አሜሪካ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ውጥረትን ለማርገብ አሰብ ወደብን "በድርድር መሣሪያነት" እንዳታቀርብ አምስት ሴናተሮች ጠየቁ

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ከኢትዮጵያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጤሞቲዮስ ጋር
የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ባለፈው ዓመት ግንቦት ላይ በዋሽንግተን ከኢትዮጵያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጤሞቲዮስ ጋር ተገናኝተው ነበር
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

የኢትዮጵያ መንግሥት አሰብ ወደብን በኃይል ለመያዝ የሚያደርገው ማንኛውም ጥረት በአሜሪካ "ተቀባይነት እንደማይኖረው ግልፅ" እንዲደረግ የአሜሪካ ሴኔት አባል የሆኑ አምስት ዴሞክራቶች አሳሰቡ።

ሴናተሮቹ፣ አሜሪካ በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ በምታደርገው ጥረት ውስጥ አሰብ ወደብ "በድርድር መሣሪያነት እንዳይቀርብም" ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ "የአፍሪካ ቀንድ እና ቀይ ባሕርን" አለመረጋጋት ውስጥ ሊከትት ወደሚችል "ባለብዙ ግንባር ግጭት" ሊያመራ ይችላል የሚል ስጋት ያነሱት ሴናተሮቹ፣ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ዲፕሎማሲያዊ ጣልቃ ገብነት እንዲያደርግ በድጋሚ ጥያቄ አቅርበዋል።

ማክሰኞ ኅዳር 1/2019 ዓ. ም. ለአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ደብዳቤ የጻፉት በሴኔቱ የውጭ ግንኙነቶች ኮሚቴ አባል የሆኑ የዴሞክራቲክ ፓርቲ ተወካዮች ናቸው። የዚህን ደብዳቤ ትክክለኛነት በአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ የዴሞክራቶች ፕሬስ ጽሕፈት ቤት ለቢቢሲ አማርኛ አረጋግጧል።

ፊርማቸውን ካኖሩት ሴናተሮች መካከል የውጭ ግንኙነቶች ኮሚቴ ከፍተኛ አባል የሆኑት ጂን ሸሂን እና እኚህን ከፍተኛ አባል ይተካሉ ተብለው የሚጠበቁት ክሪስቶፈር ኤ ኩንስ ይገኙበታል።

"የኤርትራ ኃይሎች ትግራይ ውስጥ እንደሚገኙ መዘገቡን" እንዲሁም ሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ማቋረጣቸውን የጠቀሱት ሴናተሮቹ፣ "በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል አዲስ ጦርነት የመቀስቀስ ዕድሉ ከፍተኛ ሆኖ ይታያል" ብለዋል።

ኢትዮጵያ እና ግብፅ አንዳቸው የሌላኛቸውን ዲፕሎማቶች ማባራራቸውን አስታውሰዋል። አዲስ አበባ እና ካርቱምም ታጣቂዎችን በመደገፍ እንደሚካሰሱ ጠቅሰዋል። በአገር ውስጥ የሚካሄዱ ግጭቶች መቀጠላቸውንም እንዲሁ በደብዳቤያቸው አስፍረዋል።

ሴናተሮቹ፣ "ይህ ሁኔታ ኢትዮጵያን፣ ሰፊውን የአፍሪካ ቀንድ፣ ቀይ ባሕርን፣ በባሕረ ሰላጤው የሚገኙ አጋሮቻችንን እና ወሳኝ የንግድ የባሕር መስመሮችን አለመረጋጋት ውስጥ ሊከት ወደሚችል ባለብዙ ግንባር ግጭት ሊያመራ ይችላል" ሲሉ አሳስበዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኢትዮጵያ ውስጥ ከተፈጠረው "የሌላ አውዳሚ የእርስ በእርስ ጦርነት እና ቀጣናዊ ግጭት ስጋት" አንጻር፣ የዋሽንግተን ዲፕሎማሲያዊ ተሳትፎ ይህንን የሚመጥን "አጣዳፊነት፣ ጉልህነት እና ቅንጅት" እንደሚጎድለው በማንሳት ተችተዋል።

"አሜሪካ ሁሉንም የሚመለከታቸው አካላት ወደ ጠረጴዛ የሚያመጣ እና በአሁኑ ግጭት የሚታዩ የተቀየሩ ሁኔታዎች የሚያንጸባርቅ የታደሰ ፖለቲካዊ ውይይት እንዲደረግ በአስቸኳይ ልትደግፍ ይገባል" ብለዋል።

ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ ንግግር በሚደረግበት ወቅት በኤርትራ የሚገኘውን አሰብ ወደብ በወታደራዊ ኃይል የመያዝ ጉዳይ ከጠረጴዛው ውጪ መሆን እንዳለበት በአጽንኦት አንስተዋል።

"የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱም በማንኛውም ድርድር ወቅት [አሰብ] ወደብን የመያዝ ጉዳይን እንደ ዲፕሎማሲያዊ መሣሪያ እንዳይጠቀም እናሳስባለን" ሲሉ በደብዳቤው አስጠንቅቀዋል።

በተጨማሪም፣ "የኢትዮጵያ መንግሥት አሰብ ወደብን በኃይል ለማግኘት የሚያደርገው ማንኛውም ሙከራ በአሜሪካ እንደማይደገፍ ወይም ተቀባይነት እንደሌለው ግልጽ መደረግ አለበት" ሲሉ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ መያዝ አለበት ያሉትን አቋም አስታውቀዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት በቀይ ባሕር ላይ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎት እንዳለው ላለፉት ሦስት ዓመታት በይፋ ሲገልጽ ቆይቷል። የአሰብ ወደብ ጉዳይን በተደጋጋሚ ሲያነሳ የቆየው መንግሥት፣ ኢትዮጵያ ይህንን ፍላጎት ማሳካት የምትሻው በንግድ ልውውጥ መሆኑን ገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም "ሰጥቶ የመቀበል አማራጭን" አቅርበዋል። የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል አዛዥ አድሚራል ክንዱ ገዙ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባደረጉት ንግግር ደግሞ፣ ቀይ ባሕርን ለማስመለስ የሚደረገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የማይሳካ ከሆነ፣ "የመጨረሻው እና የማንመርጠው መፍትሔ" ሲሉ በገለጹት መንገድ የባሕር በር ማግኘት "የማይቀር" መሆኑን ገልጸዋል።

ጂን ሸሂን
የምስሉ መግለጫ, ደብዳቤውን የጻፉት ሴናተሮች የተመሩት በሴኔት የውጭ ግንኙነቶች ኮሚቴ ከፍተኛ አባል በሆኑት ጂን ሸሂን ነው

"ሲሆን በቀለለው፣ መለስተኛ ዋጋ በሚጠይቀው፣ በሠለጠነው መንገድ፤ ካልሆነ በመጨረሻው መንገድ ምርጫችን አድርገን መሄድ የማይቀር መሆኑን አምነን እየተዘጋጀን ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።

ኤርትራ በበኩሏ አዲስ አበባ "ሉዓላዊ የባሕር በር" የማግኘት ሐሳብን በማንሳት "ወረራ" የመፈጸም ዕቅድ አላት የሚል ክስ አቅርባለች።

በመስከረም አጋማሽ በመንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል በድጋሚ ግጭት መቀስቀሱን ይህ በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረውን ውጥረት አባብሷል።

በመስከረም መጨረሻ የኤርትራ ኃይሎች ግጭት ወዳለባቸው የትግራይ ክልል አካባቢዎች መግባታቸው ከተገለጸ በኋላ፣ ኢትዮጵያ "ራሷን ከመከላከል ውጪ አማራጭ እንደሌላት" ገልጻ ነበር። ኤርትራ ይህንን ክስ ውድቅ አድርጋለች።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ከሦስት ሳምንት በፊት ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ድንበሮቻቸው ላይ ወታደሮችን እንዳሰፈሩ ተናግረው ነበረው።

ይህ ዓይነቱ የሠራዊት እንቅስቃሴ ደግሞ "ወደ መጠነ ሰፊ ግጭት ሊያመራ ይችል ይሆን" የሚል ስጋት መፍጠሩን አንስተዋል። በዓለም ላይ ሌላ ግጭት እንዲፈጠር እንደማይፈለግም አክለዋል።

ሩቢዮ በወቅቱ፣ በኢትዮጵያ ከመንግሥት ጋር ግጭት ውስጥ ያሉትን ታጣቂዎች "ተገንጣይ ቡድኖች" በማለት የገለጹ ሲሆን "የሽብር" ጥቃቶችን ፈጽመዋል ሲሉም ከስሰው ነበር። አዲስ አበባ ውስጥ የድሮን ጥቃት መፈጸሙንም አንስተዋል።

ወታደሮች መቀለ አየር ማረፊያ
የምስሉ መግለጫ, መስከረም ላይ ዳግም ግጭት ከተነሳ በኋላ ፌደራል መንግሥት እና አጋር ኃይሎቹ የትግራይ ክልል ዋና ዋና ከተማዎችን ተቆጣጥረዋል።

አሜሪካ በትግራይ ጦርነት ወቅት ኢትዮጵያ ላይ ጥላው የነበረውን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ግንቦት ላይ ማንሳቷ፣ አሁን በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ለተፈጠረው ውጥረት አስተዋጾ አድርጎ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተጠይቀው ነበር።

ሩቢዮ፣ ማዕቀቡ መነሳቱ አሁን እየተፈጠረ ካለው ሁኔታ ጋር ግንኙነት እንደሌለው በመግለጽ ምላሽ ሰጥተዋል።

ማክሰኞ ለሩቢዮ ደብዳቤ የላኩት ዴሞክራት ሴናተሮች ግን፣ ግጭቶች በቀጠሉበት በአሁኑ ሁኔታ ውስጥ "አሜሪካ ለኢትዮጵያ አዲስ የጦር መሣሪያዎች ሽያጭ እንዳይደረግ መከልከል" እንዳለባት አሳስበዋል።

አምስቱ ሴናተሮች አክለውም፣ በኢትዮጵያ ያለው ግጭት ወደ ቀጣናው እንዳይስፋፋ አሜሪካ እርምጃ እንድትወስድ ጠይቀዋል። "አሜሪካ ከኤርትራ፣ ከግብፅ፣ ከሱዳን እና ከሌሎች የቀጣናው ተዋናዮች ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖ ልትጠቀምበት ይገባል" ብለዋል።

ሦስቱ አገራት ላይ ይህንን ዓይነቱን አካሄድ በመከተል፣ "ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር፣ ለታጣቂ ቡድኖች የጦር መሣሪያ ወይም ሌላ ቁሳዊ አቅርቦት እንዳይደረግ እንዲሁም ግጭቱን ሊያሰፉ የሚችሉ ሌሎች እርምጃዎችን" እንድታስቀር ጠይቀዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ፣ "ኢትዮጵያ የቀጣናዊ የውክልና ጦርነት ሜዳ መሆን እንደሌለባት አሜሪካ በግልጽ ማሳወቅ አለባት" ብለዋል።

ይህንን ደብዳቤ በተመለከተ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በኩል በይፋ የተሰጠ አስተያየት የለም። ይሁን እንጂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ከጦርነቱ ማገርሸት በኋላ በጥቅምት መጀመሪያ ስለ ሁኔታው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ተነጋግረው ነበር።

"ከኤርትራ ጋር እየተባባሰ የመጣውን ውጥረት" በተመለከተ በተደረገው በዚህ ንግግር፣ ሩቢዮ "በሁሉም ወገኖች በኩል ውጥረት ማርገብን" እንደሚደግፉ መሥሪያ ቤታቸው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በወቅቱ ሩቢዮ "ሁሉም የአፍሪካ ቀንድ አገራት የጎረቤቶቻቸውን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማክበር አለባቸው" ማለታቸው ተጠቅሷል። አገራቱ "ድንበር ተሻጋሪ ወረራ እንዳይፈጽሙ" ማሳሰባቸውም ተገልጿል።