የሱዳን መንግሥት በገዳሪፍ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ቆንስላ ዘጋ
የሱዳን መንግሥት በገዳሪፍ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ቆንስላ መዝጋቱን እና ዲፕሎማቶቹን ማስወጣቱን ሮይተርስ የዜና ወኪል ሁለት ምንጮችን ጠቅሶ ዘገበ።
ሱዳን ይህንን እርምጃ የወሰደችው ኢትዮጵያ ስድስት የሱዳን ዲፕሎማቶች በ48 ሰዓታት ውስጥ አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ መስጠቷን ተከትሎ ነው።
ምንጮች ጉዳዩ ስስ ዲፕሎማሲያዊ ጉዳይ ስለሆነ በሚል ስማቸው እንዳይገለጽ መጠየቃቸውን ሮይተርስ በዘገባው ላይ ጠቅሷል።
ኢትዮጵያ ከሱዳን ጦር ጋር እየተፋለመ የሚገኘውን ፈጥኖ ደራሽ ኃይልን (አርኤስኤፍ) በመደገፍ በሱዳን የምትከሰስ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በበኩሏ በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል የሚገኙ አማጺያንን በመደገፍ ሱዳንን ትወነጅላለች።
ሆኖም ሁለቱም ወገኖች የሚቀርብባቸውን ክሶች ያስተባብላሉ።
የፈረንሳይ የዜና ወኪል አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ አንድ የሱዳን ባለሥልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እሁድ ዕለት የሱዳንን አምባሳደር ጠርተው ቆንስላው እንደሚዘጋ አሳውቀዋል።
በዚህም የሱዳን ቆንስላ ሠራተኞች ማክሰኞ ምሽት ከስፍራው መውጣታቸውን ባለሥልጣኑ ገልጸዋል።
የኤኤፍፒ ምንጭም የዲፕሎማሲ ውዝግቡን ማባባስ አልፈልግም በማለት ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠይቀዋል።
በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ ኢትዮጵያ በኤርትራ መዲና አሥመራ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ለመዝጋት መወሰኗን እና 10 የኤርትራ ዲፕሎማቶች ከአገሪቱ እንዲወጡ ትዕዛዝ መስጠቷን ተከትሎ፤ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉንም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች አቋርጣለች።
ኢትዮጵያ ይህንን እርምጃ የወሰደችው ኤርትራ "ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ" በሆነ መንገድ ለምትፈፅመው "የጠብ ጫሪነት እና የትንኮሳ" ድርጊቶች ምላሽ ለመስጠት እንደሆነ ተገልጿል።
የኤርትራ ኤምባሲ ይህንን ተከትሎ ኢትዮጵያ "እነዚህን ያልተገቡ የጠብ አጫሪነት ድርጊቶች ምክንያታዊ ለማድረግ ኤርትራን ከስሳለች" ብሏል።
ኢትዮጵያ ከዚህ በተጨማሪ አንድ የግብጽ ዲፕሎማትንም ከአገሯ አስወጥታለች።
የሱዳን እና ኢትዮጵያ ግንኙነት እየሻከረ መምጣቱ በየአገራቱ የሚካሄደውን ጦርነት ሊስፋፋ እንዲሁም ወደ ቀጣናው ሊዛመት ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።
የሱዳን የሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት የፖለቲካና የውጭ ጉዳይ አማካሪ የሆኑት አምጃድ ፋሪድ ለሮይተርስ የሱዳን መንግሥት የግዛቱን አንድነትና ደኅንነት ለመጠበቅ ቁርጠኛ ቢሆንም፣ ከኢትዮጵያ ጋር ግልጽ ወደሆነ ጦርነት እንዳይገባ የሚቻለውን ሁሉ ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል።
እሑድ ዕለት የሱዳን መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት እና ለአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤት አቤቱታ ማቅረቡን አስታውቋል።
ሱዳን፣ ኢትዮጵያ የፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) በሱዳን መሠረተ ልማቶች ላይ ለሚፈፅማቸው የድሮን ጥቃቶች መነሻ ግዛቷን እንዲጠቀም ፈቅዳለች ስትል ትከስሳለች።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ የሱዳን ዲፕሎማቶችን ማባረሯን በተመለከተ ሮይተርስ የዜና ወኪል ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ቃል አቀባይ አስተያየት መጠየቁን የገለጸ ሲሆን ወዲያውኑ ምላሽ አልሰጡም።
ቢቢሲም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አስተያየት የጠየቀ ሲሆን ወዲያውኑ ምላሽ አላገኘም።
ተያያዥ ዜናዎች፡