።
ኢሕአፓ ጥቃቱን በማውገዝ ባወጣው መግለጫ፣ "አሰቃቂ" ባለው ጥቃት "34 ንጹኀን ዜጎች መገደላቸውን" ከአካባቢው ነዋሪዎች ከደረሰው መረጃ መረዳቱን አመልክቷል።
ኢሕአፓ የእንደቶውን ጨምሮ ባለፉት ዓመታት የተፈፀሙ ጥቃቶች በአስቸኳይ፣ ገለልተኛ በሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲመረመር እና ለጥቃቱ ተጠያቂ የሆኑ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ ጠይቋል።