ኢትዮጵያን የሳይበር ጥቃት ምን ያህል ያሰጋታል?

የኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነት ማኅበር መሥራችና ዳይሬክተር ዶ/ር ብርሃኑ በየነ
የምስሉ መግለጫ, የኢትዮጵያ የሳይበር ደኅንነት ማኅበር መሥራች እና ዳይሬክተር ዶ/ር ብርሃኑ በየነ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

በቅርቡ በፈረንሳይ የደረሰ አንድ የሳይበር ጥቃት የዲጂታል ደኅንነት ስጋት ከኮምፒውተሮች እና ከድረ ገጾች አልፎ የሰዎችን የዕለት ተዕለት ኑሮ ሊጎዳ እንደሚችል አሳይቷል።

በመቶዎች በሚቆጠሩ ሱፐርማርኬቶች ውስጥ ያሉ የማቀዝቀዣ ሥርዓቶች የሙቀት መጠናቸው እንዲጨምር ባደረገው ጥቃት ምክንያት በሚሊዮኖች ዩሮ የሚገመት ትኩስና የቀዘቀዘ ምግብ ተበላሽቷል።

በኋላም በተለያዩ የአውሮፓ አገራት ተመሳሳይ ጥቃቶች መፈጸማቸው ተዘግቧል።

ምንም እንኳን እነዚህ ጥቃቶች እርስ በእርሳቸው የተያያዙ ስለመሆናቸው የተረጋገጠ መረጃ ባይኖርም፣ በችርቻሮ ንግድ፣ በምግብ ስርጭት እና በአውቶሜትድ የኢንዱስትሪ ሥርዓቶች ላይ ያለውን የሳይበር ተጋላጭነት በድጋሚ ወደ ትኩረት አምጥተዋል።

የኢንፎርሜሽን ኔትወርክ ሴኩሪቲ አስተዳደር (INSA) ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሐሚድ "ንቁ ዜጋ ለደኅንነቱ የተጠበቀ አገር" በሚል መሪ ቃል የተከበረውን 7ኛውን የብሔራዊ ሳይበር ደኅንነት ወር በተመለከተ መግለጫ በሰጡበት ወቅት፤ በዓለም አቀፍ እና በአገራዊ ደረጃ የሳይበር ጥቃቶች ቁጥርና ተጽዕኖ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል።

በዓለም ደረጃ በሳይበር ወንጀል የሚደርሰው ዓመታዊ የኢኮኖሚ ኪሳራ ከ9.5 ትሪሊዮን እስከ 10.5 ትሪሊዮን ዶላር እንደደረሰም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያም የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመሩ መሆኑን አስረድተው፤ በ2018 ዓ. ም. ብቻ ከ71 ሺህ በላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

የሳይበር ጥቃት ምንድን ነው?

የሳይበር ጥቃት ማለት በኮምፒውተር ሥርዓቶች፣ በመረጃ ቋቶች፣ በድረ ገጾች ወይም በመረብ አውታሮች ላይ የሚፈጸም ሕገወጥ የዲጂታል ጥቃት መሆኑን የኢትዮጵያ የሳይበር ደኅንነት ማኅበር መሥራች እና ዳይሬክተር ዶ/ር ብርሃኑ በየነ ለቢቢሲ አብራርተዋል።

በዓለም ዙሪያ የሚታዩ ዋና ዋና የሳይበር ጥቃት ዓይነቶች የመረጃ ስርቆት (Data Breach)፣ የኢሜይል ማጭበርበር (Phishing)፣ ማልዌር (Malware) እና ራንሰምዌር (Ransomware) ናቸው።

በኢትዮጵያም ከዲጂታል አገልግሎቶች መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሳይበር ጥቃት ስጋት እየጨመረ መምጣቱን ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ኮምፒውተሩ ላይ ሆኖ የሚሰራ ወጣት

የሳይበር ጥቃት ለምን ጨመረ?

ዶ/ር ብርሃኑ የሳይበር ጥቃት መጨመር ከበርካታ ቴክኖሎጂያዊ እና ጂኦፖለቲካዊ ለውጦች ጋር የተያያዘ መሆኑን ያስረዳሉ።

ከእነዚህ መካከል የዲጂታል ሽግግር መፋጠን፣ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) መስፋፋት፣ የራንሰምዌር ጥቃቶች መበራከት፣ በአገራት መካከል ያለ የጂኦፖለቲካ ውጥረት፣ ሰውን ማዕከል ያደረጉ የማጭበርበር ዘዴዎች እንዲሁም በስማርት መሣሪያዎች ላይ ያለ ተጋላጭነት ተጠቃሽ ናቸው።

በተለይም የሰው ሠራሽ አስተውሎት የሳይበር ጥቃት ለማድረስ እና ጥቃቱን ለመከላከልም ጥቅም ላይ መዋሉ ሁኔታውን ከዚህ ቀደም ከነበረው በበለጠ ውስብስብ አድርጎታል።

እንደ ዶ/ር ብርሃኑ ማብራሪያ በዓለማችን የሚታዩትን ጦርነቶች በግልጽ እና በስውር የሚካሄዱ ብለን ብንመድብ "በስውር የሚደረገው ያይላል" በማለት ይህም በዳታ እና በሳይበር ደኅንነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያስረዳሉ።

ሰውን ማዕከል ያደረገ የሳይበር ጥቃት ሌላው ከምክንያቶቹ መካከል የሚጠቀስ ሲሆን የሰዎችን ባህሪ አጥንቶ፣ በዚያ ባህሪያቸው ገብቶ ማጭበርበር የተለመደ እና አስቸጋሪ እየሆነ የመጣው የጥቃት ዓይነት መሆኑን ገልጸዋል።

ክሪፕቶከረንሲ እና ዳርክ ዌብ ሌላው ለሳይበር ጥቃት ምክንያት መሆኑን የሚያነሱት ዶ/ር ብርሃኑ፣ እውቅ የክሪፕቶከረንሲ ኩባንያ የሆነው ባይናንስ 6.3 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የዲጂታል ገንዘብ ላይ ተጽዕኖ ያሳደረ ስርቆት እንደተፈጸመበት አስታውሰዋል።

ክሪፕቶከረንሲ በስውር የሚፈጸም ግብይት ስለሆነ ለጥቃት ከፍተኛ የሆነ ተጋላጭነት አለው ሲሉ አብራርተዋል።

ማቲልዳ ጆቫኒ፣ የሳይበር ደህንነት ባለሙያ
የምስሉ መግለጫ, ማቲልዳ ጆቫኒ፣ የሳይበር ደህንነት ባለሙያ

አጥቂዎችን መለየት ይቻላል?

በኢትዮጵያ የሳይበር ደኅንነት ማኅበር የፕሮግራም አስተባባሪ የሆነችው ማቲልዳ ጆቫኒ እንደምትለው፣ የዲጂታል ፎረንሲክስ ምርመራን በመጠቀም የጥቃቱን መነሻ፣ ጥቃቱን ለመፈጸም የተጠቀሙበትን መንገድ እና ጥቃቱ ማንን ሊጠቅም እንደሚችል በመተንተን አድራሻውን ማግኘት ይቻላል።

ሆኖም የሳይበር ጥቃቶች ዓለም አቀፍ መሆናቸው፣ በብዙ አገራት የተበተኑ ሰርቨሮችን መጠቀማቸው እና የማንነት መደበቂያ መሣሪያዎችን መጠቀማቸው አጥቂዎችን ማወቅ እንዲከብድ ያደርጋል።

የአይፒ አድራሻዎች፣ የዶሜይን ስሞች እና የማልዌር ኮድ ትንተና የጥቃቱን መነሻ እና ፈጻሚውን ለመለየት ይረዳሉ።

የጥቃት ስልቶችን፣ የፊሺንግ መልዕክቶችን ቋንቋ እና ጥቃቱን የተፈጸመበት ሰዓት በመመርመር ስለ ፈጻሚዎቹ ፍንጭ ማግኘት ይቻላል።

የክሪፕቶከረንሲ የገንዘብ ዝውውሮችን መከታተል እና የጥቃቱን ዓላማ መተንተን ከጀርባው ያሉ አካላትን ለመለየት እንደሚያግዝ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ባለሙያዎች አስረድተዋል።

ሆኖም ጥቃት ፈጻሚዎች ሆን ብለው የሌላ ቡድን አሻራ ሊተዉ ስለሚችሉ፣ ባለሙያዎች ሁሉንም ቴክኒካዊና የባህሪ ፍንጮች በማጣመር የፈጻሚውን ማንነት ይገምታሉ።

ምን ያህል አስጊ ነው?

የኢትዮጵያ የሳይበር ደኅንነት ማኅበር ባለሙያዎቹ እንደሚሉት የሳይበር ጥቃት ከፋይናንስ ኪሳራ በላይ የአገር ደኅንነትን፣ ኢኮኖሚን፣ የሕዝብ አገልግሎቶችን እና ማኅበራዊ መረጋጋትን ሊያናጋ ይችላል።

ዘመናዊ ጥቃቶች ከመረጃ ስርቆት ባሻገር የባንክ አገልግሎቶችን ሊያቋርጡ ይችላሉ፣ የኤሌትሪክ ኃይል መረቦችን ሊያሰናክሉ ይችላሉ፤ የጤና ተቋማትን ሥርዓቶች ሊያጠቁ፣ በሐሰተኛ መረጃ ስርጭት የማኅበራዊ ግጭት መንስኤ ሊሆኑም እንደሚችሉ ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች እየተናገሩ ያሉትም የወደፊት ግጭቶች ከመሬት፣ ከባሕር እና ከአየር ጦርነት ባሻገር በዲጂታል ምኅዳር እየተካሄዱ መሆናቸውን ነው።

የሳይበር ጥቃት በዓለማችን ላይ አሳሳቢ እየሆኑ ከመጡ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው

ኢትዮጵያ ምን ያህል ተጋላጭ ናት?

በኢትዮጵያ የዲጂታላይዜሽን ሒደት እየፋጠነ በመምጣቱ የሳይበር ጥቃት ዒላማ ሊሆኑ የሚችሉ ወሳኝ መሠረተ ልማቶች እየበዙ ነው።

ከእነዚህም መካከል የኃይል ማመንጫዎች እና ግድቦች፣ የጤና ተቋማት፣ የባንክ እና የክፍያ ሥርዓቶች፣ የቴሌኮሙኒኬሽን አውታሮች፣ የአቪዬሽን አገልግሎቶች እንዲሁም የመንግሥት የመረጃ ሥርዓቶች ይጠቀሳሉ።

በተለይም የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች መበራከት፣ የሞባይል ባንኪንግ እና የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶች መስፋፋት የሳይበር ደኅንነትን የአገር ደኅንነት አካል አድርጎ አስቀምጦታል።

ምን መደረግ አለበት?

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዩናይትድ ኪንግደም በጥቅምት 2026 ባወጣችው የሳይበር ጥቃት ስጋት ማስጠንቀቂያ ዜጎች ቢያንስ ለሦስት ቀናት የሚበቃ ምግብ እና ውኃ እንዲያከማቹ መክራለች።

ጃፓንም በተመሳሳይ ሁኔታ ከኅዳር 2026 ጀምሮ ተግባራዊ በሚሆነው አዲስ የአደጋ መከላከል መመሪያ መሠረት ዜጎች የሦስት ቀን እና ቢቻል የአንድ ሳምንት አስፈላጊ እቃዎች ክምችት እንዲኖራቸው አሳስባለች።

ጀርመን፣ ስዊድን፣ ኖርዌይ እና ፊንላንድም ከሚጨምረው የሳይበር ጥቃት ስጋት ጋር በተያያዘ ዜጎቻቸው ለድንገተኛ አደጋዎች ዝግጁ እንዲሆኑ በተደጋጋሚ ምክሮችን ሲያስተላልፉ ቆይተዋል።

በአሜሪካም የፌዴራል የአደጋ ጊዜ አስተዳደር ኤጀንሲ (FEMA) ለረዥም ጊዜ ሲያስተዋውቀው በቆየው የአደጋ ጊዜ ዝግጁነት መመሪያ መሠረት፣ እያንዳንዱ ቤተሰብ ቢያንስ ለሦስት ቀናት የሚበቃ ምግብ፣ ውኃ እና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶች እንዲያዘጋጅ ይመከራል።

እንደ ሳይበር ደኅንነት ባለሙያው ዶ/ር ብርሃኑ ገለጻ፣ እነዚህ አገራት የሳይበር ጥቃት ወይም ሌሎች አደጋዎች ቢያጋጥሙ ዜጎቻቸው ራሳቸውን ለመጠበቅ እንዲችሉ የማንቂያ መልዕክቶችን እና የዝግጁነት ምክሮችን ይሰጣሉ።

በአፍሪካ ግን ይህ ዓይነቱ የሕዝብ ግንዛቤ ማሳደግ እና የቅድመ ዝግጁነት ሥርዓት በበቂ ደረጃ እንደማይታይ በመጥቀስ፣ አገራቱ ከእነዚህ ተሞክሮዎች ትምህርት ሊወስዱ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ባለሙያዎቹ እንደሚመክሩት የሳይበር ጥቃትን ለመቀነስ የቴክኖሎጂ መፍትሔዎች ብቻ በቂ አይደሉም። የሕዝብ ግንዛቤ፣ የተቋማት ዝግጁነት እና ጠንካራ ፖሊሲዎች ያስፈልጋሉ።

ማቲልዳ መደረግ ያለባቸውን ጥንቃቄዎች ስትዘረዝር፤ የሳይበር ንቃተ ሕሊናን ማሳደግ፣ የሠራተኞችን ሥልጠና ማጠናከር እና የሲስተም የደኅንነት ፍተሻዎችን በየጊዜው ማካሄድን ትጠቅሳለች።

በተጨማሪም ጠንካራ የሳይበር ደኅንነት ጥበቃ ፖሊሲዎችን መተግበር፣ የጥቃት ምልክቶች ሲታዩ በፍጥነት ሪፖርት ማድረግ እና ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን በልዩ ጥበቃ ሥር ማዋልን ትመክራለች።

የፈረንሳይ ሱፐርማርኬቶች ላይ ያነጣጠረው ጥቃት የሳይበር ወንጀል የሚያስከትለው ጉዳት በመረጃ ስርቆት ብቻ እንዳልተወሰነ አሳይቷል።

ዲጂታል ሥርዓቶች የኢኮኖሚ፣ የምግብ ሰንሰለት፣ የጤና እና የብሔራዊ ደኅንነት አካል በሆኑበት ዘመን የሳይበር ደኅንነት የቴክኖሎጂ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የልማትና የሉዓላዊነት ጉዳይ ሆኗል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ አፍሪካዊ አገራት የዲጂታል መሠረተ ልማታቸውን እያስፋፉ ባሉበት ወቅት ለሳይበር ጥቃቶች ተመጣጣኝ የመከላከያ አቅም መገንባት የወደፊቱ ቁልፍ ፈተና ይሆናል።