13 ሺህ ዶላር የተሸለመው ደራሲ ኤአይ መጠቀሙን የሚያሳይ ማስረጃ እንዳልተገኘ ተገለጸ

ዚምባብዌያዊው ደራሲ ሲምባራሼ ኩንዲዜዛ ለጽሑፉ ኤአይ መጠቀሙን ማስረጃ እንዳልተገኘ ኬን ፕራይዝ ገልጿል
የምስሉ መግለጫ, ዚምባብዌያዊው ደራሲ ሲምባራሼ ኩንዲዜዛ ለጽሑፉ ኤአይ መጠቀሙን ማስረጃ እንዳልተገኘ ኬን ፕራይዝ ገልጿል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ለአፍሪካውያን ደራሲዎች የሚሰጠውን ኬን ፕራይዝ ያሸነፈው ጸሐፊ ሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) መጠቀሙን የሚያሳይ ማስረጃ እንዳልተገኘ ተገለጸ።

በተደረገው ምርመራ መሠረት ዚምባብዌያዊው ደራሲ ሲምባራሼ ኩንዲዜዛ ለጽሑፉ ኤአይ መጠቀሙን ማስረጃ እንዳልተገኘ ኬን ፕራይዝ ገልጿል።

በአጭር ሥነ ጽሑፍ ዘርፍ የ13 ሺህ ዶላር ተሸላሚ መሆኑም ተገልጿል።

የኬን ፕራይዝ የቦርድ ኃላፊ ኤላህ ዋካታማ እንደተናገሩት፤ በአሜሪካው መጽሔት ዘ አትላንቲክ ላይ የወጣውን ዘገባ ተከትሎ በደራሲው ጽሑፍ ላይ ምርመራ ተደርጓል።

ዘ አትላንቲክ ያወጣው ዘገባ ጽሑፉ የኤአይ መሆኑን ይጠቁማል።

ኃላፊዋ ግን "ጥልቅ ምርመራ አድርገናል። ያገኘነው ማስረጃ ግልጽ ነው። 'ዘ ብሉ ፋይተር' የተጻፈው በሰው ነው" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ባስተላለፉት የቪድዮ መልዕክት አስተባብለዋል።

ደራሲው ኤአይ ተጠቅሟል የሚለው ክስ በማኅበራዊ ሚዲያ ከፍተኛ ውዝግብ አስነስቷል። ደራሲው ኤአይ አለመጠቀሙን ገልጿል።

የአትላንቲክ ጋዜጠኛ ቫውሂኒ ቫራ፣ በኤአይ የተዘጋጀ ጽሑፍን የሚፈትሸውን 'ፓናግራም' መተግበሪያ ተጠቅማ ምርመራ ማድረጓን ገልጻለች።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቤተሰቡ ፈተና ስለሚገጥመው ታዳጊ የሚያወሳው ጽሑፍ ሙሉ በሙሉ በኤአይ የተሠራ እንደሆነም ተናግራለች።

ዘገባው ከወጣ በኋላ በዚህ ዓመት የተሰጡ ሌሎች የሥነ ጽሑፍ ሽልማቶች ላይም ጥያቄ ተነስቷል።

ይህም ለትሪኒዳዱ ደራሲ ጃሚር ናዚር የተሰጠውን የኮመንዌልዝ የአጫጭር ሥነ ጽሑፍ ሽልማት ያካትታል። ደራሲው ኤአይ ተጠቅሟል የሚል ክስ ቀርቦበታል።

ካናዳዊ-ሄይቲያዊ ደራሲ ታይሰን ኦርሌን 'ጎንኮርት' ከተባለው ከፍተኛው የፈረንሳይ የሥነ ጽሑፍ ውድድር ውጭ እንዲሆን ተደርጓል። ደራሲው የመጀመሪያውን ልብ ወለዱን የጻፈው በኤአይ ነው ቢባልም አስተባብሏል።

የአትላንቲክ ጋዜጠኛ ከቢቢሲ ጋር ባደረገችው ቆይታ እንደገለጸችው፤ ከዚህ በፊት የኬን ፕራይዝ አሸናፊዎችን ጽሑፍ በፓናግራም መተግበሪያ ስትፈትሽ "መቶ በመቶ በሰው መጻፋቸውን" ማረጋገጥ ችላለች።

በጋዜጠኛዋ የቀረበውን ክስ ተከትሎ አፍሪካውያን ደራሲዎች ምላሽ ሰጥተዋል። የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች በኤአይ የተጻፉ ናቸው የሚሉ ውንጀላዎች ጥቁር ደራሲያን ላይ ያነጣጠሩ ናቸው ሲሉ አጣጥለዋል።

የኬን ፕራይዝ የቦርድ ኃላፊ ኤላህ ዋካታማ እንደተናገሩት ተቋሙ የጋዜጠኛዋን ውንጀላ "በጥንቃቄ እና ፍትሐዊነት በተሞላው መንገድ" ፈትሿል።

"ምርመራውን ያደረግነው ሰውን ማዕከል አድርገን ነው። ከደራሲው፣ ከ2026 የሽልማት ኮሚቴ እና ጽሑፉን መጀመሪያ ላይ ካተመው 'ሻሎ ቴልስ ሪቪው' ጋር ቃለ ምልልስ አድርገናል" ብለዋል።

ደራሲው ያዘጋጀው የመጀመሪያ ረቂቅ ላይ በገለልተኛ ወገኖች እና በባለሙያዎች ምርመራ መደረጉንም አክለዋል።

ጽሑፉ ገለልተኛ በሆነ የሳይበር ደኅንነት እና የዲጂታል ፎረንሲክ መርማሪ ፍተሻ እንደተደረገበት ተገልጿል።

ጥቅምት ላይ ኬን ፕራይዝን ባሸነፈ ማግሥት ደራሲ ሲምባራሼ ኩንዲዜዛ ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ፤ ለጽሑፉ መነሻ ያደረገው አንድ ግጥምን መሆኑን ተናግሯል።

አምና ጋና ውስጥ ደቡብ አፍሪካዊቷ ቫንጊሌ ጋንትሾ ያነበበችውን ግጥም ሰምቶ ለጽሑፉ እንዳነሳሳው ገልጿል። ደራሲዋ ቫንጊሌ ግጥሙን የጻፈችው አባቷ ለዓሣ ታንክ ያላቸውን ፍቅር መነሻ አድርጋ ነው።

ግጥሙን፣ በ2002 በዚምባብዌ ከተከሰተው የምጣኔ ሃብት ቀውስ እና በሕይወቱ ካሉ ልብ ወለዳዊ ትርክቶች ጋር እንዳዋሀደው ተናግሯል።