በጣሊያን፣ ስኮትላንድ እና ሰሜን አየርላንድ በሺህዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች ሐሰተኛ የቦምብ ዛቻ ደረሰባቸው

ተማሪዎች እና መምህራን ትምህርት ቤቶችን ለቅቀው ሲወጡ
የምስሉ መግለጫ, ረቡዕ ዕለት በደረሰው የቦምብ ዛቻ በጣሊያን ሮም ህፃናት ትምህርት ቤቶችን ለቅቀው እንዲወጡ ተደርጓል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በመላው ጣሊያን 6,300 ትምህርት ቤቶች እና በስኮትላንድ እና ሰሜን አየርላንድ ደግሞ ከ700 የሚበልጡ ትምህርት ቤቶች የቦምብ ጥቃት ዛቻ እንደደረሳቸው ባለሥልጣናት አስታወቁ።

በጣሊያን ለጥንቃቄ ሰዎች ከርካታ ትምህርት ቤቶች እንዲወጡ የተደረገ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ እስካሁን በተደረጉ ፍተሻዎች "ተጨባጭ አደጋ" ስለመኖሩ ማስረጃ እንዳልተገኘ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሯ በፌስቡክ ገፃቸው "ሪፖርቶቹ ስጋት እና ጭንቀት ለማሳደር በሚል የተደረጉ ይመስላሉ" ብለዋል።

የስኮትላንድ የትምህርት ሚኒስትር ሜሪሲ ማክአለን ለማኅበረሰቡ ስጋት የሚሆን ነገር እንደሌለ እና የሳይበር ወንጀል መርማሪዎች የመልዕክቶቹን ምንጭ ለመለየት እየሰሩ ነው ብለዋል።

በሰሜን አየርላንድ የትምህርት ባለሥልጣናት ትምህርት ቤቶች በፖሊስ ምክር ሀሳብ ካልቀረበላቸው በቀር ክፍት ሆነው እንዲቆዩ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

በሦስት አገራት የተፈጠሩት ክስተቶች የተያያዙ ስለመሆናቸው እስካሁን ግልፅ አይደለም።

የስኮትላንድ ፖሊስ ማስጠንቀቂያዎቹ የውሸት እንደሆኑ "ወዲያው ተመርምረዋል" ብሏል።

ይሁን እንጂ አንዳንድ የአካባቢ ባለሥልጣናት ለጥንቃቄ ሲባል በተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ሰዎች ለቅቀው እንዲወጡ መደረጉን ተናግረዋል።

የስኮትላንድ ፖሊስ "ምክራችን ትምህርት ቤቶችን ለቅቆ ለመውጣት የሚያስገድድ ነገር የለም። ወይም በኢሜሎች ብቻ ተመርኩዞ ሕፃናትን ከትምህርት ቤት የሚያርቅ ምንም ተጨባጭ ነገር እንደሌለ ነው" ብሏል።

የጣሊያን ባለሥልጣናት ረቡዕ ዕለት በአጠቃላይ ካሉት 7,476 ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለ6,300 ትምህርት ቤቶች አንድ ኢሜል መላኩን እና የግል ትምህርት ቤቶች ምንም ተፅዕኖ እንዳልደረሰባቸው አስታውቀዋል።

የኢሜል መልዕክቱ 'የቪሊያት ዲ ሚሶጊኒስታን' መሪ ነው ከተባለ 'ሚካኤል አንዶፖቭ' እንደሆነ የሚገልፅ ሲሆን፤ መልዕክቱ በበርካታ ትምህርት ቤቶች ጭንቀት ፈጥሯል።

ቢቢሲ ለስኮትላንድ ትምህርት ቤቶች የተላከውን ኢሜል የተመለከተ ሲሆን ተመሳሳይ አፃፃፍ የያዘ እና 'ሚካኤል አንዶፖቭ' 'የሬድ አውል' ፕሮጄክት መሪ መሆኑን ይገልፃል።

የጣሊያን የትምህርት ሚኒስትር ጁሴፔ ቫልዲታራ በጣሊያን ትምህርት ቤቶች ላይ የተፈጠረውን ክስተት ምንአልባት "የሳይበር ጥቃት" እንጂ እውነተኛ ስጋት እንዳልሆነ ተናግረዋል።

በአውሮፓ በረራዎችን፣ የንግድ መደበሮችን እና ሆስፒታሎችን ዒላማ ያደረገው አይነት ስልት ከጀርባ እንዳለ ግልፅ ነው ሲሉም አክለዋል።

የጣሊያን አየር ማረፊያዎች ከአውሮፓ አየር መንገዶች ጋር ባለፈው ሳምንት ሀሰተኛ የቦምብ ማስጠንቀቂያ ደርሷቸዋል።

ምንም እንኳ ለበርካታ ዛቻዎቹ አንድ አክራሪ ቡድን ኃላፊነት ቢወስድም በኋላ ላይ በሀሰተኛ ማስጠንቀቂያዎቹ ላይ እጁ እንደሌለ አስተባብሏል።