ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ውጤት ለሩሲያ፣ ለቻይና፣ ለኢራን፣ ለሳዑዲ . . . ምን ማለት ነው?
በአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ዴሞክራቶች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በሴኔቱ አብላጫ መቀመጫ አግኝተዋል። በዚህም ለቀሩት የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ሁለት የሥልጣን ዓመታት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱን መቆጣጠር ችለዋል።
በፖለቲካ ምህዳሩ የታየው ይህ ያልተጠበቀ ለውጥ ለፕሬዚደንቱ ትልቅ ሽንፈት ሆኗል። ትራምፕ ለበርካታ የሪፐብሊካን ፓርቲ ተወካዮች ሽንፈት የኢራን ጦርነት እና የኑሮ ውድነት አስተዋፅኦ ማድረጉን ተናግረዋል።
ለመሆኑ ይህ ያልተጠበቀ እና አባላቱን ያስደነገጠው የሪፐብሊካኖች ሽንፈት ለተቀረው ዓለም ምን ማለት ነው? የቢቢሲ ጋዜጠኞች ከዩክሬን እና መካከለኛው ምሥራቅ እስከ የቻይና የንግድ ግንኙነት ድረስ ምን ተፅዕኖ ሊኖረው እንደሚችል በዝርዝር ተመልክተውታል።
ኢራን
በለንደን የምትገኘው የቢቢሲ ፐርሽያ አገልግሎት ከፍተኛ ሪፖርተር የሆነችው ጎንችህ ሃቢቢያዛድ እንደዘገበችው፣ የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጂታባ ኻሜኒ በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ የታየው ለውጥ አሜሪካ በኢራን ላይ የምትፈፅመውን ጥቃት ይለውጣል ብሎ ማሰብ "እጅግ ስህተት ነው" ብለዋል።
ኻሜኒ አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት የምትፈፅም ከሆነም ምላሹ የበለጠ እንደሚከፋ አስጠንቅቀዋል።
አሜሪካ እና እስራኤል በጋራ በከፈቱት ጥቃት የተገደሉትን አባታቸውን አሊኻሜኒን ተክተው እስላማዊ ሪፐብሊኳን እየመሩ ያሉት ሞጂታባ ለወራት በአደባባይ ታይተው አያውቁም።
ይህንን አስተያየታቸውን የሰጡት እአአ በ1979 በቴህራን የሚገኘውን የአሜሪካ ኤምባሲ የኢራን ተማሪዎች የተቆጣጠሩበትን ዕለት በማስመልከት ረቡዕ ዕለት ባስተላለፉት ስድስት ገጽ የጽሑፍ መልዕክት ነው።
የባሕረ ሰላጤው አገራት
የቢቢሲ የደኅንነት ዘጋቢ ፍራንክ ጋርድነር እንደሚለው በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ሪፐብሊካኖች በምርጫው መሸነፋቸው ለባሕረ ሰላጤው አገራት እንደ ውድቀት ታይቷል።
ምክንያቱም ፕሬዚደንቱ እና ቤተሰባቸው ከአብዛኞቹ ጋር የግል እና የንግድ ግንኙነት አላቸው።
በዱባይ የትራምፕ ዓለም አቀፍ የጎልፍ መጫዎቻ ሥፍራ አለ። ኳታርም 400 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የግል አውሮፕላን በስጦታ አበርክታላቸዋለች።
ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ( ዩኤኢ) እና ሳዑዲ አረቢያ በዶናልድ ትራምፕ አማች ጃረድ ኩሽነር ድርጅት በሆነው 'አፊኒቲይ ካፒታል' ላይ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር አፍስሰዋል።
ትራምፕም እአአ በ2017 በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው የመጀመሪያውን የውጭ ጉብኝታቸው መዳረሻነት የመረጡት ሪያድን ነበር።
ሳዑዲ በተለይ ከትራምፕ በፊት ከነበሩት ከዴሞክራቱ ጆ ባይደን ጋር ውጥረት የበዛበት ግንኙነት ነበራት።
እአአ በ2022 ባይደን በቀጣናው ፀጥታ እና በኢነርጅ አቅርቦት ላይ ለመነጋጋር እንዲሁም የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማጠናከር ወደ ሳዑዲ አቅንተው እንደነበር አይዘነጋም። በዚያ ወቅት ሁለቱ መሪዎች እጃቸውን ጨብጠው በማጋጨት የተለዋወጡት ሰላምታ የሚረሳ አይደለም።
የባሕረ ሰላጤው አገራት መሪዎች፣ መርዛማ ጋዝ በመጠቀም ጥቃት ፈፅመዋል በሚል የሚከሰሱት የሶሪያው ፕሬዚደንት ባሽር አልአሳድ ላይ እርምጃ ሳይወስዱ በመቅረታቸው በቀድሞው ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ላይም ጥርጣሬ እና አለመተማመን ነበራቸው።
በዚህ ዓመት የተከሰተው የኢራን ጦርነትም ሰዎች በትራምፕ ላይ ያላቸውን አመለካከት እንዲለውጡ አድርጓቸዋል።
ጦርነቱ በተቀሰቀሰበት ወቅት አንድ አስተያየት ሰጪ " ፕሬዚደንት ትራምፕ በባሕረ ሰላጤው አገራት ላይ እሳት ለኩሰዋል" ብለዋል። አሁንም ኢራን በወሳኝ መሠረተ ልማቶቻቸው ላይ ጥቃት በመፈፀም የበቀል እርምጃ እንድትወስድ ያደረጋትን እና ከፍተኛ ውድመት ያስከተለውን ጦርነት የበለጠ ሊያቀጣጥሉት ይችላሉ የሚል ስጋት አለ።
በምርጫው ውጤት ላይ የኢራን ቦታ
ከዋሽንግተን ዲሲ የቢቢሲዋ ሪፖርተር ሬቤካ ፒደር እንደዘገበችው፣ የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚደንት ጄዲ ቫንስ ሪፐብሊካኖች በምርጫው ለመሸነፋቸው በኢራን ጦርነት አሳብበዋል ሲሉ ወቅሰዋል።
በእርግጥም ጦርነቱ በነዳጅ ዋጋ ላይ እንዲሁም በአሜሪካውያን ላይ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት አስከትሏል።
ትራምፕ እአአ በ2024 ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመናቸው የምርጫ ዘመቻ በሚያካሂዱበት ጊዜ የቤንዚን ዋጋን በጋሎን ከ2 ዶላር በታች ለማድረስ ቃል ገብተው ነበር። ሆኖም ባለፈው ኅዳር ወር ላይ የአንድ ጋሎን አማካይ ዋጋ 4.31 ዶላር ደርሷል።
ከዚህም በተጨማሪ ወደ ዋይት ሃውስ የሚገቡ ከሆነ አዲስ ጦርነት እንደማይኖር ተናግረው ነበር።
ከአጋማሽ ዘመን ምርጫው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ግን በኢራን ደሴት ላይ አዲስ ጥቃት ከፍተዋል። ጦርነቱን በመጀመራቸውም " እንደማይፀፀቱ" ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ለጦርነቱ እልባት ለመስጠት ከአሜሪካ ጋር በሚደረገው ድርድር የኢራን ዋነኛ ተደራዳሪ የምርጫ ውጤቱን ተከትሎ በሰጡት አስተያየት " አሜሪካውያን ጦርነት በቃ ብለዋል" ሲሉ ተናግረዋል።
ነገር ግን የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጂታባ ኻሜኒ በመግለጫቸው በምርጫው ውጤት "የአሜሪካ ፖሊሲ ይቀየራል" ብለው እንደማይጠብቁ ገልጸዋል።
ትራምፕም "ግጭቱ የሚያበቃው እኔ አብቅቷል ስል ነው" ሲሉ ዛሬ በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።
ቻይና
ላውራ ባይከር ከቻይና እንደዘገበችው፣ ቻይና የአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫን እንደ እድል ነው የተመለከተችው። ይህ ክፍለ ዘመን በቤይጂንግ እና በዋሽንግተን ያለው ግንኙነት ከፍተኛ ፉክክር የታየበት ነው።
ፕሬዚደንት ዢ ጂንፒንግ በዚህ ወር መጨረሻ ላይ ዶናልድ ትራምፕን ለመቀበል እየተሰናዱ ባሉበት በአሁኑ ወቅት በዚህ ውድድር የበላይነቱን እንደያዙ ሊሰማቸው ይችላል።
ትራምፕ ወደ አሜሪካ በሚገቡ የቻይና ምርቶች ላይ ቀረጥ ጥለዋል። ምክንያታቸውም የአሜሪካ አምራቾችን ከቻይና መናኛ ምርቶች መጠበቅ እንደሆነ ተናግረዋል።
ነገር ግን ዢ ከአሜሪካ ወደ አጋራቸው በሚገቡ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ቀረጥ በመጣል የአፀፋ ምላሽ በመስጠታቸው ትራምፕ 'ያጓኑት ድንጋይ ተመልሶ ከአናት' ሆኖባቸዋል። ይህ ማለት ልብሶች እና አሻንጉሊቶችን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ቁሳቁሶች ለአሜሪካውያን እጅግ ውድ ሆኗል።
ከዚህም በተጨማሪ ቻይና የአሜሪካ የግብርና ምርቶችን መግዛት ያቆመች ሲሆን የትራምፕ ደጋፊዎች ባሉበት ግዛቶች ያሉ አርሶ አደሮችን እየጎዳ ነው።
ይህ የንግድ ጦርነት በስምምነት የተቋጨ ቢሆንም ጊዜያዊ ስምምነቱ ጥር ወር መጨረሻ ላይ ያበቃል። በዚህም ቻይና ትራምፕ ከአጋማሽ ዘመን ምርጫው በኋላ አገግመው ስምምነት ላይ ለመድረስ ይፈልጋሉ ብላ ልታስብ ትችላለች።
ዢ ለቻይና የተሻለውን ለማድረግ ያሉ አድሎችን ያማትራሉ።
ሩሲያ
የዴሞክራቶችን ድል ተከትሎ የቢቢሲ የሩሲያ አርታኢ ስቲቭ ሮስንበርግ ከሩሲያ የተሰሙ መረጃዎችን አሰባስቧል።
በዚህም የቭላድሚር ፑቲን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ፣ " ዶናልድ ትራምፕ የሚያደርጉትን የሰላም ጥረት ይቀጥላሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ሲሉ ለሩሲያ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
" ሃሳቦች አሉ" ያሉት ፔስኮቭ " በቅርቡ ሌላ ዙር የሦስትዮሽ ድርድር ይኖራል" ብለዋል። ቃል አቀባዩ የሦስትዮሽ ድርድር ያሉት በሚቀጥለው ሳምንት በሩሲያ ፣ በዩክሬን እና በአሜሪካ መካከል በአቡ ዳቢ ለማካሄድ የታቀደውን ንግግር ነው።
ቃል አቀባዩ ፔስኮቭ አክለውም " በሜላኒያ ትራምፕ የተካሄደውንና ውጤታማ የሆነው የሜላኒያ ትራምፕን የሰብዓዊ የሰላም ጥረት ተመልክተናል" ብለዋል።
ፔስኮቭ የሰላም ጥረት ያሉት በቅርቡ በሩሲያ በተያዘችው ኦሌሽኪይ የሰብዓዊ ድጋፍ ዘመቻን ነው።
" ይህ ሁሉ እንደሚቀጥል ተስፋ እናደርጋለን" ሲሉም አክለዋል።
ይህ የሰላም ጥረት ምንም ለውጥ ካላመጣም ሞስኮ ከዚህ ቀደም እንዳደረገችው ዩክሬን እና አውሮፓን ልታሳብብ ትችላለች።
ከዚህም በተጨማሪ አሁን ላይ ዴሞክራቶችን እና የአጋማሽ ዘመን ምርጫውን ምክንያት ልታደርግም ትችላለች። ሞስኮ ምን አልባት ዶናልድ ትራምፕን ላትወቅስ ትችላለች። ምክንያቱም ክሬሚሊን ከትራምፕ ጋር ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ብዙ ጥረት አድርጋለች። በመሆኑም ሞስኮ አሁንም ከትራምፕ አስተዳደር ጋር የምጣኔ ሃብት ትብብሯን ለማሳደግ ተስፋ ታደርጋለች።
የዓለም ሚዲያ ምን አለ?
በዩክሬን፣ በኢራን እና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚኖሩ ሰዎች የአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ የአገር ውስጥ የፖለቲካ ውድድር ብቻ አድርገው እንዳልተመለከቱት ቢቢሲ ሞኒተሪንግ ያጠናቀራቸው ሪፖርቶች አመልክተዋል።
ይበልጥ ያተኮሩት የምርጫው ውጤት እየተካሄዱ ባሉ ግጭቶች ላይ ምን ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል በሚለው ላይ ነው።
የዩክሬን ተንታኞች ትኩረታቸው ትራምፕ ጦርነቱን እንዴት ነው የተቆጣጠሩት በሚለው ላይ ነው። ጋዜጠኛ ሮማን ቲይምባልዩክም ፕሬዚደንቱ " ሌሎች ሁሉንም ጦርነቶች ፈትተው፤ ራሳቸውን በሚመለከተው ጦርነት ተሸንፈዋል" ሲሉ አፊዘዋል። ይህ ትራምፕ ዓለም አቀፍ ግጭቶችን ማስቆም እችላለሁ ሲሉ በተደጋጋሚ ለሚሰጧቸው አስተያየት የቀረበ ትችት ነው።
ሩሲያ የዩክሬን የኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት መሰንዘሯን በቀጠለችበት በዚህ ወቅት አንዳንድ የኪየቭ ነዋሪዎች የዴሞክራቶች ማሸነፍ በሞስኮ ላይ ጠንካራ ማዕቀብ ለመጣል እንደሚረዳ ተስፋ ሰንቀዋል።
ሌሎች በበኩላቸው በዋሽንግተን ያለው የፖለቲካ ለውጥ ዩክሬንን በተመለከተ ያለው ፖሊሲ ላይ አዲስ ችግር ሊደቅን ይችላል ሲሉ ስጋት ገብቷቸዋል።
በሞስኮ፣ ክሬሚሊን ትራምፕ ጦርነቱን ለመቋጨት የማሸማገል ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ በይፋ ያላትን ተስፋ ገልጻለች። ሌላ የሩሲያ እና የዩክሬን ድርድር በዚህ ወር ውስጥ እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
ሆኖም ጦርነቱን የሚደግፉ የሩሲያ ድምጾች ዴሞክራቶች የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱን መቆጣጠራቸው ትራምፕ ከክሬሚሊን ጋር ስምምነት ላይ እንዳይደርሱ ወይም የሩሲያን ማዕቀቦች ለማላላት ማነቆ ሊሆንባቸው እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢራን አስተዳደር እና ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸው መገናኛ ብዙኃን የዴሞክራቶችን ማሸነፍ የትራምፕን የጦርነት ፖሊሲ ሕዝብ እንደተቃወመው አድርገው ተመልክተውታል።
የኢራን መገናኛ ብዙኃንም የምርጫውን ውጤት አሜሪካ ከቴህራን ጋር ለገባችው ወታደራዊ ግጭት እየከፈለችው ያለ "የፖለቲካ ዋጋ" ሲሉ ገልጸውታል።