ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"ሕልሜ ሕዋ ነበር"፡ በትግራይ ሁሉም ነገሮች የተቀያየሩበት ስድስት ዓመታት
አክሱማዊት የማነ ወደ ሕልሟ ቀረብ የሚያደርጋትን ውሳኔ የወሰነችው ሁለተኛ ዓመት የዩኒቨርስቲ ተማሪ ሆና ነበር።
"የፊዚክስ ሰው ነኝ" ትላለች ፈገግ እያለች።
አዳማ ተወልዳ ያደገችው አክሱማዊት በ2012 ዓ. ም. ከፍተኛ የሁለተኛ ደረጃ ፈተና ውጤት ካመጣች በኋላ ነበር ምህንድስና ለማጥናት መቀለ ዩኒቨርስቲ የገባችው።
"ይሁን እንጂ ሁሌም ቢሆን ፍላሆቴ ሕዋ ነበር" ትላለች።
የዩኒቨርስቲ ሕይወት በሳቅ፣ በጠንካራ ጓደኞች እና ከሁሉም በላይ በወደፊት ተስፋ የተሞላ ነበር ስትል ታስታውሳለች።
"የሐሳብ፣ ፈጠራ፣ ቴክኖሎጂ እና የዕድል ጊዜ ነበር።"
በሕዋ ሳይንስ ሕልሟን ለመቀጠል ቁርጠኛ የነበረችው አክሱማዊት የትምህርት ዘርፏን ከምህንድስና ወደ አፕላይድ ፊዚክስ በመቀየር ጎን ለጎን ደግሞ በግል ኮሌጅ ማኔጅመንት እያጠናች ነበር።
ይሁን እንጂ ለነገ ያየችው ሕልም መሬት መንካት አልቻለም። ትምህርቷ ተስተጓጉሏል። ከዚህ ቀጥለው የመጡት ዓመታት ተስፈኝነቷን ፈትነዋል።
የአክሱማዊት ታሪክ በትግራይ ክልል የብዙ ወጣቶች ታሪክም ነው።
በ2013 ዓ. ም. የተቀሰቀሰው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የብዙዎችን ሕይወት አበላሽቷል። ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች እና ሌሎች የሕዝብ ተቋማትም ተመሳሳይ እጣ ደርሷቸዋል።
ከጠባሳ ጋር መኖር
የአውሮፓ ኮሚሽን ጥር 2018 ዓ. ም. ባወጣው ሪፖርት ባለፉት ሦስት ዓመታት በትግራይ ክልል 2.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ለትምህርት የደረሱ ሕፃናት ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን አስታውቋል።
በክልሉ 88 በመቶ የሚሆነው የትምህርት ቤት መሠረተ ልማት ጉዳት እንደደረሰበትም አክሏል።
በመላው ክልሉ ለዓመታት የዘለቀ የደኅንነት እጦት፣ ደካማ የመንግሥት ተቋማት፣ የበጀት እጥረት እና የመሠረታዊ አገልግሎት እጦት ሕይወትን እና ማኅበራዊ ደኅንነትን በእጅጉ ፈታኝ እንዳደረጉት ተንታኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአዲግራት ዩኒቨርስቲ የሕክምና እና ጤና ሳይንስ የቀድሞ መምህር የሆኑት ማዕረግ ዓለሙ "የስድስት ዓመታት ጠባሳ ከባድ ነው" ይላሉ።
"ከጦርነቱ በኋላ ወደ መደበኛ የመማር የማስተማር ሥራ መመለስ ቀላል አልሆነም" ይላሉ።
"ወጣቶች ሕልማቸውን እና ፍላጎታቸውን ለመከተል ተቸግረዋል። በርካቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል።"
አክሱማዊት ወጣትነት ለትምህርት፣ ለግላዊ እድገት እና ለአዋቂነት ለመዘጋጀት ወሳኝ ምዕራፍ እንደሆነ ታነሳለች።
አሁን በረድኤድ ድርጅት የፕሮግራም አስተባባሪ እና የአእምሮ ጤና ባለሙያ የሆኑት ማዕረግም በዚህ ይስማማሉ።
ይሁን እንጂ ወጣቶች ያለፉትን ስድስት ዓመታት በገንዘብ ችግር፣ በደኅንነት እጦት እና በስነ ልቦና ቁስል እየተፈተኑ መሆኑን ይገልፃሉ።
"በርካታ ወጣቶች በሱስ እየተሰቃዩ ነው። ሕፃናትን እና ታዳጊዎች በመቀለ ጎዳናዎች ወጥተው እና ሲጋራ ሲያጨሱ ማየት ልብ ይሰብራል" ይላሉ።
የክልሉ የድኅረ ጦርነት ፈተና አቅም የሌላቸው ቤተሰቦችን እና ተፈናቃዮችን ጨምሮ በዋናነት ተጋላጭ ቡድኖች ላይ በትሩን አሳርፏል።
እንደ የአውሮፓ ኮሚሽን ሁኔታው ወደ ብዝበዛ፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻ እና ስደት ክፍ ብሏል።
ከሁለት ዓመት በፊት በትግራይ ወጣቶች ማኅበር በተደረገ ዳሰሳ መሠረት ከ10 ወጣቶች ስምንቱ ሥራ አጥ ናቸው።
ተጨማሪ 12 በመቶ ወጣቶች በአካላዊ ጉዳት፣ የጤና ሁኔታ እና ሌሎች ጉዳዮች ምክንያት ሥራ መፈለግ አይችሉም።
ከግማሽ በላይ የሚሆኑ የዳሰሳው ተሳታፊዎች የተሻለ ዕድልን ፍለጋ አካባቢያቸውን ጥለው መውጣት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
ሰላምን ጥበቃ
ለአክሱማዊያት የጦርነቱ ማብቃት ወደ ወጠነችው ሕይወት መመለስ ማለት አልነበረም።
በ2016 ዓ.ም. ኢትዮጵያን ለቅቃ ወደ ኬንያ ተሰደደች።
"ይህ ባይፈጠር ኖሮ በእርግጠኝነት በሕዋ ሳይንስ እገፋ ነበር" ትላለች።
ኬንያ ከአፍሪካ ቀንድ ግጭትን፣ የፖለቲካ አለመረጋጋትን እና የሰብአዊ ቀውስን ሸሽተው የሚሰደዱ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን አስጠልላለች።
እንደ መንግሥታቱ ድርጅት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን መረጃ 43 ሺህ ኢትዮጵያዊያን ስደተኛ እና ጥገኝነት ጠያቂዎች እስከ ያለፈው ዓመት ድረስ በኬንያ ይኖራሉ።
በትግራይ ክልል የሰብአዊ ሠራተኛ ሆነው ክብሮም ወልደገብርኤል የዕድል እጦት፣ ተስፋ ማጣት እና ሕገ ወጥ ስደት ለወጣቶች ትልቅ ፈተና ሆነው ቀጥለዋል ይላል።
አክሱማዊት ምንም እንኳ ከባድ ሁኔታ ብታሳልፍም የተሻለ ወደፊት እንደሚገጥማት አሁንም ታምናለች።
ምንም እንኳ ሕልሟ ለስድስር ዓመታት ቢስተጓጎልም ሰዎች የሚከበሩበት፣ ዕድሎች ያሉበት እና ሰላም የፀናበት ጊዜ እንደሚመጣ እምነቷ ነው።
ይህ ተስፋዋ በትግራይ ክልል የሚኖሩ በርካታ ወጣቶች የሚጋሩት ነው።
"በርካታ ሕልሞች አሉኝ፤ ነገር ግን አሁን በጣም የሚያስፈልገን ሰላም እና ይቅርታ ነው" ይላል ክብሮም።