በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ድንበር አካባቢዎች ውጊያ መካሄዱን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ

መንገድ ዳር ቆመ ታንክ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በዚህ ሳምንት በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ድንበር አካባቢዎች በመከላከያ ሠራዊት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል "በከባድ መሣሪያ የታገዘ" ግጭት ታካሂዶ እንደነበር ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ። ግጭቱን ተከትሎ ለድንበር በቀረቡ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል ሸራሮ፣ ዓዲ ሃገራይ እና ቢያራ በተባሉት አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ በሳምንቱ መጀመሪያ ማክሰኞ እና ረቡዕ ኅዳር 2 ቀን 2019 ዓ.ም. የተካሄደው ውጊያ፣ የገጠር አካባቢዎችን ያዳረሰ ነበር።

ባለፉት ቀናት በነበሩት ውጊያዎች፣ እንደ መድፍ ያሉ ከባድ መሣሪያ እና ድሮን ጥቅም ላይ መዋላቸውን ሁለት ነዋሪዎች ገልጸዋል።

አንድ ነዋሪ፣ "ማክሰኞ እና ረቡዕ ዕለት በዓዲ ክልተ የነበረው ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ቀኑ 8፡00 ሰዓት ያለምንም እረፍት ውጊያ ሲካደድ ነበር። ስንት ነፍሰ ጡሮች እና ሕፃናት ባሉበት፣ በድንገት የከባድ መሣሪያ እና የድሮን ድብደባ ሲከፈት ሕዝቡ በፍርሃት ተደናግጦ ቆመ" ብለዋል።

ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው፣ ሐሙስ ዕለት የትግራይ ኃይሎች ወደሚገኙበት የባድመ አቅጣጫ መድፍ ሲተኮስ እንደነበር ተናግረዋል።

በሸራሮ ከተማ፣ ከዓዲ ነብሪኢድ እና ከዓዲ ሓሮ የሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ "በከባድ መሣሪያ" በታገዘ ውጊያ በባድመ አቅጣጫ የምትገኘው ዓዲ ሕረት ላይ "ድብደባ በማካሄድ የትግራይ ኃይሎችን ለመግፋት" እንደሞከረ አስረድተዋል።

ከዓዲ ክልተ ወደ ሽረ ከተማ የተፈናቀሉ ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው፣ በዓዲ ክልተ የተካሄደው ውጊያ እጅግ ከባድ እንደነበር ገልጸዋል።

"በዓዲ ክልተ ከንጋት 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ድብደባ ሲካሄድ ውሏል። የእግረኛ ውጊያም ነበር፤ የዲሽቃ እና የብሬን ተኩስ ሲሰማ ነው የዋለው። ውጊያው የተካሄደው በትግራይ ሠራዊት እና በኢትዮጵያ ሠራዊት መካከል ብቻ ነው፤ በአካባቢው የኤርትራ ሠራዊት አልነበረም" ብለዋል።

ዓዲ ክልተ በአሁኑ ሰዓት በመከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ሥር መሆኗን አክለዋል።

ቢቢሲ በድንበር አካባቢ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ከመከላከያ ሠራዊት ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ኮሎኔል ቢረሳው ሽፈራው አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ትናንት አርብ ከመቀለ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ፣ ሠራዊቱ "የኛ ምሽጎች የነበሩ ላይ ነው" ያለው ሲሉ ተደምጠዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፣ "የመከላከያ ሠራዊት ከ6 ዓመታት በኋላ ወደ ኤርትራ ድንበር የቀድሞ ምሽጎቹ ተመልሷል" ማለታቸውን ብሔራዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ በፌስቡክ ገጹ ዘግቦ የነበረ ቢሆንም ከቆይታ በኋላ አንስቶታል።

የፌደራል መንግሥቱ አጋር የሆነው የትግራይ ሠላም ኃይል ቃል ኮሎኔል ሰሎሞን ኃይለማርያም ከቢቢሲ ትግርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ የተሠራጩትን በባድመ አካባቢ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሠራዊቶች መካከል ውጊያ ስለመካሄዱ የሚገልጹ መረጃዎች አስተባብለዋል።

ባድመ በየትኛው ኃይል ቁጥጥር ሥር እንደሆነች የተጠየቁት ኮሎኔል ሰሎሞን፣ "«ባድመ በእከሌ እጅ ናት፣ በእከሌ እጅ ናት ማለት ተገቢ አይመስለኝም፤ ምክንያቱም አካባቢው ወታደራዊ እንቅስቃሴ የሚደረግበት ስለሆነ በእከሌ እጅ ናት ማለት አይጠቅምም" ብለዋል።

ዛላምበሳ አካባቢ
Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቃል አቀባዩ አክለውም፣ ትግራይ ውስጥ ከፌደራል መንግሥቱ ጎን የተሠለፈው የትግራይ ሠላም ኃይል ከኤርትራ ሠራዊት ጋር እንደማይዋጋ ጠቁመዋል።

"ከኢትዮጵያ መከላከያ ጋር ሆነን እንደገና ከኤርትራ ጋር የምንዋጋበት ተልዕኮ የለንም። ድንበር ላይ ያለው ነገር የፌዴራል ጉዳይ ስለሆነ፣ የድንበር ጥበቃ እና የግዛት አንድነትን የማስከበር አጀንዳ መከላከያ ሠራዊትን ነው የሚመለከተው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሰሞነኛውን ሁኔታ በተመለከተ ከኤርትራ መንግሥት በኩልም የተሰጠ አስተያየት የለም። ይሁን እንጂ የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር በበኩሉ ትናንት በፌስቡክ ገጹ ባጋራው ጽሑፍ፣ የአገሪቱ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር ሊኖር የሚችል ግጭትን ለማስቆም ብቻ ሳይሆን ለማሸነፍ እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቋል።

በመንግሥታዊው የኤርትራ ቴሌቪዥንም የተነበበው ይህ ጽሑፍ፣ ኢትዮጵያ በኤርትራ ህዝብ ላይ "ወረራ አውጃለች" ሲል ከስሷል። ወረራ ሲል የገለጸው ተግባር መቼ እና የት እንደተፈጸመ አላብራራም።

በመስከረም አጋማሽ በትግራይ ክልል ዳግም ጦርነት ከተነሳ ወዲህ፣ ላለፉት ዓመታት ውጥረት ውስጥ የገቡት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወደ ወታደራዊ ግጭት ሊገቡ ይችላሉ የሚል ስጋት ተፈጥሯል። የኤርትራ ወታደሮች ወደ ትግራይ አካባቢዎች መግባታቸው እና የድሮን ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ተዘግቧል።

የኢትዮጵያ መንግሥትም የኤርትራ ሠራዊት ድንበር አልፎ በመግባት "ወረራ" እንደፈጸመ በመግለጽ፣ "ራሱን ከመከላከል ውጪ አማራጭ እንደሌለው" በመስከረም መጨረሻ ለተባበሩት መንግሥታት በጻፈው ደብዳቤ አስታውቆ ነበር።

ኤርትራም በተመሳሳይ መልኩ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በላከችው ደብዳቤ፣ ኢትዮጵያ "ራስን በመከላከል ስም" በሉዓላዊት የተመድ አባል ላይ የምትፈጽመውን ጦርነት ምክንያታዊ ለማድረግ እየሞከረች ነው የሚል ክስ አቅርባለች።

የዚህ ሳምንቱን ውጊያ ተከትሎ ግጭት በተካሄደባቸው ለድንበር የቀረቡ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች እንደ ሽረ ወዳሉ አካባቢዎች መሸሸታቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አንድ ነዋሪ፣ "መከላከያ ከኋላ አለ፤ የኤርትራ ሰራዊት እና የትግራይ ሰራዊትም ከኤርትራ በኩል አለ። እና ህዝቡ ስጋት ላይ ነው ያለው። በጣም በከባድ ችግር ውስጥ ነው የገባው። ትንሽ እንኳን ሳያርፍ እንደገና ወደ አዲስ መፈናቀል ነው የገባው" ሲሉ ሁኔታውን ገልጸዋል።

"ውጊያ ከሚካሄድበት አካባቢ ወደ ሽሬ የመጡ ተፈናቃዮች አሉ። ወደ አዲ ክልተ ወደ አዲ ነብሪኢድ እና አዲ ዳዕሮ አካባቢ የተፈናቀሉም አሉ። በብዛትም ወደ ሽሬ ይገባሉ" በማለትን ነዋሪዎች የተፈናቀሉባቸውን ስፍራዎች ጠቅሰዋል።

ሌላ ነዋሪም በተመሳሳይ፣ "ከቢያራ፣ ከዓደ ስመሮ፣ ከሓድሽ ዓዲ እንዲሁም ደንበ ገዳሙ ወደተባሉት አካባቢዎች ተመልሶ የነበረው ሕዝብ፣ ከረቡዕ ጀምሮ በእግሩ፣ ባገኘው መጓጓዣ እና በግመል ወደ ዓዲ ሃገራይ፣ ሸራሮ፣ ማዕከላይ አድያቦ እና ታሕታይ አድያቦ እየወጣ ነው" ብለዋል።