ትራምፕ በቢቢሲ ላይ ያቀረቡት ስም የማጥፋት ክስ እንዲቀጥል ተወሰነ

ዶናልድ ትራምፕ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ፍሎሪዳ የሚገኙ የፌደራል መንግሥት ዳኛ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቢቢሲ ላይ ያቀረቡት ሥም የማጥፋት ክስ አንዲቀጥል ወሰኑ። ይህም ቢቢሲ ክሱ ውድቅ እንዲደረግ ጥያቄ ካቀረበ በኋላ የተሰጠ ውሳኔ ነው።

ሆኖም ዳኛው ጄፍሪ ኩንትዝ በ10 ቢሊዮን ዶላር ክስ ውስጥ ፍትሃዊ ያልሆነ የንግድ ተግባር በሚል አንቀጽ ሥር የቀረበውን ሁለተኛ ክስ ውድቅ አድርገውታል።

ሆኖም ዳኛው ጄፍሪ ኩንትዝ በ10 ቢሊዮን ዶላር ክስ ውስጥ በፍሎሪዳ ግዛት የፍትሃዊ ንግድ ልማዶች ሕግ ስር የቀረበውን ሁለተኛ ክስ ውድቅ አድርገዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ቢቢሲ በፓናሮማ ዘጋቢ ፊልም ላይ ከካፒቶል ሂል አመፅ በፊት እንደ አውሮፓውያኑ 2021 ያደረጉትን ሁለት የንግግር ክፍሎችን አያይዞ በመስራቱ ክስ መሥርተዋል።

ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት በትሩዝ ሶሻል ላይ ባጋሩት ልጥፍ የዳኛውን ውሳኔ "ትልቅ ድል" ሲሉ ገልጸዋል።

የቢቢሲ ቃል አቀባይ በበኩላቸው "በዚህ ውሳኔ ተገርመናል፤ ሆኖም የፍርድ ቤቱን ሥልጣን እናከብራለን፣ እንዲሁም ጉዳዩ አሁን ወደ ቀጣዩ የሕግ ሂደት እንደሚሸጋገር እናስተውላለን" ብለዋል።

ቃል አቀባዩ አክለውም "በአቋማችን ላይ አሁንም ሙሉ እምነት አለን፤ እንዲሁም በተገቢው የሕግ ሂደት አማካኝነት ምላሻችንን መስጠታችንን እንቀጥላለን" ብለዋል።

ዳኛ ኩንትዝ ትራምፕ በቢቢሲ ላይ ያቀረቡት የሥም ማጥፋት ክስ ጉዳዩ እንዲቀጥል የሚያስችል በቂ መሠረት እንዳለው ቢናገሩም፣ በክሱ ይዘት እና ትክክለኛነት ላይ ግን የመጨረሻ ውሳኔ አልሰጡም።

ዳኛው ማክሰኞ ዕለት ባስተላለፉት ትዕዛዝ "ፕሬዚዳንት ትራምፕ እነዚህን ክሶች ማረጋገጥ እና በማጠቃለያ ፍርድ ወይም በችሎት ሂደት ወቅት ጉዳት እንደደረሰባቸው ማስረዳት ይችሉ እንደሆነ ለሌላ ቀን የሚተው ጉዳይ ነው" ሲሉ ጽፈዋል።

በፍሎሪዳ የቀረበው የትራምፕ ክስ፣ ቢቢሲ በ2021 ጥር 6 ቀን ከካፒቶል ሕንፃ ውጭ ያደረጉትን ንግግር "ሆን ብሎ፣ በክፉ አሳብ እና በአሳሳች መንገድ አርትኦት አድርጎ ለውጦታል" ሲል ይወነጅላል።

ቢቢሲ በበኩሉ ይቅርታ በመጠየቅ ስርጭቱ "ትራምፕ ለጥቃት እርምጃ በቀጥታ ጥሪ አቅርበዋል የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ፈጥሯል" ብሏል።

ከዚያ በኋላ ቢቢሲ ፕሮግራሙ በሕግ የተደነገጉትን የሥም ማጥፋት መስፈርቶች እንደማያሟላ እና በአሜሪካ ውስጥ እንዳልተሰራጨ በመግለጽ ክሱ ውድቅ እንዲደረግ ፍርድ ቤቱን ጠይቆ ነበር።

ከሥም ማጥፋት ክስ በተጨማሪ፣ ትራምፕ ቢቢሲ የፍሎሪዳን ሕግ፣ በተለይም "አታላይና ፍትሃዊ ያልሆኑ የንግድ ልማዶች ሕግ" ጥሷል ሲሉ ክስ አቅርበዋል።

ሆኖም ዳኛ ጄፍሪ ኩንትዝ ማክሰኞ ዕለት ይህንን ክስ ውድቅ በማድረግ፣ ዘጋቢ ፊልሙ የንግድ ዓላማ ያለው የንግግር ይዘት አይደለም በማለት ወስነዋል።

ባለፈው ወር ትራምፕ ቢቢሲ ላይ ለመሠረቱት የሥም ማጥፋት ክስ እስከ ታኅሳስ መጀመሪያ ድረስ ቃለ መሀላ በመፈጸም ጥያቄዎችን እንዲመልሱ ውሳኔ ሰጥተዋል።