ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የካሊፎርኒያ አስተዳዳሪ የ548 ሰዎችን የሞት ፍርድ ወደ እድሜ ልክ እስራት ቀየሩ
የካሊፎርኒያ ግዛት አስተዳዳሪ ጋቪን ኒውሶም 548 እስረኞች ላይ የተጣለውን የሞት ፍርድ በሙሉ በመሻር፣ በምትኩ የዕድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ ወሰኑ።
"አሁን እነዚህ ወንጀለኞች ተረስተው በእስር ቤት እንዲሞቱ ማድረግ እንችላለን፤ እኛ ግን ተጎጂዎችን ለዘላለም እያሰብን እና እያከበርን እንቀጥላለን" ሲሉ በደብዳቤያቸው ላይ ገልጸዋል።
በካሊፎርኒያ ግዛት የሞት ፍርድ ውሳኔ ቢሰጥም እአአ ከ2006 ጀምሮ በሞት የተቀጣ አንድም እስረኛ የለም።
ሆኖም ባለሙያዎች እርምጃው በየዓመቱ በሚሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር የፍርድ ቤት ወጪን ሊያስቀር እንደሚችል ይገልጻሉ።
እአአ በ1978 መራጮች የሞት ፍርድን ዳግም ካጸደቁ በኋላ 13 እስረኞች ብቻ ተገድለዋል።
የዴሞክራት ፓርቲ አባል የሆኑት ኒውሶም፣ በአሜሪካ ብዙ ሕዝብ ያላት ግዛት አስተዳዳሪ ሲሆኑ ለ2028 የፕሬዚዳንትነት ምርጫ ሊወዳደሩ ከሚችሉ እጩዎች መካከል ስማቸው እየተጠቀሰ ይገኛል።
ጋቪን ኒውሶም የሥልጣን ዘመናቸው በጥር ወር የሚጠናቀቅ ሲሆን በቅርቡ በተደረገው ምርጫ ያሸነፉት የዴሞክራት ፓርቲ አባሉ ዛቪየር ቤሴራ ቦታቸውን ተረክበው ግዛቲቱን ማስተዳደር ይቀጥላሉ።
ኒውሶም በደብዳቤያቸው ላይ በሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸውን ሥልጣን በመጠቀም የሞት ፍርዶቹን ወደ የዕድሜ ልክ እስራት መቀየራቸውን አብራርተዋል።
"ለ30 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በሕዝብ አገልግሎት ላይ ከቆየሁ በኋላ፣ መንግሥት በፍትሃዊ መንገድ ሊያሳካቸው የሚችላቸው ነገሮች ገደብ እንዳላቸው ተረድቻለሁ" ሲሉ ኒውሶም ገልጸዋል።
"ይህን እርምጃ የወሰድኩት በመንግሥት የሚፈጸም ግድያ ከካሊፎርኒያ እሴቶች ጋር የማይጣጣም፣ የሕጋዊ ሥርዓታችንን መሠረት የሚያዳክም እና የእያንዳንዳችንን ክብር የሚቀንስ መሆኑን አበክሬ ስለማምን ነው" ብለዋል።
ካሊፎርኒያ በሞት ፍርድ በሚቀጡ እስረኞች ብዛት ከአሜሪካ ግዛቶች ቀዳሚዋ ነች። ኒውሶም እአአ በ2019 በግዛቱ የሞት ፍርድ እንዳይፈጸም ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር።
ኒውሶም ውሳኔያቸውን አስቸጋሪ ቢሆንም "ትክክለኛ የሞራል እርምጃ" ሲሉ ገልጸውታል። በካሊፎርኒያ ውስጥ በርካቶች አሰቃቂ ወንጀል የሚፈጽሙ ሰዎች የሞት ቅጣት ይገባቸዋል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸው "መንግሥት እነሱን በሞራል ደረጃ ሊገድላቸው አይችልም" ሲሉ ተናግረዋል።
ኒውሶም እንዳሉት፣ በማንኛውም መስፈርት ሲታይ የካሊፎርኒያ የሞት ቅጣት አፈጻጸም ሥርዓት "ውድቀት" ነው። ሥርዓቱ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ አልተተገበረም፤ ወደፊትም በፍትሃዊ መንገድ ሊተገበር አይችልም ብለዋል። እንዲሁም ንጹሃን ሰዎች በስህተት እንዲፈረድባቸው አድርጓል ሲሉ አብራርተዋል።
እሳቸው በሕግ አግባብ ተፈጻሚ ሊያደረጉት የሚችሉት እጅግ ከባዱ ቅጣት እና ግዛቱም በተገቢው መንገድ ሊያስፈጽመው የሚችለው ቅጣት ያለ ምንም ይቅርታ የዕድሜ ልክ እስራት መሆኑን ገልጸዋል።
የእድሜ ልክ እስራት ውሳኔያቸው አንዳንድ የካሊፎርኒያ ነዋሪዎችን እንደሚያስቆጣና እንደሚያሳዝን መገንዘባቸውን ጠቅሰው፣ ይህም "ሁልጊዜ በልቤ ላይ ከባድ ሸክም ሆኖ ይቆያል" ብለዋል።
"እንደ አስተዳዳሪ፣ ለዚህ ውሳኔና ለሚያስከትለው ውጤት እኔ ብቻ ኃላፊነቱን እወስዳለሁ፤ ልክ እያንዳንዱ የሞት ፍርድ ቢፈጸም ኖሮ ለዚያም እኔ ብቻ እንደምጠየቅ ሁሉ" ሲሉ ጽፈዋል።
"ስለዚህ የሕሊናዬን ድምጽ ለመከተል ተገድጃለሁ፤ እንዲሁም በሕገ መንግሥታችን በተሰጠኝ ሥልጣን መሠረት ለካሊፎርኒያ ግዛት ጥቅም ይህን ውሳኔ ወስኛለሁ" ብለዋል።
በአሜሪካ ውስጥ የወንጀል ክሶችን የመክፈትና የሞት ፍርድን የማስፈጸም ሥልጣን በአብዛኛው ለግዛቶች የተሰጠ በመሆኑ፣ በዚህ ጉዳይ የግዛት አሰተዳዳሪዎች ከፍተኛ ሚና አላቸው።
የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የሕግና የሲቪል ነጻነቶች ፕሮፌሰር በርናርድ ኢ. ሃርኮርት ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ በአሜሪካ የሞት ቅጣት አሁንም ሰፊ ድጋፍ ቢኖረውም፣ ለፕሬዚዳንትነት ሊወዳደሩ የሚችሉ ፖለቲከኞች በምርጫ ዋዜማ የሞት ቅጣትን በግልጽ የሚቃወሙ አቋም መያዛቸው አዲስ አይደለም።
ፕሮፌሰሩ፣ ፍራንሷ ሚተራንድ በ1981 የፕሬዚዳንትነት ዘመቻቸው ወቅት ተመሳሳይ አቋም መውሰዳቸውን አስታውሰው፣ "ከፍተኛውን የሥነ ምግባር መደላድል ያዙ እና ሕዝቡም ለዚያ ሸለማቸው" ብለዋል።
በፌዴራል ደረጃ፣ የሞት ቅጣትን ለረጅም ጊዜ ሲደግፉ የቆዩት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የሞት ቅጣትን "እጅግ አሰቃቂ ወንጀሎችንና ገዳይ የጥቃት ድርጊቶችን በአሜሪካ ዜጎች ላይ የሚፈጽሙ ሰዎችን ለመከላከልና ለመቅጣት አስፈላጊ መሣሪያ" ሲሉ ገልጸውታል።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2020 በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው ወቅት፣ ትራምፕ በፌዴራል ደረጃ በሞት ቅጣት ላይ ለ20 ዓመታት ያህል ተጥሎ የነበረውን እገዳ በማንሳት፣ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ 13 የሞት ፍርዶች እንዲፈጸሙ አዘዋል።
በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ወቅት እገዳው እንደገና ተመልሶ ቢጸናም፣ ትራምፕ እአአ በ2025 ሁለተኛውን የሥልጣን ዘመናቸውን በጀመሩበት ቀን የፈረሙት ፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዝ የፌዴራል የሞት ቅጣት እንደገና እንዲተገበር አድርጓል።