ቀጥታ , ሶሪያ ወታደሮቿን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመላክ እየተዘጋጀች ነው

ሶሪያ ወታደሮቿን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመላክ እና በድንበር አካባቢ በማሰማራት በየመን ካሉ የሁቲ አማፂያን ጋር በምታደርገው ውጊያ ድጋፍ ለመስጠት መስማማቷን ዕቅዱን በቅርበት የሚያውቁ ሦስት ባለሥልጣናት ለአሶሼትድ ፕሬስ ተናገሩ። አንድ የቀጣናው ባለሥልጣን እና ሁለት የሶሪያ ባለሥልጣናት እንዳሉት የሶሪያ ወታደራዊ አማካሪዎች አስቀድመው ወደ ሳዑዲ አረቢያ አቅንተዋል። በጉዳዩ ላይ ለመናገር ፍቃድ እንዳልተሰጣቸው የተናገሩት እነዚህ ባለሥልጣናት ሥማቸው አንዳይገለጽ ጠይቀው እስካሁን ምንም ተዋጊ ኃይል ወደ የመን አልተላከም ብለዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በፖላንድ ስድስት ሰዎችን ገድሏል የተባለው ተጠርጣሪ በሆስፒታል ውስጥ ሕይወቱ አለፈ

    የፖላንድ ሁለተኛዋ ከተማ በሆነችው ክራኮው ስድስት ሰዎችን በመግደል የተጠረጠረው ግለሰብ በሆስፒታል ውስጥ ሕይወቱ አለፈ።

    በክራኮው ጽንፈኛ የፖለቲካ አመለካከት እንዳለው በሚጠረጠር በዚህ ግለሰብ በተፈጸመ ጥቃት 6 ሰዎችን ሲገደሉ 16 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ተገልጿል።

    ከተገደሉት መካከል አራት ሴቶች እና ሁለት ወንዶች ይገኙበታል። ሦስቱ የፖላንድ ዜጎች ሲሆኑ፣ አንዱ የብሪታንያ ዜጋ ነው ተብሏል።

    ከ16ቱ ቁስለኞች መካከል ሁለት ፖሊሶች እና ከኦስትሪያ፣ ጀርመን፣ ፖርቹጋል፣ ሩሲያ እና ብሪታንያ የመጡ የውጭ ዜጎች ይገኙበታል። ከፖሊሶቹ አንዱ ከባድ ጉዳት እንደደረሰበት ተገልጿል።

    የ24 ዓመት ዕድሜ ያለው ፖላንዳዊው ተጠርጣሪ ከፖሊስ ጋር የተኩስ ልውውጥ ካደረገ ቆስሎ ተይዞ ወደ ሆስፒታል የተወሰደ ቢሆንም ሕይወቱ ግን እዚያው አልፏል።

    የአገሪቱ ባለሥልጣናት ግለሰቡ ስለሞተበት ምክንያት ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ባይሰጡም፣ በግድያዎቹ ላይ የተጀመረው ምርመራ እንደቀጠለ መሆኑን አረጋግጠዋል።

    በተኩስ ጥቃቱ ስድስት ሰዎች ሲገደሉ፣ በርካታ ሌሎች ደግሞ ቆስለዋል። ጥቃቱም ባለሥልጣናት የአደጋውን መነሻ ለማወቅ ሰፊ የጸጥታ ዘመቻ እንዲያካሂዱ አስገድዷል። የፖላንድ ባለሥልጣናት ክስተቱን በቅርብ ዓመታት ከታዩት በከባድ የጦር መሣሪያ ከታገዙ ጥቃቶች ሁሉ ከባዱ በማለት ገልጸውታል።

    መርማሪዎች በወንጀል ቦታውና ከተጠርጣሪው ጋር ተያይዘው በተለያዩ ቦታዎች የተሰበሰቡ ማስረጃዎችን መመርመራቸውን ቀጥለዋል።

    ዓቃቤ ሕግ ቢሮም ተጠርጣሪው ድርጊቱን ብቻውን ፈጽሟል ወይስ ሌሎች ተባባሪዎች ነበሩት የሚለውን እንዲሁም ወደ ጥቃቱ ያደረሱትን ምክንያቶች ለማጣራት እየሠራ ነው።

    የአገሪቱ የፖለቲካ መሪዎችና የማኅበረሰብ አባላት ለሟቾች ቤተሰቦች የሐዘን መልዕክት በመላክ ለተጎጂዎች ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

    ተያያዥ ዜናዎች፡

  2. ከኢራን ጋር የሚደረገው ድርድር እንቅፋት በገጠመበት ወቅት ትራምፕ ከኳታሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በዝግ ሊነጋገሩ ነው

    የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ከኳታሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሐመድ ቢን አብዱልራህማን አል ታኒ ጋር በዋሽንግተን በዝግ ሊነጋገሩ እንደሆነ ዋይት ሐውስ አስታወቀ።

    ትራምፕ የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም በመሆን እያገለገሉ ካሉት ሼክ ሞሐመድ ቢን አብዱልራህማን አል ታኒ ጋር ዛሬ ሰኞ በዝግ እንደሚነጋገሩ አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣንን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።

    እንደ ባለሥልጣኑ ከሆነ የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚደንት ጄዲ ቫንስም ከኳታሩ መሪ ጋር ይገናኛሉ።

    መሪዎቹ ውይይቱን የሚያካሂዱት ከኢራን ጋር የሚደረገውን ጦርነት ለመቋጨት የሚደረገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንቅፋት በገጠመው ወቅት ነው።

    ዋይት ሐውስ መሪዎቹ የሚወያዩባቸው አጀንዳዎች ምን እንደሆኑ አልጠቀሰም። ውይይቱ ቀድሞ ከተገለጸው የጉዞ እገዳ ጋር የተያያዘም አይመስልም።

    ኳታር ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በቴህራን እና በዋሽንግተን መካከል ዋነኛ አደራዳሪ ሆናለች።

    የስምምነት እቅዶችን በማስተላለፍ እና በኢራን የኑክሌር ፕሮግራም ላይ ያሉ ልዩነቶችን ለመፍታት እና ግጭቱን ለማቆም እንደ ድልድይ በመሆን እያገለገለች ነው።

    የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እሁድ ዕለት ከኢራን ጋር የሚደረገው ድርድር "ትንሽ ለውጥ" እንዳሳየ ገልጸዋል።

    ሩቢዮ በፓሪስ ለሚካሄደው የቡድን ሰባት አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ለማቅናት ከፍሎሪዳ ሲነሱ "ትራምፕ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ እንደሚመርጡ" ተናግረዋል።

    ሆኖም ኢራን "ተቀባይነት የሌለው" እና በአንዳንድ ሁኔታዎች "አስቂኝ እና የሚያስቆጡ እንዲሁም ተጨባጭ ያልሆኑ ፍላጎቶች" አሏት ብለዋል።

    ተያያዥ ዜና፡

  3. ትራምፕ ድርድሩ እስከቀጠለ ድረስ በኢራን ላይ አዲስ ጥቃት የማዘዝ ዕድሉ እጅግ ዝቅተኛ ነው አሉ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚደረገው ድርድር እስከ ቀጠለ ድረስ አዲስ ጥቃት እዲፈጸም የማዘዝ ዕድላቸው አነስተኛ መሆኑን ተናገሩ።

    ትራምፕ እሁድ ዕለት እንደተናገሩት፣ ግጭቱን ለማስቆም የሚደረገው ውይይት መሻሻል እያሳየ ከሆነ በኢራን ላይ አዲስ ወታደራዊ ጥቃቶችን የማዘዝ ዕድላቸው “እጅግ ዝቅተኛ” መሆኑን ገልጸዋል።

    ትራምፕ ለሲኤንኤን በስልክ በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ “ጉዳዩ በጣም ጠንካራ ስምምነት ይፈርሙ አይፈርሙ በሚለው ላይ የተመሠረተ ነው። መልሱ ግን ያ አስፈላጊ የሚሆንበት ዕድል እጅግ ዝቅተኛ ነው” ብለዋል።

    ሲኤንኤን ትራምፕን በትክክል ምን እንደጠየቀ ባይገልጽም፣ ፕሬዚዳንቱ ጥቃቶች እንደገና ከተጀመሩ አሜሪካ ልትመታቸው የምትችላቸውን የመሠረተ ልማት ዒላማዎች አስቀድማ ለይታለች ብለዋል። "38 ድልድዮችን ጨምሮ በአንድ ሰዓት ውስጥ ልናፈርሳቸው እንችላለን” ሲሉም ተናግረዋል።

    በኋላ በትሩዝ ሶሻል የማኅበራዊ ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ “አይረን ጌት የተባለው ግብረ ኃይል” በኢራን ላይ ሙሉ በሙሉ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።

    ሮይተርስ ዘመቻው ኢራን የጦር መሣሪያና ሌሎች ማዕቀብ የተጣለባቸውን ቁሳቁሶችን በየብስ ድንበሮቿ እና በካስፒያን ባሕር በኩል እንዳታጓጉዝ ለማገድ ያለመ ነው።

    ትራምፕ ከአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ በኋላ በሰጡት ቃለ ምልልስ የኢራን ጦርነት ሪፐብሊካኖች በምርጫው እንዲሸነፉ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ነው ሲሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ ግን “የተሸነፍንበት ምክንያት ጦርነቱ ነው” በማለት ግልጽ አቋም ወስደዋል።

    ትራምፕ እሁድ ዕለት ለጋዜጠኞች “ብዙ ሰዎች ቫንስ ስለ ኢራን የሰጡትን አስተያየት አልወደዱትም” ብለዋል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በበኩላቸው፣ በጦርነቱና በምርጫ ውጤቱ መካከል ግንኙነት ስለመኖሩ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

    ሩቢዮ “መናገር የምችለው አንድ ነገር ቢኖር፣ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለረዥም ጊዜ የነበረን እውነተኛ ስጋት ለይተው ተገቢውን እርምጃ ወስደዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

    ጦርነቱን ለማስቆም እየተገደረጉ ስላሉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች በተመለከተም፣ ወዲያውኑ መፍትሄ ይገኛል ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል።

    “ፕሬዚዳንቱ ሁልጊዜ ይህንና ሌሎች ችግሮችን በዲፕሎማሲ መፍታትን ይመርጣሉ። አንዳንድ ጊዜ ግን ይህ አይቻልም። ዕድሉ ካለ እንመረምረዋለን። ነገር ግን እስካሁን ሂደቱ ፍሬያማ አልሆነም፤ ምክንያቱም የኢራን ጥያቄዎች ተቀባይነት የሌላቸው ብቻ ሳይሆኑ፣ በአንዳንድ ሁኔታዎች የተጋነኑ፣ የማይጨበጡ እና ከእውነታው የራቁ ናቸው” ብለዋል።

    ትራምፕ ምርጫው ካለፈ በኋላ በኢራን ላይ ሰፊ ጥቃት እንደሚጀምሩ ፍንጭ ሲሰጡ ቢቆዩም፣ እስካሁን ትልቅ የአሜሪካ ወታደራዊ ዘመቻ የሚጀመረበት ምልክት አልታየም።

    ኢራን በበኩሏ ውጊያው ከቀጠለ በአሜሪካ እና በእስራኤል ዒላማዎች ላይ ጥቃት እንደምትፈጽም አስጠንቅቃለች።

    በተጨማሪም፣የኢራን ሚዲያዎች ቅዳሜ በደቡባዊ ኢራን የተሰሙት ፍንዳታዎች ከአሜሪካ ጥቃት ሳይሆን ከኢራን ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ጋር የተያያዙ እንደነበሩ ዘግበዋል።

    ተያያዥ ዜናዎች፡

  4. ኢራቅ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ነዳጅ ለመላክ ከአሜሪካ ጋር ተስማማች

    የኢራቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፉአድ ሁሴን አገራቸው በኦማን አቅራቢያ በሚገኘው የሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ነዳጅ መላኳን እንድትቀጥል ከአሜሪካ ጋር መስማማቷን ገለጹ።

    ሁሴን እንደተናገሩት በኢራን ጦርነት የተነሳ ነዳጅ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ላይ በተፈጠሩ መስተጓጎሎች የተነሳ ኢራቅ 60 ቢሊዮን ዶላር ከስራለች።

    ኢራቅ ለውጭ ገበያ የምታቀርበው ነዳጅ በጥቅምት ወር መሻሻል ማሳየቱንም ሚኒስትሩ ጨምረው ገልጸዋል።

    የኢራቅ የኢነርጂ ዘርፍ ኃላፊዎች እንዳሉት በመስከረም ወር አገሪቱ በቀን ትልክ ከነበረው 2.65 ሚሊዮን በርሜል በጥቅምት ወር ወደ 3.5 ሚሊዮን በርሜል አድጓል።

    ሚኒስትሩ በተጨማሪም የአሜሪካ ገንዘብ ሚኒስቴር በቴህራን ላይ የሚደረገውን የኢኮኖሚ ጫና ለማሳደግ ኢራቅ ከኢራን ጋር ያላትን ሁሉንም የድንበር መሻገሪያዎች እንድትዘጋ ተጠይቃለች ብለዋል።

    ሁለት ክፍት ሆነው እንዲቆዩ ከተፈቀደላቸው የድንበር መሻገሪያዎች አንዱ በኩርዲስታን ክልል የሚገኝ መሆኑንም ገልጸዋል።

    ተያያዥ ዘገባዎች፡

  5. ሶሪያ ወታደሮቿን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመላክ እየተዘጋጀች ነው

    ሶሪያ ወታደሮቿን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመላክ እና በየመን ድንበር አካባቢ በማሰማራት አገሪቱ ከሁቲ አማፂያን ጋር በምታደርገው ውጊያ ድጋፍ ለመስጠት መስማማቷን ዕቅዱን በቅርበት የሚያውቁ ሦስት ባለሥልጣናት ለአሶሼትድ ፕሬስ ተናገሩ።

    የፈረንሳይ የዜና ወኪል አንድ የቀጣናው ባለሥልጣን እና ሁለት የሶሪያ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው የሶሪያ ወታደራዊ አማካሪዎች አስቀድመው ወደ ሳዑዲ አረቢያ አቅንተዋል።

    በጉዳዩ ላይ ለመናገር ፍቃድ እንዳልተሰጣቸው የተናገሩት እነዚህ ባለሥልጣናት ሥማቸው እንዳይገለጽ ጠይቀው እስካሁን ምንም ተዋጊ ኃይል ወደ የመን አልተላከም ብለዋል።

    የሳዑዲ አረቢያ ባለሥልጣናት በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

    በየመን ውስጥ በሁቲ አማፅያንና በሳዑዲ በሚደገፉት የመንግሥት ኃይሎች መካከል እየተደረገ ያለው ውጊያ ተባብሶ ቀጥሏል።

    ሁቲዎች በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በቀጥታ ጥቃቶችን መፈጸማቸውም ተዘግቧል።

    በሳዑዲ እና በሁቲ አማፂያን መካከል ያለው ግጭት የተስፋፋው አሜሪካና እስራኤል ባለፈው ዓመት የካቲት ወር በኢራን ላይ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ነው።

    ሶሪያ በረዥም የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የተፈተኑ ተዋጊዎች ቢኖሯትም፣ እስካሁን በቀጣናው የተስፋፋውን ግጭት ከሩቅ ስትከታተል ቆይታለች።

    ሳዑዲ አረቢያ በአሜሪካ የተሰጧት ዘመናዊ የውጊያ አውሮፕላኖች እና የሚሳዔል መከላከያ ሥርዓቶች ቢኖሯትም ሁቲዎችን ማሸነፍ ግን አልቻለችም።

    ከሳዑዲ አረቢያ አጋሮች ብዙዎቹ በሁቲዎች ላይ በምታደርገው ጦርነት የእግረኛ ጦር ለማሰማራት ፈቃደኛ ባይሆኑም፣ የሶሪያ መንግሥት ከአገሪቱ ጋር ያለው ግንኙነት የተለየ መሆኑ ይጠቀሳል።

    ሳዑዲ አረቢያ በሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ለተለያዩ የተቃዋሚ ኃይሎች የገንዘብ ድጋፍ ታደርግ የነበረ ሲሆን፣ ከጦርነቱ በኋላ ለሚደረገው የሶሪያ መልሶ ግንባታም አገሪቱ በእጅጉ የምትፈልገውን የገንዘብ ድጋፍ እንደምትሰጥ ቃል መግባቷ ተነግሯል።

    አንድ የሶሪያ ባለሥልጣን እንደገለጹት፣ በመጀመሪያ ዙር 600 የሚጠጉ የሶሪያ ልዩ ኃይል ተዋጊዎች በመጪው ሳምንት ወደ ሳዑዲ አረቢያ እንደሚንቀሳቀሱ ይጠበቃል።

    ባለሥልጣኑ አክለውም ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሚላኩት ተዋጊዎች የሶሪያ ዜጎች ብቻ እንዲሆኑ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።

    በሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ወደ አገሪቱ በመምጣት የተለያዩ አማፂ ቡድኖችን የተቀላቀሉ የውጭ ተዋጊዎች እንዳይካተቱም አጽንዖት ተሰጥቷል።

    በተጨማሪም፣ በ82ኛው ክፍለ ጦር አዛዥ ካሊድ ኻጣብ የተመራ የሶሪያ ልዑክ በቅርቡ ለሁለት ሳምንታት ወደ ሳዑዲ አረቢያ ጉብኝት ማድረጉን ገልጸዋል።

    ሁለተኛ የሶሪያ ባለሥልጣን በበኩላቸው፣ 36 የሶሪያ ወታደራዊ ኃላፊዎች በጂዳ የሚገኝን በሳዑዲና በየመን ባለሥልጣናት የሚተዳደር የጦር ዕዝና የኦፕሬሽን ማዕከል መጎብኘታቸውን ተናግረዋል። በዚያም ስለ ተለያዩ የውጊያ ግንባሮችና የኦፕሬሽን ቦታዎች ማብራሪያ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።

    በውይይቶቹ ላይ እውቀት ያለው አንድ የክልሉ ባለሥልጣን ደግሞ፣ ሶሪያ አስቀድማ “አነስተኛ ቁጥር” ያላቸው ወታደራዊ አማካሪዎችን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ማሰማራቷን ገልጸዋል። እነዚህ አማካሪዎች በሳዑዲ ውስጥ የሚገኙ የየመን ኃይሎችን በማሰልጠን ላይ እንደሚሳተፉም ተነግሯል።

    ተጨማሪ ዘገባዎች፡

  6. የሰኞ የጥቅምት 30/ 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ስርጭት ተጀምሯል

    የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች እንደምን አደራችሁ፤ የጥቅምት 30/ 2019 ዓ. ም. የቀጥታ ስርጭታችን ተጀምሯል።

    የአገር ውስጥ እና የውጭ ዜናዎችን በአጭሩ እናቀርብላችኋለን። እንድትከታተሉን በአክብሮት እንጋብዛለን።