ሩሲያ በዩክሬን ወሳኝ መሠረተ ልማት ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ከ600ሺህ በላይ ነዋሪዎች ከኤሌትሪክ አቅርቦት ውጪ ሆኑ
ሩሲያ በዩክሬን የኤሌትሪክ ኃይል መሠረተ ልማት ተቋማት ላይ ጥቃት ከፈጸመች በኋላ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደተቋረጠባቸው የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተናገሩ።
በማዕከላዊው የዲኒፕሮፔትሮቭስክ ክልል “ከ600 ሺህ በላይ ነዋሪዎች የኤሌትሪክ ኃይል ተቋርጦባቸዋል” ሲል የኃይል ኩባንያው ዲቲኢኬ በቴሌግራም ገጹ አስታውቋል። ኩባንያው በሌሊት በተፈጸመ ጥቃት ወሳኝ የኃይል ተቋማት መጎዳታቸውን ገልጿል።
ዲቲኢኬ የኤሌክትሪክ አገልግሎቱን ለመመለስ እየሠራ መሆኑን ገልጾ፣ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ሥራውን ማስተጓጎላቸውን አክሏል።
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ቀደም ሲል ሩሲያ በቀጣይ ሳምንት ከሚካሄዱ የሦስትዮሽ ውይይቶች በፊት የምትፈጽማቸውን ጥቃቶች አጠናክራ ቀጥላለች ሲሉ ከሰው ነበር።
በሌላ ጥቃት፣ በሰሜን ምስራቅ የካርኪቭ ክልል ውስጥ ያለ “ወሳኝ መሠረተ ልማት ተቋም” በሩሲያ ድሮን እንደተመታ የዝላቶፒል ከተማ ከንቲባ ሚኮላ ባክሼየቭ በማኅበራዊ ሚዲያ ገልጸዋል።
“በካርኪቭ ክልል ወደ 250 ሺህ የሚጠጉ ተጠቃሚዎች የኤሌትሪክ ኃይል ተቋርጦባቸዋል” ሲሉም ባክሼየቭ ተናግረዋል።
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በሌሊት የተፈጸሙት ጥቃቶች “በመላ አገሪቱ ሰፊ የኃይል መቋረጥ” እንዳስከተሉ ተናግረዋል።
ዜሌንስኪ ጥቃቶቹ በዩክሬን የኃይል መሠረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረሳቸው በርካታ ክልሎችና ከተሞች ከኤሌክትሪክ ኃይል ውጪ መሆናቸውን ጨምረው ገልጸዋል።