በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ 'ፖለቲካዊ ግጭቶች' ለምን ጨመሩ?

የፎቶው ባለመብት, AFP
ያለፉት ጥቂት ዓመታት የኢትዮጵያን መረጋጋት ያናወጡ በርካታ ውስጣዊ ግጭቶች የሚታዩባቸው ጊዜያት ሆነዋል።
በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች በሚከሰቱ የብሄር ግጭቶች እንዲሁም የመንግሥት ኃይሎች በተለያዩ አካባቢዎች ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች በሚያደርጋቸው ውጊያዎች ምክንያት ደግሞ በርካታ ሰዎች ለሞት እና መፈናቀል የተጋለጡ ሆነዋል።
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ግጭቱ የቀጠለ ሲሆን፣ ይህም ኢትዮጵያ እንደገና የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ልትገባ ትችላለች የሚል ስጋት ፈጥሯል።
አብዛኛው ጥቃት የተፈጸመባቸው ክልሎች ደግሞ አማራ፣ ትግራይ እና ኦሮሚያ መሆናቸውን የአክሌድ መረጃ ያሳያል።
ባለፉት ስምንት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭት የተለመደ ክስተት መሆኑን የሚናገሩት ቢቢሲ ያነጋገራቸው የቀጠናው የሕግ እና የፖለቲካ ምሁራን፣ ለግጭቶቹ መስፋፋት መንግሥት ኃላፊነቱ አለመወጣቱ ነው ሲሉ ወቅሰዋል።
በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች የተከሰቱ ጥቃቶችን እየመረመመረ መሆኑን የሚገልጸው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በአገሪቱ "በአንፃራዊነት ጥቃቶች መቀነሳቸውን" ገልጿል።
'ግጭትን መሠረት ያደረገ ፖለቲካል ኢኮኖሚ'
የሕግ እንዲሁም የሰላም ግንባታ እና የግጭት አፈታት ባለሙያ የሆኑት ጌታቸው ገብረኪሮስ ተማረ በኢትዮጵያ ውስጥ ግጭት "የፖለቲካ ማስፈጸሚያ መሣሪያ ሆኗል" የሚል እምነት አላቸው።
መንግሥትም ሆነ ታጣቂ ኃይሎች "በውይይት የሚፈታ ችግር የለም" የሚል እምነት መያዛቸው በአገሪቱ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፉ ግጭቶች መብዛታቸውን ያስረዳሉ።
"የፌደራል መንግሥቱም ወይም የክልላዊ መንግሥቱም ጦርነት እንደ አንድ የፖለቲካ ማስፈጸሚያ መንገድ ነው የሚጠቀሙበት" ያሉት አቶ ጌታቸው "ሌሎች ተቃራኒ ኃይሎችም በዛው ልክ ቁጭ ብለን ተወያይተን የምንፈታው ችግር የለም ስለዚህ መብቶቻችን መሆን የፍላጎቶቻችን በጦርነት ማስፈጸም ያለብን ወደሚል ነገር ውስጥ [ገቡ]" ሲሉ ተናግረዋል።
በቅርቡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሰባት አማጺ ቡድኖች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ከሥልጣን የማውረድ ግብ ይዘው ጥምረት መፍጠራቸው ይታወቃል።
በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ድጋሚ ጦርነት መቀስቀሱ ከተሰማ በኋላ ደግሞ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች የበርካታ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ግጭት እና ጥቃት ተከስተዋል።
ሦስተኛ ወሩን በያዘው የ2019 ዓ.ም. በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ በሱማሌ ክልል የተከሰቱ ግጭቶች እና ጥቃቶችን እንደ ምሳሌ ይጠቀሳሉ።
በጥቅምት ወር ብቻ በደቡብ ኢትዮጵያ ፣በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ ክልል፣ በኦሮሚያ አርሲ ሮቤ፣ ሽርካ ፣ መርቲ ወረዳ፣ በቀድሞው ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን እንዲሁም በሞያሌ ከተማ በርካታ ሰዎች የተገደሉበት ግጭት እና ጥቃት በተለያየ ቀን ተፈጽሟል።
በእነዚህ አካባቢዎች በተፈጸመው ጥቃት እንዲሁም በተከሰተው ግጭት ከ200 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ቢቢሲ ከነዋሪዎች እና ከዐይን እማኞች ባገኘው መረጃ ማወቅ ተችሏል።
ከተጠቀሱት አካባቢዎች በርካታ ሰዎች የተገደሉበት አንዱ የኦሮሚያ ክልል ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰቱ ግጭቶችን፣ ጥቃቶችን፣ አመጾችን እና ተያያዥ ክስተቶችን የሚመዘግበው የአክሌድ መረጃ እንደሚያሳየው በክልሉ የተፈጸሙ አብዛኛው ጥቃቶች ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ ናቸው።
ተቋሙ ወደ ቢቢሲ በላከው መረጃ የመስከረም እና የጥቅምት ወራት በኢትዮጵያ በተፈጸሙ ፖለቲካዊ ግብ" ባላቸው ጥቃቶች ሳቢያ 1,556 ሞት ተመዝግበዋል ብሏል።
በባለፈው የጥቅምት ወር ብቻ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች በተፈጸሙ "ፖለቲካዊ ግብ" ባላቸው ጥቃቶች ሳቢያ 863 ሞት መመዝገባቸውን አክሌድ አስታውቋል። ከተመዘገበው ሞት ውስጥ 300 የሚሆነው ሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመ መሆኑንም ገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዩናይትድ ኪንግደም ሼፊልድ ዩኒቨርስቲ የሕግ መምሕር እና የምሥራቅ አፍሪካ የፖለቲካ የግጭቶች ተንታኝ አወል ቃሲም አሎ (ዶ/ር) የፌደራል መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች ዳግም ወደ ጦርነት መግባታቸው ለግጭቶቹ መብዛት አንድ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል። በትግራይ ካገረሸው ጦርነት በፊት ትብብር መመስረታቸውን ያስታወቁት ታጣቂ ቡድኖችም ለእነዚህ ግጭት እና ጥቃቶች መብዛት ሚና ሊኖራቸው እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
"የተቀናጀ በሚመስል መልኩ የትግራይ ጦርነት ሲፈነዳ እዚህ አካባቢ ላይ ያሉት የምናያቸው ችግሮች በምን ሁኔታ የተከሰቱ ማለት እንችላለን ለሚለው ጥያቄ አንድ መልስ የሚሆነው፣ ምናልባት ይሄ 'ትብብር ለኅልውና' የተባለው ቡድን ጦርነቱን ከመርዳት አንፃር፣ የመንግሥትን ኃይል ለመለጠጥ ያደረጉት ነገር ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ማድረግ ይቻላል" ሲሉ የግጭቶቹ መስፋፋት መንስዔ ያሉትን ገልጸዋል።
ጥቅምት 15 እና 16/2019 ዓ. ም. በኦሮሚያ ክልል በቀድሞው ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን አቤ ደንጎሮ ወረዳ ቱሉ፡ የአርሲ ዞን፣ ሽርካ ወረዳ እና በአርሲ ሮቤ ወረዳ በታጣቂዎች በተፈፀሙ ጥቃቶች በድምር 118 ሰዎች መገደላቸው ቢቢሲ በተለያዩ ዘገባዎቹ ማወቅ ችሏል።
የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በክልሉ ለተፈጸሙ ጥቃቶች "ትብብር ለሕልውና" በተሰኘው ጥምረት ውስጥ ያሉትን ታጣቂዎች ተጠያቂ አድርጓል። ህወሓትን ጨምሮ ሰባት ታጣቂ ቡድኖችን ያካተተው ይህ ጥምረት የኢትዮጵያን መንግሥት በማስወገድ "የሽግግር መንግሥት" የመመሥረት ዓላማ ያለው ነው።
በዚህ ጥምረት ውስጥ አባል የሆኑት ኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን እና የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ አባላት በአርሲ ሸርካ ወረዳ ጥቃት መፈጸማቸውን የክልሉ መንግሥት ገልጿል። የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ከሁለት ሳምንት በፊት በሰጡት መግለጫ፤ የታጣቂ ቡድኖቹ አባላት ናቸው የተባሉ 73 ሰዎች በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እያለ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በባለፈው የጥቅምት ወር ብቻ በርካታ ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት አስተናግዷል። በክልሉ አሶሳ ዞን ቡልዲግሉ ወረዳ በምትገኘው ዳለቲ ቀበሌ ቅምት 26/2019 ዓ. ም. ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት 52 ሰዎች መገደላቸው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ለቢቢሲ ገልጿል።
አቶ ጌታቸው በአገሪቱ ከሚነሱ ግጭቶች የሚጠቀሙ ኃይሎች ውስጥ የመንግሥት አካላት መኖራቸውን ገልጸው፣ መንግሥት ግጭቶቹን በተመለከተ የሚሰጣቸውን ማብራሪያዎች "እንደ ጥሩ ምክንያት እንደማይወስዱት" ተናግረዋል። መሠረታዊ የሆነ የግጭትን መቆጣጠር የሚቻልበት መንገድ ካልተፈጠረ በስተቀር በአገሪቱ የሚስተዋለው ግጭት እና ጥቃት ሊቆም እንደማይችል ገልጸዋል።
"ብዙ ሰው ልብ የማይለው ኢትዮጵያ ውስጥ እየቀጠለ ያሉ ግጭቶች ዋናው ሹፌር የሚመስለኝ ቋሚ ሆነው እንዲቀጥሉ የሚያደርጋቸው የግጭትን መሠረት ያደረገ ፖለቲካል ኢኮኖሚ [በመኖሩ ነው]" ሲሉ አስረድተዋል።
ጌታቸው አክለውም "እነዚህ ችግሮች እስካልተፈቱ፣ መሠረታዊ የሆነ ግጭት የምንቆጣጠርበት መንገድ እስካልተፈጠረ ድረስ፣ በቅርቡ እነዚህ ግጭቶች ያቆማሉ የሚል እምነት የለኝም" በማለት አስተያየታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በአገሪቱ የሚታየው ግጭት "መንግሥት ዜጎች መጠበቅ አለመቻሉን" ማሳያ አድርገው ያነሱት ደግሞ አወል አሎ ናቸው።
"በየቦታው የሚታየው ግጭት እና ንጹኃኑ ማኅበረሰብ ላይ የሚደርሰው ችግር የሚያሳየው በግልጽ መንግሥት እየጠበቃቸው አይደልም መንግሥት ደግሞ እንደ አንድ ድክመት መቀበል አለበት" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"የጥቃት መጠኑ ጨምሯል የሚያስብለን አይደለም" - ኢሰመኮ
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች የተከሰቱ ጥቃቶችን እየመረመረ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጿል።
ተቋሙ ከኦሮሚያ ክልል ውጭ የተፈጸሙ ጥቃቶችን በተመለከተ ምርመራ እያካሔደ መሆኑን የሰብአዊ መብቶች ትምሕርት እና ሥልጠና ኮሚሽነር የሆኑት አቶ በዳሳ ለሜሳ ለቢቢሲ ገልጸዋል። በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፣ በኦሮሚያ ክልል በሆሮ ጉድሩ እና በምስራቅ ወለጋ እና አርሲ የመረጃ ማሰባሰብ ሥራ የተጠናቀቀባቸው ክልሎች መሆናቸውም ገልጸዋል።
በብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋም በአርሲ ሽርካ ወረዳ የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ ባወጣው መግለጫ 48 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል። ይህን ጥቃት የፈጸሙት በክልሉ የሚንቀሳቀሰው "የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት" እና "ኢ መደበኛ ታጣቂዎች" መሆናቸውንም ይጠቅሳል።
ኮሚሽነሩ በማብራሪያቸው "አሁንም ተመሳሳይ ክስተቶች እየተፈጠሩ ናቸው። የኛ ምርመራም በሂደት ላይ ነው ያለው" ብለዋል።
"አዳዲሶቹን ደግሞ በየቀኑ የሚፈጸሙትን [ጥቃቶች]፣ የሚፈጠሩትን ሁኔታዎች፣ ክስተቶችን የመመዝገብ፣ ከተመዘገቡ በኋላ ደግሞ እያንዳንዱ ሁኔታ በርቀት እንዲሆን እያረጋገጥን ነው ያለነው ሁኔታው ደግሞ ሲመች በአጠቃላይ በቦታው ተገኝተን እንደተለመደው የምርመራ ስራችንን እናከናውናለን" ሲሉ አስረድተዋል።
ምንም እንኳን ተቋሙ ይሄንን ቢልም በአገሪቱ "በአንፃራዊነት ጥቃቶች መቀነሳቸውን" ኮሚሽነር በዳሳ ተናግረዋል። "ጎላ ብሎ ስለወጣ ነው እንጂ ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ጥቃቶች በተለያየ አካባቢዎች ይፈጸሙ ነበር አዲስ የጥቃት መጠኑ ጨምሯል የሚያስብለን አይደለም በእኛ ሪከርድ" በማለት ተናግረዋል።

































