ቀጥታ , የሁቲ አማፂያን ሳዑዲ አረቢያ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 33 ሰዎች መገደላቸውን አስታወቁ

የመን ከሁቲ ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸው መገናኛ ብዙኃን ሳዑዲ አረቢያ በፈጸመችው የአየር ጥቃት እናቶች እና ሕፃናትን ጨምሮ ቢያንስ 33 ሰዎች መገደላቸውን ዘገቡ። በየመን ዓለም አቀፍ ዕውቅና ላለው መንግሥት ድጋፍ የሚያደርገው በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው ጥምር ኃይል እስካሁን ስለጥቃቱ አስተያየት አልሰጠም። በሁቲዎች የሚተዳደረው አል ማሲራ የቴሌቪዥን ጣቢያ በቀጥታ ባሰራጨው ምስል፣ ከዋና ከተማዋ ሰነዓ በስተምሥራቅ በምትገኘው አል-ሻሪያ ከተማ ውስጥ የሕይወት አድን ሠራተኞች ከፈራረሱ ሕንጻዎች ሥር አስከሬኖችን ሲያወጡ አሳይቷል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ሩሲያ በዩክሬን ወሳኝ መሠረተ ልማት ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ከ600ሺህ በላይ ነዋሪዎች ከኤሌትሪክ አቅርቦት ውጪ ሆኑ

    ሩሲያ በዩክሬን የኤሌትሪክ ኃይል መሠረተ ልማት ተቋማት ላይ ጥቃት ከፈጸመች በኋላ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደተቋረጠባቸው የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተናገሩ።

    በማዕከላዊው የዲኒፕሮፔትሮቭስክ ክልል “ከ600 ሺህ በላይ ነዋሪዎች የኤሌትሪክ ኃይል ተቋርጦባቸዋል” ሲል የኃይል ኩባንያው ዲቲኢኬ በቴሌግራም ገጹ አስታውቋል። ኩባንያው በሌሊት በተፈጸመ ጥቃት ወሳኝ የኃይል ተቋማት መጎዳታቸውን ገልጿል።

    ዲቲኢኬ የኤሌክትሪክ አገልግሎቱን ለመመለስ እየሠራ መሆኑን ገልጾ፣ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ሥራውን ማስተጓጎላቸውን አክሏል።

    የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ቀደም ሲል ሩሲያ በቀጣይ ሳምንት ከሚካሄዱ የሦስትዮሽ ውይይቶች በፊት የምትፈጽማቸውን ጥቃቶች አጠናክራ ቀጥላለች ሲሉ ከሰው ነበር።

    በሌላ ጥቃት፣ በሰሜን ምስራቅ የካርኪቭ ክልል ውስጥ ያለ “ወሳኝ መሠረተ ልማት ተቋም” በሩሲያ ድሮን እንደተመታ የዝላቶፒል ከተማ ከንቲባ ሚኮላ ባክሼየቭ በማኅበራዊ ሚዲያ ገልጸዋል።

    “በካርኪቭ ክልል ወደ 250 ሺህ የሚጠጉ ተጠቃሚዎች የኤሌትሪክ ኃይል ተቋርጦባቸዋል” ሲሉም ባክሼየቭ ተናግረዋል።

    የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በሌሊት የተፈጸሙት ጥቃቶች “በመላ አገሪቱ ሰፊ የኃይል መቋረጥ” እንዳስከተሉ ተናግረዋል።

    ዜሌንስኪ ጥቃቶቹ በዩክሬን የኃይል መሠረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረሳቸው በርካታ ክልሎችና ከተሞች ከኤሌክትሪክ ኃይል ውጪ መሆናቸውን ጨምረው ገልጸዋል።

  2. የሳዑዲ ነዳጅ ኩባንያ አራምኮ ሕንፃ በሚሳኤል ጥቃት ጉዳት እንደደረሰበት እማኞች ተናገሩ

    በሳዑዲ አረቢያ ሪያድ የሚገኘው የአገሪቱ ብሔራዊ የነዳጅ ኩባንያ (አራምኮ) ሕንፃ አካበቢ እሑድ ጠዋት ከፍተኛ ፍንዳታ መስማታቸውን ለፈረንሳይ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ የዓይን እማኞች ተናገሩ።

    በሪያድ ንጉስ አብደላ ፋይናንስ ዲስትሪክት የሚገኘው የአራምኮ ሕንፃ በበርካታ ወለሎች ላይ ጉዳት መድረሱን እማኞች ጨምረው ገልጸዋል።

    በጥቃቱ አንዳንድ ወለሎች ክፉኛ የተጎዱ ሲሆኑ፣ ሌሎች ወለሎች ላይ ደግሞ በውጫዊ ክፍሎቻቸው (መስኮቶች) ላይ ጉዳት ታይቷል።

    የዓይን እማኞች በደኅንነት ስጋት ምክንያት ስማቸው እንዳይገለጽ ጠይቀዋል።

    በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው ጥምር ጦር እሁድ ማለዳ ወደ ሪያድ እና ሌሎች ክልሎች ያነጣጠሩ ያላቸው ሁለት ባለስቲክ ሚሳኤሎችን እና ሁለት ክሩዝ ሚሳኤሎችን ማክሸፉን አስታውቋል።

    ጦሩ ሚሳኤሎቹን የተኮሱት ሁቲዎች ናቸው ሲል ከስሷል።

    የሳዑዲ የኢነርጂ ሚኒስቴር በበኩሉ የተሞከረው ጥቃት “የወዳደቁ ቅሪቶች በሕንፃው ላይ ቀላል ጉዳት አስከትለዋል” ብሏል።

    በአደጋው የተጎዳ ወይም የሞተ ሰው እንደሌለም ጨምሮ ገልጿል።

    አሶሼትድ ፕሬስ የሳዑዲን ዓለም አቀፍ ግንኙነት ማዕከል እና አራምኮ አስተያየት እንዲሰጡ ቢጠይቅም ወዲያውኑ ምላሽ አላገኘም።

    በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው ጥምር ጦር አክሎም ከየመን ጋር በድንበር የሚዋሰነውን ደቡባዊ ክልል ዒላማ ያደረገ አንድ ባለስቲክ ሚሳኤል ማክሸፉን አስታውቋል።

    ይህ አካባቢ በተደጋጋሚ በሁቲ ታጣቂዎች ጥቃቶች ይደበደባል።

    የሁቲ ጥቃት የተሰማው ቅዳሜ እለት በአማፂዎች ቁጥጥር ስር ባለችው የየመን ዋና ከተማ ሰንዓ አቅራቢያ በሳዑዲ የአየር ጥቃቶች ከተፈፀሙ በኋላ ነው።

    የሁቲ ባለሥልጣናት እንዳሉት በእነዚህ ጥቃቶች ቢያንስ 27 ሰዎች ተገድለዋል።

  3. የኢራንን ጦርነት ለማስቆም የሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ከምን ደረሱ?

    የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ መሐመድ ቢን አብዱራህማን ቢን ጃሲም አል ታህኒ የአሜሪካ-ኢራን ግጭትን ለመፍታት የሽምግልና ጥረቶች እንደቀጠሉ ተናግረው፤ አሜሪካ “መፍትሄ ለማግኘት እርምጃዎችን ለመውሰድ” ፍላጎት እና ዝግጁነት አላት ብለዋል።

    የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተያየት የተሰማው ዶናልድ ትራምፕ ዋይት ሐውስ ከኢራን ተወካዮች ጋር እየተነጋገረ መሆኑን እና “ከኢራን ጋር [በሚደረገው ድርድር] የተሻለ እመርታ አሳይተናል” ካሉ በኋላ ነው።

    ይሁን እንጂ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት፤ ትራምፕ በመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴት እና በአሜሪካ ማዕከላዊ ጦር ኮማንድ (ሴንትኮም) አዛዥ ብራድ ኩፐር ዳግም ጥቃቶች እንዲጀምሩ ግፊት እየተደረገባቸው ነው።

    የሴንትኮም አዛዥ የአሜሪካን የባሕር እገዳ በማስፋፋት፣ ከኢራን ወደቦች የሚነሱ የአቅርቦት መስመሮችን “ለማስተጓጎል” የተዘጋጀ አዲስ ዕቅድ አስተዋውቀዋል።

    የኢራን የደኅንነት ጉዳዮች ኃላፊ ሞህሴን ሬዛኢ ደግሞ ትራምፕ ጥቃቶችን ዳግም እንዳይጀምሩ በማስጠንቀቅ፣ “ጦርነት ብትጀምሩ አውዳሚ ምላሽ ይገጥማችኋል” ብለዋል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በ48 ሰዓታት ውስጥ ከ12 የቀጣናው አገራት አቻዎቻቸው ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የእስላማዊ ሪፐብሊክ ዜና ወኪል ዘግቧል።

    አራግቺ ከቀጣናው ውጭ ያሉ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት የሌለበት ክልላዊ የደኅንነት ሥርዓት እንዲፈጠር ጥሪ አቅርበዋል።

  4. የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ በእሳት ከተያያዘ የጭነት መርከብ ውስጥ 22 ሰዎችን ማውጣቷን አስታወቀች

    የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ብሔራዊ ዘብ በኦማን ባሕረ ሰላጤ በአንድ የጭነት መርከብ ላይ እሳት ከተነሳ በኋላ 22 ሰዎችን ማዳኑን አስታወቀ።

    ብሔራዊ ዘቡ በኤክስ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ በመርከቡ ላይ እሳት ከተነሳ በኋላ ከሠራተኞች ጥሪ እንደደረሰው እና ለዚያ ምላሽ መስጠቱን ገልጿል።

    መግለጫው አክሎም የሕይወት አድን ሠራተኞች መርከቧ ያላችበትን ስፍራ ከለዩ በኋላ በውስጧ የነበሩትን 22 የአረብ ዜግነት ያላቸው ሠራተኞችን በሙሉ ማዳናቸውን ጠቅሷል።

    ብሔራዊ ዘቡ በመግለጫው ላይ “አስፈላጊውን የመጀመሪያ ሕክምና ከሰጧቸው በኋላ ለሚመለከታቸው ባለሥልጣናት አስረክበዋቸዋል፤ ሁሉም በተረጋጋ የጤና ሁኔታ ላይ ይገኛሉ” ብሏል።

    የእሳቱ መንስዔ ምን እንደሆነ ግን አልተገለጸም።

    ቀደም ሲል የኢራን አብዮታዊ ዘብ በሆርሙዝ ወሽመጥ አቅራቢያ ሁለት የነዳጅ ጫኝ መርከቦች በፈንጂ ተመትተው በእሳት መያያዛቸውን ገልጸ ነበር።

    አብዮታዊ ዘቡ እንዳለው ሁለቱ መርከቦች የቀዘፋ ስርዓት ጠቋሚ መሣሪያቸውን አጥፍተው ባልተፈቀደ መስመር ላይ እየተጓዙ ነበር።

    አንደኛዋ መርከብ ከሆርሙዝ ወሽመጥ በስተ ምሥራቅ መመታቷን፣ ሌላኛዋ ደግሞ በወሽመጡ ውስጥ መመታቷን በመግለጽ በርካታ ጥሰቶችን ፈጽመዋል ሲል ከስሷል።

    በተየዓያዘ ዜና የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ በኢራን ላይ የሚያነጣጥር አዲስ ግብረ ኃይል መመሥረቱንና ለወራት ሲተገበር የቆየውን በቴህራን ወደቦች ላይ የተጣለ የባሕር እገዳ ማስፋፋቱን አስታውቋል።

    ሴንትኮም ባወጣው መግለጫ፣ እርምጃው ቴህራን የጦር መሣሪያዎችን ለማጓጓዝ የምድር መስመሮችን እንዳትጠቀም የሚያደርግ መሆኑን ገልጿል።

    እንደሴንትኮም ገለጻ፣ ዘመቻው የኢራንን የገቢ ምንጮች ለማቋረጥ ያለመ ሲሆን፣ ይህም በኢራን የመሬት ድንበሮች ብቻ ሳይሆን በካስፒያን ባሕር አካባቢም ተፈጻሚ እንደሚሆን ተገልጿል።

    እርምጃው በኢራንና በአሜሪካ መካከል ያለው ውጥረት እየተባባሰ በመጣበት ወቅት የተወሰደ ሲሆን፣ ቀጣናዊ የደህንነትና የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ተጨማሪ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ተገምቷል።

  5. በሳዑዲ የሚመራው ጥምር ኃይል ከሁቲ አማፂያን የተወነጨፉ ሚሳዔሎችን ማክሸፉን አስታወቀ

    በየመን ከሁቲዎች ጋር እየተዋጋ የሚገኘው በሳዑዲ አረቢያ የሚመራ ጥምር ኃይል፣ ሁለት ባለስቲክ እና ሁለት ክሩዝ ሚሳዔሎችን ማክሸፉን አስታወቀ።

    የጥምር ኃይሉ ቃል አቀባይ ሜጀር ጄኔራል ቱርኪ አል-ማሊኪ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባወጡት መግለጫ፣ “የአየር መከላከያ ሥርዓቶች ወደ ሪያድና ወደ ደቡብ አካባቢዎች ያነጣጠሩ ሁለት ክሩዝ ሚሳዔሎችን አክሽፈው አውድመዋል” ብለዋል።

    አል-ማሊኪ ክሩዝ ሚሳዔሎቹ ከየት እንደተተኮሱ ተጨማሪ ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጡም።

    ይህ መግለጫ የየመን ሁቲ አማፂያን ወደ ሳዑዲ ዋና ከተማ ሪያድ አቅጣጫ የተኮሷቸውን ሁለት ባለስቲክ ሚሳዔሎች ማክሸፋቸውን ከገለጹ ከአንድ ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የተሰጠ ነው።

    ከዚህ በፊትም እሁድ ዕለት፣ ጥምር ኃይሉ ከሁቲዎች ወደ ሳዑዲ ምሥራቃዊ ግዛት የተወነጨፈ ሌላ ባለስቲክ ሚሳዔል ማክሸፉን አስታውቆ ነበር።

    እነዚህ ጥቃቶች የተፈጸሙት በየመን መንግሥት ኃይሎችና አንሳር አላህ በመባል በሚታወቁት ሁቲዎች መካከል ውጊያው እየተባባሰ በመጣበት ወቅት ነው።

    የየመን መንግሥት ኃይሎች ባለፈው ወር “የየመን ጎህ” በተሰኘ ዘመቻ ዋና ከተማዋን ሰነዓን ጨምሮ ሁቲዎች የተቆጣጠሯቸውን አካባቢዎች መልሶ ለመቆጣጠር ጥቃት ጀምረዋል።

    የሁቲዎች የጤና ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አኒስ አል-አስባሂ ቅዳሜ ዕለት እንዳስታወቁት፣ በሰነዓ አቅራቢያ በምትገኘው አል-ሻሪያ መንደር ላይ በሳዑዲ አረቢያ በሚመራው ጥምር ኃይል በተፈጸመ የአየር ጥቃት 33 ሰዎች ተገድለዋል።

    ከሟቾቹ መካከል ስምንት ሴቶችና 13 ሕፃናት እንደሚገኙበትም ተገልጿል።

    በሳዑዲ አረቢያ በሚመራው ጥምር ኃይል በኩል ስለ ጥቃቱ እስካሁን ይፋዊ አስተያየት አልተሰጠም።

  6. ኢራን ለእስራኤልና አሜሪካ ሲሰሩ ተገኝተዋል ያለቻቸውን ሦስት ሰዎች በሞት ቀጣች

    ኢራን ለእስራኤልና ለአሜሪካ ሲሰሩ ነበር፣ እንዲሁም ባለፈው ዓመት በጥር ወር በተካሄዱ የተቃውሞ ሠልፎች ወቅት በትጥቅ የታገዘ ሁከት ውስጥ ተሳትፈዋል በሚል ተከስሰው የተፈረደባቸውን ሦስት ሰዎች በሞት ቀጣች።

    ዛሬ እሁድ ዕለት ተፈጻሚ የሆነው የሞት ቅጣት ኢራን በቅርብ ወራት ከተቃው ሞሠልፎች ጋር በተያያዘ ስትፈጽማቸው የነበሩት ተከታታይ የሞት ቅጣቶች አካል ነው።

    እንደ ኢራን የፍትህ ቢሮ ገለጻ፣ ሀሰን ዲዮባንድ፣ ሀሚድ ካዜሚ እና ሬዛ ዛንጋኔህ የጦር መሣሪያዎችን፣ የእጅ ቦምቦችን እና ተቀጣጣይ ጋዝን በመጠቀም በካራጅ ከተማ የሚገኙ የሕዝብ ተቋማትን በማቃጠል እና የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ተቋምን በማውደም ተከሰው ነበር። ይህ የግለሰቦቹ ድርጊትም በአንዳንድ አካባቢዎች የኃይል መቆራረጥ እንዲከሰት አድርጓል ተብሏል።

    የአገሪቱ የፍትህ ቢሮ እንደገለጸው፣ ሀሰን ባለፈው ዓመት እአአ በጥር 11 ቀን ከሕዝብ ንብረት ማውደም ጥቃቶች እና ሁከትን ከማነሳሳት ጋር በተያያዘ በተደረገ ምርመራ ዋና ተጠርጣሪ መሆኑ ከታወቀ በኋላ በቁጥጥር ሥር ውሎ ነበር።

    ከዚያ በኋላ በእርሱ ይመራ በነበረው ቡድን ውስጥ በሁከቱ ተሳትፈዋል የተባሉ 10 ተጨማሪ ግለሰቦች ተይዘዋል።

    ሦስቱ ተከሳሾች በሞት እንዲቀጡ የተፈረደባቸው ሲሆን፣ ንብረቶቻቸውም እንዲወረሱ ታዟል። የሞት ፍርዳቸው በኢራን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከጸና በኋላ ተፈጽማ ሆኗል።

    በጉዳዩ ውስጥ የተካተቱት ሌሎች ተከሳሾች ደግሞ ከ5 እስከ 10 ዓመት የሚደርስ የእስራት ቅጣት ተፈርዶባቸዋል።

    ተጨማሪ ዘገባዎች፦

  7. አሜሪካ በኦማን ባሕረ ሰላጤ በመርከብ ላይ ጥቃት መፈጸሟን ስትገልጽ፣ ኢራን ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች በፈንጂ መመታታቸውን አስታወቀች

    አሜሪካ በኦማን ባሕረ ሰላጤ በአንድ የጭነት መርከብ ላይ ወታደራዊ እርምጃ መውሰዷን ስትገልጽ የኢራን ጦር በበኩሉ ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች በፈንጂ እንደተመቱ አስታውቋል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ቅዳሜ የኢራን ወደቦች ውስጥ ገብቶ ሲወጣ የነበረ መርከብ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውም ችላ በማለቱ መመታቱን ይፋ አድርጓል።

    በሌላ ዜና የኢራን ጦር በሆርሙዝ አካባቢ ሁለት መርከቦች በፈንጂ ተመትተው በእሳት መያያዛቸውን ተናግሯል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ መርከቧ የቅዱስ ኪትስ እና ኔቪስባንዲራን የምታውለበልብ ነበረች ያለ ቢሆንም የኢራን ጦር ግን የመርከቦቹን ባለቤት ወይንም መዳረሻ አላሳወቀም።

    የአሜሪካ ጦር በኢራን ወደቦች የሚገቡ እና የሚወጡ መርከቦች ላይ የእንቅስቃሴ ገደብ ከጣለ ወራት አልፈውታል።

    አሜሪካ ለመጨረሻ ጊዜ የጭነት መርከብን መምታቷን ያሳወቀችው ከአንድ ወር በፊት በኦማን ባሕረ ሰላጤ ላይ ነበር።

    ቅዳሜ ዕለት መርከቦቹ ላይ የደረሰው ጥቃት የተሰማው ቢያንስ ሁለት ጥቃቶች መፈጸማቸውን የሚገልጹ ዘገባዎች ከወጡ በኋላ ነው።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ እንዲሁም ባለሥልጣናቱ በቀጣናው ወታደራዊ ድብደባ ስለ መፈጸሙ ባይናገሩም የአካባቢው መገናኛ ብዙኃን ግን ፍንዳታዎች መሰማታቸውን ዘግበዋል።

    የኢራን ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ቅዳሜ ምሽት በሆርሙዝ ወሽመጥ በምትገኘው ቄሸም ደሴት እና በጃስክ ወደብ በርካታ ፍንዳታዎች መሰማታቸውን ዘግበዋል።

    የፍንዳታዎቹ መንስኤ ምን እንደሆነ ወዲያውኑ ለማወቅ አልተቻለም። የአሜሪካ ጦር ኃይል የፈረንሳይ ዜና ወኪል የሆነው አሶሼትድ ፕሬስ ላቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።

    የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዓርብ ዕለት እንዳስታወቁት፣ የአሜሪካ ጦር ኃይል በኢራን ላይ አዲስ ውስን ወታደራዊ ጥቃቶችን ፈጽሟል። ጥቃቱ ያነጣጠረው በኢራን የአየር መከላከያ ሥርዓት ላይ እንደነበር ተገልጿል።

    ትራምፕ እርምጃውን “ውስን” ወታደራዊ እርምጃ ሲሉ ገልጸውታል። ሆኖም፣ ትራምፕ ጥቃቱን መፈጸሙን ቢያረጋግጡም የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ግን በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።

    ትራምፕ ለሳምንታት ያህል ከአጋማሽ ዘመን ምርጫ በኋላ አዲስ የጥቃት ማዕበል በኢራን ላይ ሊከፍቱ እንደሚችሉ ሲናገሩ ቆይተዋል። በዚህም ምክንያት መካከለኛው ምሥራቅና ሌሎች የዓለም ክፍሎች አሜሪካ ከሁለት ወራት ገደማ በኋላ በኢራን ላይ ሙሉ ወታደራዊ ዘመቻ ዳግም ትጀምር ይሆን በሚል ስጋት ውስጥ ቆይተዋል።

    ከስምንት ወራት በላይ የዘለቀው ጦርነት በዓለም ገበያዎች እና በዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ላይ ከፍተኛ መናወጥ አስከትሏል። ግጭቱን ለማስቆም የተደረጉ የዲፕሎማሲ ጥረቶችም መቆማቸው ተገልጿል።

    በጥቅምት ወር በሆርሙዝ ወሽመጥ በሚንቀሳቀሱ የንግድ መርከቦች ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጥቃት ተፈጽሟል።

  8. የሁቲ አማፂያን ሳዑዲ አረቢያ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 33 ሰዎች መገደላቸውን አስታወቁ

    በየመን ከሁቲ ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸው መገናኛ ብዙኃን ሳዑዲ አረቢያ በፈጸመችው የአየር ጥቃት እናቶች እና ሕፃናትን ጨምሮ ቢያንስ 33 ሰዎች መገደላቸውን ዘገቡ።

    በየመን ዓለም አቀፍ ዕውቅና ላለው መንግሥት ድጋፍ የሚያደርገው በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው ጥምር ኃይል እስካሁን ስለጥቃቱ አስተያየት አልሰጠም።

    በሁቲዎች የሚተዳደረው አል ማሲራ የቴሌቪዥን ጣቢያ በቀጥታ ባሰራጨው ምስል፣ ከዋና ከተማዋ ሰነዓ በስተምሥራቅ በምትገኘው አል-ሻሪያ ከተማ ውስጥ የሕይወት አድን ሠራተኞች ከፈራረሱ ሕንጻዎች ሥር አስከሬኖችን ሲያወጡ አሳይቷል።

    ከፍርስራሹ ውስጥ ከወጡት መካከል የታዳጊ ሕፃናት አስከሬኖችም ይገኝበታል

    የቴሌቪዥን ጣቢያው በተጨማሪም ቁስለኞች በቃሬዛ ተጭነው ወደ ሆስፒታል ሲወሰዱ የሚያሳዩ ምስሎችን አሰራጭቷል።

    በሁቲዎች የሚተዳደረው ሳባ የዜና ወኪል በበኩሉ፣ ጥቃቱ በሳዑዲ አረቢያ መፈጸሙን ገልጾ 39 ሰዎች መጎዳታቸውን ዘግቧል።

    ሳዑዲ አረቢያ በየመን ለሚገኘው እና ዓለም አቀፍ ዕውቅና ላለው መንግሥት ድጋፍ በመስጠት ከአስር ዓመታት በላይ ከሁቲዎች ጋር ስትዋጋ ቆይታለች።

    በየመን ለበርካታ ዓመታት ተዳፍኖ የቆየው ግጭት በኢራን ጦርነት ምክንያት በቅርቡ ዳግም ተቀስቅሷል።

    ሳዑዲ አረቢያ ሁቲዎች በሚቆጣጠሩት የሰነዓ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ሊያርፍ የነበረ የኢራን አውሮፕላንን ለማስቆም ጥቃት ከፈጸመች በኋላ፣ በየመን ተደርሶ የነበረው የተኩስ አቁም ስምምነት ፈርሷል።

    በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች በምላሹ በሳዑዲ አረቢያ የሚገኘውን የአብሃ አውሮፕላን ማረፊያ ዒላማ ያደረጉ ሲሆን፣ በኋላም በሆርሙዝ ወሽመጥ ፈንታ በየመን የባሕር ዳርቻ አካባቢ በቀይ ባሕር የነዳጅ ማጓጓዣ መስመርን ሲጠቀሙ በነበሩ የሳዑዲ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸም ጀምረዋል።

    ከዚያ በኋላ በየመን ውስጥ በሁቲዎች እና በሳዑዲ በሚደግፈው የየመንግሥት ኃይሎች መካከል ከባድ ውጊያዎች መካሄድ ጀምረዋል።

    አርብ ዕለት በታይዝ ግዛት በአንድ ገበያ ላይ በተፈጸመ ጥቃት 30 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።

    ሁቲዎች ጥቃቱን ሳዑዲ አረቢያ ፈጽማዋለች ቢሉም የመንግሥት ኃይሎች በበኩላቸው ሁቲዎች በስፍራው ላይ ሚሳዔል መተኮሳቸውን ተናግረዋል።

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩሉ ውጊያው ዳግም ከተጀመረ ወዲህ ከ1,600 በላይ ሰዎች መገደላቸውን እና ከ300,000 በላይ ሰዎች ደግሞ ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን ይፋ አድርጓል።

    ሳዑዲ አረቢያ የሁቲ ይዞታዎችን በተደጋጋሚ በአየር ስትደበድብ ሁቲዎችም በምላሹ በሳዑዲ ውስጥ በሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎችና የነዳጅ ተቋማት ላይ ሚሳዔሎችን ተኩሰዋል።

    በአል-ሻሪያ ከተማ ከደረሰው ጥቃት ከጥቂት ሰዓታት በፊት፣ በሳዑዲ የሚመራው ጥምር ኃይል ወደ ሪያድ ከተማ አቅጣጫ የተተኮሰን አንድ ሚሳይል ማክሸፉን አስታውቆ ነበር።

    የሁቲዎች ከፍተኛ መሪ መህዲ አል-ማሻት በየመን ላይ ለተፈጸሙት የቅርብ ጊዜ ጥቃቶች ቡድናቸው አጸፋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ዝተዋል።

    ተያያዥ ዜናዎች፡

  9. የእሁድ የጥቅምት 29/ 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ስርጭት ተጀምሯል

    የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች እንደምን አደራችሁ፤ የጥቅምት 29/ 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ስርጭታችን ተጀምሯል።

    የአገር ውስጥ እና የውጭ ዜናዎችን በአጭሩ እናቀርብላችኋለን። እንድትከታተሉን በአክብሮት እንጋብዛለን።

  10. የካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ ከቀዶ ሕክምና በኋላ የላቲን አሜሪካ ጉብኝታቸውን ሲጀምሩ “በጥሩ ጤንነት” ላይ መሆናቸውን ገለፁ

    የሮማ ካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ ወደ ላቲን አሜሪካ አብረዋቸው ለተጓዙ ጋዜጠኞች፣ ከሳንባ ካንሰር ቀዶ ሕክምና በኋላ ስለ ጤናቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ሲናገሩ “በጣም ጥሩ የጤና ሁኔታ ላይ ነኝ” አሉ።

    ሊቀ ጳጳሱ ቀዶ ሕክምናው ከተደረገላቸው ከሦስት ሳምንታት በኋላ የ12 ቀናት የላቲን አሜሪካ ጉብኝታቸውን ለመጀመር ኡራጓይ ደርሰዋል።

    የ71 ዓመቱ ሊቀ ጳጳስ ባለፈው ወር ባደረጉት መደበኛ የጤና ምርመራ ወቅት ዕጢ ከተገኘባቸው በኋላ ይህ ጉብኝት ሊሰረዝ ይችላል ተብሎ ቢገመትም፣ ጉዞውን ማድረግ በመቻላቸው “በጣም ደስተኛ” መሆናቸውን ገልፀዋል።

    ጉብኝቱ አርጀንቲናን እንዲሁም ሊቀ ጳጳሱ ለብዙ ዓመታት በሚሲዮናዊነት እና በኋላም በኤጲስ ቆጶስነት ያገለገሏት ፔሩን ያካትታል። ቫቲካን ጳጳሱ በፔሩ የሚያደርጉትን ጉብኝት “ወደ ቤታቸው እንደመመለስ ነው” ሲል ገልጿል።

    ሊቀ ጳጳሱ ወደ ኡራጓይ እየተጓዙ አውሮፕላን ውስጥ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፣ “እውነቱን ለመናገር፣ ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ምንም ጥርጣሬ አልነበረኝም፤ ይህ ጉዞ መቀጠል እንዳለበት እርግጠኛ ነበርኩ” ብለዋል።

    “ለአስደናቂው የሕክምና ቡድን ምስጋና ይግባውና... በጣም ጥሩ የጤና ሁኔታ ላይ እንደምገኝ አምናለሁ” ሲሉም ተናግረዋል።

    ባለፈው ወር ዕጢውን ለማስወገድ የተደረገው ቀዶ ሕክምና የተሳካ ሲሆን፣ ሐኪሞቻቸውም ካንሰሩ ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች እንዳልተስፋፋ ገልፀዋል።

    ሊቀ ጳጳሱ ዓርብ ዕለት ወደ ኡራጓይ ዋና ከተማ ሞንቴቪዲዮ ሲደርሱ፣ ብዙ ሰዎች የእርሳቸውን ስም እየጠሩ በደስታ ተቀብለዋቸዋል።

    • ተያያዥ ዜናዎች
  11. የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በጦርነቱ ዙሪያ ከ12 አገራት ጋር መነጋገራቸውን ገለፁ

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ፣ አሜሪካ እና እስራኤል ሊወስዷቸው በሚችሉ "ግጭት አባባሽ እርምጃዎች" እና ሊያስከትሏቸው በሚችሉ ውጤቶች ዙሪያ ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ ከ12 የተለያዩ አገራት አቻዎቻቸው ጋር በስልክ መነጋገራቸውን ገለፁ።

    አራግቺ በስልክ የተነጋገሩት ከኦማን፣ ከግብፅ፣ ከዮርዳኖስ፣ ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ ከኳታር፣ ከቆጵሮስ፣ ከቱርክ፣ ከኩዌት፣ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች፣ ከቱኒዚያ፣ ከኢራቅ እና ከፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር መሆኑን ተናግረዋል።

    ኳታር እና ፓኪስታን በአሁኑ ጊዜ በኢራን እና በአሜሪካ መካከል ያሉ ዋና አደራዳሪ አገራት ሲሆኑ፣ ኦማንም ከዚህ ቀደም ቴህራን እና በዋሽንግተንን የማደራደር ተመሳሳይ ሚና ተጫውታለች።

    አራግቺ በኢንስታግራም ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ “በእነዚህ ምክክሮች የኢስላማዊት ሪፓብሊክ ኢራንን መሠረታዊ አቋሞች አስረድቼ፣ የአገራትን ብሔራዊ ሉዓላዊነት ማክበር፣ ወረራና ዛቻን ማስቆም፣ ጎጂ የውጭ ጣልቃ ገብነቶችን ማስወገድ እንደሚገባ እንዲሁም በቀጣናው ያሉ አገራት የደኅንነት ችግሮች እንዳይስፋፉ ያለባቸውን ኃላፊነት በጉልህ አንስቻለሁ” ብለዋል።

    ከሰሞኑ በቴህራን እና በዋሽንግተን መካከል የቃላት ውጥረቶች ዳግም ከፍ እያሉ መምጣታቸውን ተከትሎ፣ የቀጣናው አገራት የሚያደርጓቸው ግንኙነቶች እንዲሁም ኢራን እና አሜሪካን ለማሸማገል የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረዋል።

    በኢራን እና በአሜሪካ መካከል የሚደረግ ድርድርን ከሚመሩ ዋነኛ አገራት አንዷ የሆነችው የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የአገራቸው አደራዳሪዎች ወታደራዊ ግጭቶች ዳግም እንዳይባባሱ ለማድረግ ባለፈው ሳምንት ብቻ አምስት ጊዜ ወደ ኢራን መጓዛቸውን በቅርቡ ገልፀዋል።

    እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ፣ በሁለቱ አገራት ባለሥልጣናት መካከል ከተደረጉት ስብሰባዎች አንዳንዶቹ ከ15 እስከ 20 ሰዓታት የሚደርስ ቆይታ የነበራቸው ናቸው።

  12. አሜሪካ ስለ ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ጥቆማ ለሚሰጡ እስከ 20 ሚሊዮን ዶላር እንደምትሸልም አስታወቀች

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስለ ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር መረጃ ለሚሰጡ ግለሰቦች እስከ 20 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት እንዳዘጋጀ አስታወቀ።

    ስለ ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ጣቢያዎች እንዲሁም ከኒውክሌር ጋር የተያያዘ ሥራ ስለሚያከናውኑ ባለሙያዎች እና በአጠቃላይ ስለ ቴክኖሎጂው መረጃ ለሚያቀብሉ ግለሰቦች ሽልማቱ ይሰጣል ተብሏል።

    የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ “ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ ለመገንባት የምታደርገውን ማንኛውንም ሙከራ ለማስቆም ቁርጠኛ ነን” ብሏል።

    ስለ ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር መረጃ ያላቸው አካላት ጥቆማ እንዲሰጡም አሳስቧል።

    የአሜሪካ መንግሥት የሚፈልገው መረጃ ከኢራን የኒውክሌር ማብላያ ተቋማት፣ ከሳይንቲስቶች እና ሌሎችም ከኒውክሌር መርሃ ግብር ጋር ትስስር ያላቸው አካላትን የሚመለከት መሆኑን አመልክቷል።

    በተጨማሪም የኒውክሌር መሣሪያ የሚያዘዋውሩ ባለሙያዎችን በተመለከተ ጥቆማ እንዲሰጠው ጠይቋል።

    ጥቆማ የሚያቀርቡ ሰዎች ከሚሰጣቸው የገንዘብ ሽልማት በተጨማሪ ወደ ሌላ አካባቢ እንዲዘዋወሩ እንደሚደረግ ገልጿል።

    አሜሪካ የገንዘብ ሽልማት ያዘጋጀችው የአገሪቱን ብሔራዊ ደኅንነት እና ፍላጎቶቿን ለማስጠበቅ መሆኑን አስታውቃለች።

    ጥቆማዎች በአገሪቱ አሠራር መሠረት እንደሚፈተሹም ተመልክቷል።

    ከዚህ በፊት ከኢራን የነዳጅ ሽያጭ፣ ከእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ እንዲሁም ከአገሪቱ የአየር ኃይል እና የሳይበር እንቅስቃሴዎች ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ለሚያቀብሉ ግለሰቦች ሽልማት እንደሚሰጥ ተገልጾ ነበር።

  13. በስፔን የባቡር አደጋ 69 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ የአውሮፓ ኅብረት የገንዘብ ምዝበራ ምርመራ ከፈተ

    ባለፈው ሳምንት በስፔን በደረሰ የባቡር መጋጨት አደጋ ሳቢያ 69 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ የአውሮፓ ኅብረት ዐቃቤ ሕግ የገንዘብ ምዝበራ ምርመራ ከፈተ።

    የአውሮፓ ኅብረት የስፔንን የባቡር ሐዲድ ለማዘመን የመደበው ገንዘብ ተመዝብሮ ሊሆን ይችላል በሚል በአገሪቱ የባቡር ትራንስፖርት ባለሥልጣናት ላይ ዐቃቤ ሕግ ምርመራ መጀመሩ ተገልጿል።

    የአውሮፓ ኅብረት ዐቃቤ ሕግ ከስፔን የሲቪል ደኅንነት ኃይል ጋር በመጣመር ምርመራውን ያካሂዳል ተብሏል።

    በማድሪድ-ስቬል የከፍተኛ ፍጥነት መስመር ላይ የተከሰተው የባቡር አደጋ በአውሮፓ የቅርብ ጊዜ ታሪክ የከፋው ነው።

    የአውሮፓ ኅብረት በዚህ ዓመት በስፔን የባቡር አገልግሎት ላይ ምርመራ ሲከፍት የአሁኑ ሁለተኛው ነው። ባለፈው ሳምንት አደጋ በደረሰበት መስመር ላይ ያለፈው ታኅሣሥ ወር በደረሰ ሌላ አደጋ 46 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።

    በዘጠኝ ወራት ልዩነት በተከሰቱት አደጋዎች በአጠቃላይ 115 ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

    የባለፈውን ሳምንት አደጋ ተከትሎ የስፔን የትራንስፖርት ሚኒስትር ኦስካር ፑንቴ ከሥልጣናቸው ለቅቀዋል።

    "እንደ ስፔን ባለች አገር፣ በአንድ ዓመት ውስጥ ሁለት ከባድ አደጋዎች ከተከሰቱ በኋላ የትራንስፖርት ሚኒስትር በሥልጣኑ መቀጠል አይችልም" ብለዋል።

    • ተያያዥ ዜናዎች
  14. በደቡብ ኢራን በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች አዲስ ጥቃት መፈጸሙ ተገለጸ

    ቃሽም ደሴትን ጨምሮ በደቡብ ኢራን በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች የሚሳዔል ጥቃት መፈጸሙን የቴህራን መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “የኢራንን የጦር አውሮፕላን መቃወሚያዎች አውድመናል” ብለዋል።

    “ኢራን አነስተኛ የጦር አውሮፕላን መቃወሚያ ገንብታ ነበር፤ አውድመነዋል” ብለዋል።

    የኢራን መገናኛ ብዙኃን ታስኒም እና ኢርና እንደዘገቡት ዛሬ ማለዳ በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል የተለያዩ ሥፍራዎች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል።

    ትራምፕ በበኩላቸው የኢራንን የጦር አውሮፕላን መቃወሚያ ማውደማቸውን ቢገልጹም ከቴህራን ጋር ውይይት እየተደረገ እንደሚገኝ እና የሆርሙዝ መወሽመጥ እንደሚከፈት ጠቁመዋል።

    በሌላ በኩል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ስለ ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር መረጃ ለሚሰጡ እስከ 20 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ሽልማት ማዘጋጀቱን ይፋ አድርጓል።

    ስለ ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ጣቢያዎች እንዲሁም ከኒውክሌር ጋር የተያያዘ ሥራ ስለሚያከናውኑ ሰዎች እና በአጠቃላይ ስለ ቴክኖሎጂው መረጃ ለሚሰጡ ግለሰቦች ሽልማቱ ይሰጣል ተብሏል።

    ትራምፕ “ኢራንን አሸንፈናል፤ ከኢራን ጋር ያሉ ነገሮች በጥሩ ሁኔታ እየሄዱ ነው። ከኢራን ጋር እየተነጋገርን ነው፤ ከዚህ በፊትም ተነጋግረናል” ብለዋል።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል የኢራን መገናኛ ብዙኃንን ጠቅሶ እንደዘገበው በቃሽም ደሴት የአሜሪካ ኤምኪው-9 ድሮን በቴህራን ጦር ተመትቶ ወድቋል።

  15. የጥቅምት 28/ 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ስርጭት ተጀምሯል

    የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች እንደምን አደራችሁ፤ የጥቅምት 28/ 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ስርጭታችን ተጀምሯል።

    የአገር ውስጥ እና የውጭ ዜናዎችን በአጭሩ እናቀርብላችኋለን። እንድትከታተሉን በአክብሮት እንጋብዛለን።

  16. በጋምቤላ ወረዳ ከምሽት አንድ ሰዓት በኋላ ነዋሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ ተከለከለ

    ከጋምቤላ ክልል ዋና ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው ጋምቤላ ወረዳ ከምሽት አንድ ሰዓት በኋላ ነዋሪዎች ከቤት ውጪ እንዳይንቀሳቀሱ ገደብ ተጣለ።

    ከዛሬ አርብ ጥቅምት27/2019 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገው ሰዓት እላፊ የተጣለው፣ ክልሉ ውስጥ እና ከውጭ የሚመጡ የጸጥታ ስጋቶችን አስቀድሞ ለመከላከል እንደሆነ የወረዳው ሰላም እና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኡጁሉ አኳይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    ይህ ገደብ እንዲጣል የወሰነው፣ የአኙዋ ብሔረሰብ ዞን መስከረም ላይ ያቋቋመው የወረዳው ጊዜያዊ አስተዳደር ነው።

    የወረዳው አስተዳደር በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መረጃ፣ “ከማታ 1፡00 ሰዓት አንስቶ እስከ ንጋት 12፡00 ሰዓት ድረስ ሕብረተሰቡ ከቤት ውጭ መንቀሳቀስ እንደማይችል” አስታውቋል።

    “ሕጋዊ ፈቃድ ካላቸው የጸጥታ አካላት ውጭ” ማንኛውም ግለሰብ የጦር መሣሪያ ይዞ የሚያደርገው እንቅስቃሴ “በጥብቅ የተከለከለ” እንዲሁም “ጥብቅ ክትትል” የሚደረግበት መሆኑን ገልጿል።

    እንደ ወረዳው ገለጻ፣ እነዚህ እገዳዎች የተጣሉት “የጸጥታ ማስከበር ሥራውን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ እና ቀጠናውን በፍጥነት ወደ መደበኛ ሰላም ለመመለስ” በማሰብ ነው።

    ለቢቢሲ ማብራሪያ የሰጡት የወረዳው ሰላም እና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኡጁሉ፤ በክልሉ ውስጥ የሚታየው የጸጥታ መደፍረስ ገደቡ እንዲጣል ምክንያት የሆነ አንድ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

    ከደቡብ ሱዳን ይነሳሉ ያሏቸውን ታጣቂዎች የሚያደርሱት ጉዳትም ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል። “እንደሚታወቀው በጋምቤላ የእርስ በእርስ ግጭት አለ። በዚያ መሠረት ድምበሩም ክፍት ስለሆነ ሾልከው የሚገቡ ታጣቂዎች አሉ።

    ወጣ ያሉ ቀበሌዎቻችን ላይ ጥቃት ያደርሳሉ” ብለዋል። በጥቅምት መጀመሪያ በአንድ ቀበሌ ላይ በደረሰ ጥቃት የአንድ ሰው ሕይወት አልፎ አራት ሰዎች መጎዳታቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

    ከትናንት ሐሙስ ዕለት አንስቶም ሌላ ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል የሚያመለክት እንቅስቃሴ መታየቱን ተናግረዋል።

    “ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት የመፍጠር አዝማመሪያዎች አሉ እርሱን ለመከላከል ነው” ሲሉ የተጣለው ሰዓት እላፊ ከዚህ ጋር የተያያዘ መሆኑን አብራርተዋል።

    ከወረዳው በ18 ኪሎ ሜትር ላይ በሚገኘው የክልሉ መዲና ጋምቤላ ከተማም በጥቅምት መጀመሪያ ላይ በተመሳሳይ ከ12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋት ድረስ የሰዎችና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ እንዳይደረግ ክልከላ ጥሎ ነበር።

    በዋና ከተማው እግዳ የተጣለው ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ነው። ቀጥሎ በከተማው በተፈጠረ ግጭት ምክንያት የክልሉ መንግሥት መስሪያ ቤቶች ተዘግተው ነበር።

  17. በዩናይትድ ኪንግደም የሥራ ማስታወቂያ የሚያወጡ ኩባንያዎች ደመወዙንም የመግለጽ ግዴታ ሊጣልባቸው ነው

    የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርንሀም የንግድ ድርጅቶች የሥራ ማስታወቂያ ሲያወጡ ደወወዙንም አያይዘው እንዲገልጹ አሳሰቡ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከሥራ ማስታወቂያ ጋር ደመወዝ አብሮ እንዲገለጽ የሚያስገድድ አዲስ ሕግ ከመውጣቱ በፊት ኩባንያዎች ይህንኑ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

    የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ከሥራ ማስታወቂያ ጋር የደመወዝ ዝርዝር በአስገዳጅነት አብሮ እንዲወጣ የማድረግ ውጥን ይዟል።

    ይህን ገቢራዊ የሚያደርግ ሕግ “በተቻለ ፍጥነት” ይቀርባል ተብሏል።

    ለውጡ ሥራ ፈላጊዎች በዋናነት ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የሥራ ማመልከቻ የሚያስገቡ ሠራተኞች የክፍያ አድልኦን ይከላከላል ተብሏል።

    ይሁን እንጂ የሰው ኃይል ማኅበር ደመወዝን ከሥራ ማስታወቂያ ጋር አብሮ ማውጣት ውስብስብ ሂደት እንደሆነ እና ደመወዝን ሁሌም መቆጣጠር የሚመች አይደለም ብሏል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የዩኬ የእኩልነት ተከታታይ ተቋም ሠራተኞች ባልደረቦቻቸው ምን ያህል እንደሚከበፈላቸው የማወቅ ሕጋዊ መብት ሊኖራቸው ይገባል ካለ በኋላ ነው።

    ጠቅላይ ሚኒስትር በርንሀም ደመወዝን ከሥራ ማስታወቂያዎች ጋር አብሮ ማውጣት የፆታ መካከል ያለውን የክፍያ ልዩነትም ያጠባል ሲሉ አክለዋል።

    ተመሳሳይ እርምጃ በአውሮፓ ሕብረትም እየቀረበ ነው።

  18. በኬንያ ለ191 ሰዎች ሞት ተጠያቂ የሆነው የአምልኮ ቡድን መሪ 200 ዓመት ተፈረደበት

    በኬንያ 190 ህጻናት እና አንድ አዋቂ ሰውን በመግደል የተወነጀለው የአምልኮ ቡድን መሪ ፖል ማኬንዚን የ200 ዓመት እስር ተፈረደበት።

    ማኬንዚ እና በመዝገቡ ውስጥ የተካተቱ ሌሎች 27 ተከሳሾች፣ የአምልኮ ቡድኑ አባላት ልጆቻቸው “ከኢየሱስ ጋር እንዲገናኙ” ለማድረግ በርሃብ እንዲገድሏቸው ትዕዛዝ በመስጠት ወንጀል ጥፋተኛ ተብለዋል።

    የ190 ህጻናትን የቀጠፈው ይህ ክስተት በኬንያ ከታዩ አሰቃቂ የሃይማኖታዊ ፅንፈኝነት ድርጊቶች አንዱ ሆኖ ተቆጥሯል።

    መዝገቡብ የተመለከቱት ዳኛ ዲያና ሞቻቼ፣ ተከታዮቹ እስኪሞቱ ድረስ እንዲጾሙ በማዘዝ “ዋነኛውን የወንጀል ተጠያቂነት” የሚሸከመው ማኬንዚ ላይ እንደሆነ ገልጸዋል።

    ዳኛዋ “እንዲህ አይነቶቹ ጭካኔዎች በሕግ የተደነገገውን ከፍተኛ ቅጣት እንደሚያስከትሉ ግልጽ መልዕክት ለማስተላለፍ ስለሚያስችል ቅጣቱ ትክክለኛ እና ፍትሐዊ ነው” ብለዋል።

    ራሱን ፓስተር ብሎ የሚጠራው ግለሰብ በቁጥጥር ስር የዋለው በአውሮፓውያኑ 2023 በአንድ ጫካ በተቆፈረ ጥልቀት የሌላው ጉድጓድ ውስጥ ከ400 በላይ አስከሬኖች ከተገኙ በኋላ ነበር።

    በኬንያ የባህር ዳርቻ አቅራቢያ በሚገኘው የሻካሆላ ጫካ ውስጥ ይህንን ያህል ቁጥር ያላቸው አስከሬኖች መገኘታቸው ኬንያውያንን ያስደነገጠ ሲሆን ዓለም አቀፍ ትኩረትንም ስቦ ነበር።

    በሞምባሳ ፍርድ ቤት የቀረበውን ክስ የመሠረቱት አቃቢያነ ሕግ፣ የወንጀሉን ክብደት ከግምት ውስጥ በማስገባት ማኬንዚ ላይ የሞት ፍርድ እንዲሰጥ ተከራክረዋል።

    በተጨማሪም ማኬንዚ ለፈጸማቸው ወንጀሎች ምንም አይነት የጸጸት ስሜት አለማሳየቱንም ጠቅሰዋል። ከአውሮፓውያኑ 1987 ወዲህ ኬንያ ውስጥ የሞት ቅጣት ተፈጻሚ ሆኖ አያውቅም።

    ሌሎቹ ተከሳሾቹ ላይ ደግሞ የዕድሜ ልክ እስራት እንዲፈረድ ጠይቀው ነበር።

    ማኬንዚ እና አብረውት የቀረቡት ተከሳሾች ፍርድ ቤቱ ምህረት እና የቅጣት ማቅለያ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

    ከሦስት ሳምንት ገደማ በፊት የጥፋተኝነት ውሳኔ ከተመተላለፉ አስቀድሞ፣ ሁሉም ተከሳሾቹ ጥፋተኛ እንዳልሆኑ በመግለጽ የተከራከሩ ሲሆን ማንም ሰው እንዲሞት አልተገደደም ብለዋል።

    ዳኛ ዲያና ሞቻቼ፣ የማኬንዚ ተከታዮች እርሱን “የኢየሱስ ልሳን” እንደሆነ ያምኑበት እንደነበር በወቅቱ ገልጸዋል። የማኬንዚን ትምህርት የተቃወሙ ሰዎች ተደብድበው እንዲሞቱ ይደረግ ነበር።

    የአምልኮ ቡድኑ ይንቀሳቀስበት በነበረው ጫካ ውስጥ የሚካሄዱ የቀብር ሥነ ሥርዓቶች “ሰርግ” ተብለው ይጠሩ የነበረ ሲሆን፣ የሞቱትም “ከኢየሱስ ጋር እንደተጋቡ ተደርገው” ይቆጠሩ እንደነበር ዳኛዋ አስረድተዋል።

    የድኅረ ሞት ምርመራ ውጤቶች እንደሚያሳዩት የአብዛኞቹ ተጎጂዎች ሞት ምክንኣት ርሃብ ነው። ሌሎች ደግሞ በአየር በመታፈን፣ በመታነቅ ወይም ጭንቅላት ላይ በደረሰ ከባድ ጉዳት የተነሳ ህይወታቸው አልፏል።

  19. የዴሞክራቶች ማሸነፍ በፈጠረው ድንጋጤ የተነሳ የኤአይ ኩባንያዎች ዋጋ በትሪሊዮኖች አሽቆለቆለ

    በአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ውጤትን ተከትሎ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ቴክኖሎጂ እድገትን ያቀዘቅዘዋል የሚል ስጋት በመፈጠሩ በዓለም አቀፍ የአክስዮን ገበያዎች ከፍተኛ የዋጋ ማሽቆልቆል ተመዘገበ።

    በአጋማሽ ዘመን ምርጫው፣ ዴሞክራቶች ኮንግረስን መቆጣጠራቸው ያሰጋቸው ባለሀብቶች በቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ውስጥ የነበሯቸውን አክስዮኖችን ሸጠዋል።

    በአሜሪካ የተጀመረው አክስዮኖችን በከፍተኛ መጠን የመሸጥ እንቅስቃሴ ወደ እስያ እና አውሮፓም ተስፋፍቷል። በዚህም የዋና ዋና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የአክስዮን ዋጋ ላይ በትሪሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር ማሽቆልቆል አጋጥሟል።

    የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች አክስዮኖችን አጠቃሎ የያዘው የናስዳክ ኢንዴክስ ሐሙስ ዕለት ዋጋው በ5.5 በመቶ ወድቋል።

    ይህ የዋጋ ማሽቆልቆል የተከሰተው፣ በዚህ ሳምንቱ የአሜሪካ አጋማሽ ዘመን ምርጫ ኮንግረስን የተቆጣጠሩት ዴሞክራቶች ኤአይን በተመለከተ ጠንካራ የቁጥጥር ሕጎችን ሊያወጡ ይችላሉ የሚል ስጋት በመፈጠሩ ነው። ዴሞክራቶቹ እጩዎች ለቴክኖሎጂው የሚያስፈልጉ የዳታ ማዕከላትን መስፋፋታቸውን ሲቃወሙ ቆይተዋል።

    በተጨማሪም የአክስዮን ዋጋ ቅናሹ የተፈጠረው ግዙፍ ወጪዎች የሚደረግባቸው የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኩባንያዎች ትርፋማ የመሆናቸው ጉዳይ ላይም ስጋት በመቀስቀሱ ነው

    በአሜሪካ የተመዘገበው የአክስዮን ሽያጭ ማዕበል፣ አፕልን፣ ኤንቪዲያን እና ቴስላን ጨምሮ ‘ሰባቱ ድንቆች’ በሚል የሚጠሩት ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በአንድ ቀን ውስጥ ዋጋቸው በአንድ ትሪሊዮን ዶላር እንዲቀንስ አድርጓል። የኤንቪዲያ አክስዮን ብቻ ከዘጠኝ በመቶ በላይ አሽቆልቁሏል።

    የኤሎን መስክ ኩባንያዎች የሆኑት ስፔስ ኤክስ እና የኤሌክትሪክ መኪና አምራቹ ቴስላ አክስዮኖችም በስምንት በመቶ እና በ11 በመቶ ገደማ ዋጋቸው ቀንሷል። ይህ ቅናሽ ከኩባንያዎቹ የገበያ ዋጋ ላይ ከ300 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንዲቀነስ ምክንያት ሆኗል።

    መስክ በአጋማሽ ምርጫው በእጩነት የቀረቡት ሪፐብሊካኖች እንዲመረጡ 450 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ገንዘብ አውጥቷል። ለቴክሳስ የሴኔት አባልነት የቀረቡትን ሪፐብሊካኑ ኬን ፓክስተን የምርጫ ቅስቀሳ ለመደገፍ ብቻ ቢያንስ 45 ሚሊዮን ዶላር ሰጥቷል። ይሁን እንጂ ማክሰኞ ዕለት በተደረገው ምርጫ ከ38 ዓመት በኋላ ቴክሳስ ውስጥ ዲሞክራት የሴኔት ተወካይ ተመርጧል።

  20. ታንዛኒያዊው ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ግጭት በማነሳሳት ወንጀል ጥፋተኛ ተባሉ

    የታንዛኒያ ዋነኛ ተፎካካሪ ፖለቲከኛ ቱንዱ ሊሱ በምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር የፖለቲካ ነፃነት ላይ ስጋት በሳደረ ግጭት የማነሳሳት ወንጀል አራት ዓመት ተፈረደባቸው።

    የዳሬ ሰላም ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሦስት ዳኞች ችሎት ፖለቲከኛው የቀረበባቸውን ብርቱ የአገር ክህደት ክስ አቃቢ ሕግ በቂ ማስረጃ ባለማቅረቡ ነፃ ብሏቸዋል።

    ይሁን እንጂ ካለፈው ዓመት ሚያዚያ ጀምሮ በቁጥጥር ስር የሚገኙት የ58 ዓመቱ ፖለቲከኛ ደጋፊዎቻቸው የ2025ቱን ጠቅላላ ምርጫ እንዲረብሹ አበረታትተዋል ተብለዋል።

    ‘ቻደማ’ የተባለውን ተቀናቃኝ ፓርቲ የሚመሩት ሊሱ ክሱን ውድቅ አድርገው ውንጀላውን ፖለቲካዊ ግፊት ያለበት ነው ብለዋል።

    ፍርድ ቤቱ “ማሻሻያ ከሌለ፤ ምርጫ የለም” የሚለው የምርጫ ዘመቻቸው ግጭት በማነሳሳት ለቀረበባቸው ክስ በቂ ማስረጃ ነው ብሏል።

    ሊሱ በአገር ክህደት ወንጀል እንጂ ግጭት በማነሳሳት እንዳልተከሰሱ ተናግረዋል።

    “ግጭት የማነሳሳት ክስ እናንተ የተከበራችሁ ዳኞች የፈጠራችሁት ነው። ያልነበረ ክስ ፈጥራችኋል። እናም ይህንም በፖለቲካዊ ትዕዛዝ ነው ያደረጋችሁት” ብለዋል ሊሱ ለፍርድ ቤቱ።

    ፖለቲከኛው የአገር ክህደት ወንጀል ባለመከሰሳቸው እና ግጭት በማነሳሳት በመሆኑ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር እንደሚጠይቁ ተናግረዋል።

    ፖለቲከኛው በቀጣይ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ፍርዱን ይግባኝ ማለት ይችላሉ።

    የአገር ክህደት ወንጀል በታንዛኒያ እጅግ ከባድ ከሚባሉ ወንጀሎች ውስጥ አንዱ ሲሆን እስከ ሞትም የሚያስቀጣ ነው።

    ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉህ ሀሰን የ2025ቱን ምርጫ 98 በመቶ ድምፅ በማግኘት አሸንፈዋል።

    ይሁን እንጂ ሊሱን ጨምሮ ሁለት ዋነኛ ተቃናቃኞቻቸው ከምርጫው ውጭ ነበሩ።