ዶናልድ ትራምፕ ወደ አሜሪካ መሰደድን የገደቡባቸው አምስት መንገዶች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

ዶናልድ ትራምፕ አዘውትረው ስለ ስደተኞች ይናገራሉ። ከ11 ዓመት በፊት ለፕሬዝዳንትነት እንደሚወዳደሩ ይፋ ካደረጉበት ቀን አንስቶ እስከ ዛሬም ስደትን ያነሳሉ።

ከ11 ዓመት በፊት ሜክሲኮ አደንዛዥ ዕፅ እና ወንጀለኞች ወደ አሜሪካ እየላከች ነው ብለው ነበር። ዘንድሮም ተመሳሳይ ንግግር ማድረግ ቀጥለዋል።

በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ስደተኞች ላይ ሊወስዷቸው ያሰቧቸው እርምጃዎች በፍርድ ቤት ተቀልብሰዋል። በሁለተኛው የሥልጣን ዘመናቸው ግን በተወሰነ ደረጃ ግባቸውን እያሳኩ ነው።

ኮንግረስ ለስደተኞች ጉዳይ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ እንዲመድብላቸው አድርገዋል። በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ትራምፕ የሚገጥማቸው ተቃውሞ እየተገደበ መጥቷል።

በአጋማሽ ዘመን ምርጫ አነጋጋሪ ከሆኑ ነጥቦች አንዱ የስደተኞች ጉዳይ ነው።

ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ሲመረጡ የአገሪቱን ድንበር እንደሚያጠናክሩ እና ስደተኞችን በጅምላ እንደሚያባርሩ ቃል ገብተዋል። ቃላቸውንም አላጠፉም።

ስደትን በተመለከተ ጠንካራ እርምጃ እንዲወሰድ የመረጡ ድምጽ ሰጪዎችም ሳይቀሩ ፕሬዝዳንቱን እየተቹ ነው። የትራምፕ እርምጃዎች ከልክ በላይ ናቸው ሲሉም ይደመጣሉ።

ትራምፕ በአሜሪካ ስደትን የለወጡባቸውን አምስት መንገዶች እንደሚከተለው እንቃኛለን።

1. አብዛኛውን ድንበር መዝጋት

ጆ ባይደን ፕሬዝዳንት ሳሉ ድንበር ተሻግረው የሚገቡ ሰዎች ቁጥር ተበራክቶ ነበር።

ከአውሮፓውያኑ 2023 እስከ 2024 ድረስ ወደ 4.5 ሚሊዮን ስደተኞች በደቡባዊ ድንበር በኩል ለመሻገር መሞከራቸው ተገልጿል።

ጥገኝነት ጠያቂዎችን በመገደብ እና በሕገ ወጥ መንገድ አሜሪካ የገቡ ስደተኞችን በማባረር ቁጥሩ ሊቀንስ ችሏል።

ትራምፕ የመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ሲገባደድ ድንበር ለመሻገር የሚሞክሩ ስደተኞች ቁጥር ቀንሷል።

ቢቢሲ ድንበር ላይ ወደምትገኘው የቴክሳስ ኤል ፓሶ ከተማ በአውሮፓውያኑ ኅዳር 2025 ተጉዞ ነበር።

በአንድ ወቅት በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ድንኳን ሠርተው የሚያጥለቀልቋቸው ጎዳናዎች ኦና ሆነዋል።

ከተወሰዱት እርምጃዎች መካከል ድንበር ላይ የጥገኝነት ጥያቄዎችን መቀበል መቆሙ ይጠቀሳል። ይህም በድንበር በኩል የተሻገሩ ስደተኞች ወደ አሜሪካ የሚገቡበትን አካሄድ የለወጠ ነው።

አሜሪካ ወደ ድንበር ወታደሮችን ከማሰማራት በተጨማሪ ሜክሲኮ የስደተኞችን ጉዞ እንድትገታ ጫና ማሳደርም ጀምራለች።

የአገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስትር ማርክዌይን ሙሊን በቅርቡ "ፕሬዝዳንት ትራምፕ ድንበርን እንደሚጠብቁ ቃል ገብተዋል፤ አሳክተውታልም። ጠንካራ ቁጥጥር ውጤታማ እንደሆነ ያሳያል" ብለዋል።

2. የድንበር አጥር ግንባታን መፋጠን

ትራምፕ "ትልቅ፣ ቆንጆ ግንብ" ይሉታል። በአሜሪካ እና ሜክሲኮ ድንበር የሚገነባው ግንብ 3,218 ኪሎሜትር ይሸፍናል።

ትራምፕ ከ10 ዓመት በፊት ግንቡን ለመገንባት ቃል መግባታቸው ይታወሳል።

ትራምፕ የግንቡን ግንባታ በሁለተኛው የሥልጣን ዘመናቸው አጠናክረው ቀጥለዋል።

የተመደበው ገንዘብ ወደ 46.5 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ያለ ሲሆን፤ ፕሬዝዳንቱ "አንድ ትልቅ ውብ በጀት" ብለው ይጠሩታል።

የመንግሥት አሐዝ እንደሚያሳየው 644 ማይል የሚሆነው የድንበሩ ግንብ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ሥልጣን ከመያዛቸው አስቀድሞም ነበር።

ተጨማሪ 75 ማይል ግንብ በአሜሪካ ግዛት ባለው የድንበሩ ክፍል ላይ ተገንብቷል።

እስካሁን የተገነባው 250 ማይል ነው። ተጨማሪ 1,443 ማይል እንደሚገነባ ተገልጿል።

ግንቡ ላይ እድሳት ወይም ማሻሻያ ከመደረጉ ባሻገር አዲስ ግንባታ መከናወኑን በተመለከተ እና ስለ ውጤቱ ተንታኞች አስተያየት ይሰጣሉ።

የስደተኞች ጉዳዮች ባለሙያ አሮን ሬይችሊን-ሜልኒክ "አዲሱ ግንብ መገንባት ከተጀመረ ወዲህ ድንበር የሚሻገሩ ስደተኞች ቁጥር ያን ያህል አልቀነሰም" ይላሉ።

ከግንቡ ይልቅ የትራምፕ የስደተኞች ፖሊሲ እና ንግግሮች የስደተኞች ቁጠር እንዲቀንስ ማድረጋቸውን ይገልጻሉ።

ትራምፕ ግን ግንቡ ስኬታማ የፖሊሲ ውጤት ነው ይላሉ። ለግንባታቸው የከፈለችው ሜክሲኮ ናት ሲሉም ይደመጣል።

በአጋማሽ ዘመን ምርጫ ቅስቀሳ ወቅት "የግንቡ ንጉሥ ነኝ፤ ለግንቡ የከፈለችው ደግሞ ሜክሲኮ ናት። ታሪፍ ጥዬባቸዋለሁ፤ ከታሪካቸው ከፍለው የማያውቁት ክፍያ ፈጽመዋል" ብለዋል።

3. ስደተኞችን ማባረር

የአሜሪካ የስደተኞች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን (አይስ) በተለያዩ ከተሞች በመዘዋወር በሕገ ወጥ መንገድ የገቡ ስደተኞችን እየያዘ ማባረሩን ቀጥሏል።

ትራምፕ የምረጡኝ ቅስቀሳ ሲያደርጉ "በአሜሪካ ታሪክ ትልቁ ስደተኞችን የማባረር እርምጃ ይወሰዳል" ሲሉ ነበር።

መጀመሪያ ላይ ዒላማ የሚደረጉት ወንጀል የሠሩ ስደተኞች መሆናቸው ተገልጿል።

ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ሥደተኞችን በቁጥጥር ሥር የማዋል እና ከአገር የማባረር እርምጃ ተጠናክሯል።

በ2026 ሐምሌ ላይ ብቻ 50,000 ስደተኞች መታሰራቸውን የካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ የጥናት ማዕከል 'ዘ ዲፖርቴሽን ዳታ ፕሮጀክት' ያወጣው መረጃ ይጠቁማል።

አብዛኞቹ የታሰሩት ሰዎች ወንጀል የሠሩ እንዳልሆኑም መረጃው ይጠቁማል። እንዲያውም ሐምሌ ላይ ወንጀል የሠሩ ስደተኞችን በቁጥጥር ሥር ማዋል 27% ቀንሷል።

አይስ በቀን በአማካይ የሚያባርራቸው ስደተኞች ቁጥር 1,255 ደርሷል። በባይደን አስተዳደር ሥር ቁጥሩ 770 ነበር።

አይስ ስደተኞችን ለመያዝ የሚጠቀማቸው ስልቶች አሜሪካውያንን ምቾት ነስተዋል። ስደተኞች ላይ እርምጃ መውሰድን የሚደግፉ አሜሪካውያንም ጭምር ትችት ሰንዝረዋል።

በሚኒያፖሊስ አይስ በወሰደው እርምጃ ሁለት አሜሪካውያን መገደላቸው ይታወሳል።

ኒው ዮርክ ታይምስ እና ሲየና ባወጡት መረጃ፤ ዴሞክራቶች ጉዳዩን በተሻለ መንገድ ይይዛሉ የሚሉ መራጮች 50 በመቶ ይሆናሉ።

ሪፐሊካኖች ስደተኞች ላይ የሚወሰድ እርምጃን በመደገፍ ቢታወቁም 46% ያህሉ ብቻ ጉዳዩ የተያዘበትን መንገድ ይቀበላሉ።

ፖለቲኮ እና ፐብሊክ ፈርስት ባወጡት መረጃ፤ አክራሪ ያልሆኑ 31% ሪፐብሊካኖች ስደተኞች ላይ የሚወሰደውን እርምጃ ይነቅሉ። የስደተኞች አያያዝ በሪፐብሊካኖስ መካከል ልዩነት መፍጠሩን ያሳያል።

4. ጥገኝነት ጠያቂዎችን አለመቀበል

ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ሥልጣን እንደያዙ ስደተኞችን መቀበል አቁመዋል።

ስደተኞችን መቀበል የሚጀምሩት ከአሜሪካ ፍላጎት ጋር የሚጣጣም ከሆነ ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል።

ያለፈው ጥር ላይ ትራምፕ የጣሉት እገዳ ለተወሰነ ጊዜ የተነሳው ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን (አፍሪካነርስ) ለመቀበል ነበር።

ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን "ዒላማ እየተደረጉ እና እየተገደሉ ነው" ሲል ዋይት ሀውስ በተደጋጋሚ ቢገልጽም የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ክሱን አስተባብሏል።

በ2026 አሜሪካ የምትቀበላቸው ስደተኞች ቁጥር 7,500 ይሆናል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ወደ 17,500 ከፍ እንዲል ተወስኗል። ለዚህም ምክንያቱ "ያልተጠበቀ የድንገተኛ ጊዜ ክስተት ነው" ተብሏል።

አሜሪካ የምትቀበላቸው ስደተኞች ቁጥር ቀንሷል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው፤ በ2026 አገሪቱ የተቀበለቻቸው ስደተኞች 16,292 ሲሆኑ ከእነዚህ 16,287 የሚደርሱት ደቡብ አፍሪካውያን ናቸው።

በባይደን አስተዳደር የመጨረሻዎቹ ሁለት ዓመታት በ2023፤ 60,000 ስደተኞች በ2024 ደግሞ 100,000 ስደተኞች አሜሪካ ገብተዋል።

አብላጫውን ቁጥር የያዙት የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ አፍጋኒስታን፣ ሶሪያ እና ቬንዝዌላ ስደተኞች ናቸው።

አሜሪካ ለስደተኞች ትሰጠው የነበረው ሰብአዊ ከለላ በስፋት የተነሳው በትራምፕ ሁለተኛው የሥልጣን ዘመን ነው።

ጊዜያዊ ጥበቃ የሚሰጥበት አሠራር (ቲፒኤስ) በተፈጥሮ አደጋዎች፣ በጦርነቶች ወይም በሌሎች ከባድ ክስተቶች ለተጎዱ አገራት ዜጎች የሚቀርብ ከለላ ነው።

በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ከከለላው ውጭ እንዲሆኑ ተደርጓል።

የአሜሪካ የፌደራል ፍርድ ቤት ከ5000 በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ተሰጥቶ የነበረውን በአገሪቱ የመኖር እና የመሥራት መብት ወይም ሕጋዊ ከለላ የትራምፕ አስተዳደር እንዲያቆም መፍቀዱም ይታወሳል።

የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሺህዎች የሚቆጠሩ የሄይቲ እና የሶሪያ ስደተኞች ሕጋዊ ከለላ እንዲያቋርጥ መፍቀዱም አይዘነጋም።

5. የቪዛ ክፍያ መጨመር

ትራምፕ ወደ አሜሪካ መግባት የሚቻልባቸውን ሕጋዊ መንገዶች ጥብቅ አድርገዋል። ይህም በአሜሪካ ለመሥራት እና ለመኖር የሚደረጉ ሙከራዎችን ያካትታል።

የትራምፕ አስተዳደር "የደኅንነት ስጋት" ያላቸው አገራት ላይ የቪዛ እና የጉዞ እቀባ ተደርጓል።

ጠንካራ ፍተሻ ከማድረግ ባሻገር አዳዲስ ሕግጋት በማውጣት ወደ አሜሪካ የሚገቡ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ ተሞክሯል።

በአሜሪካ መኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት የሚጠይቁ ሰዎች ወደ አገራቸው ተመልሰው እንዲጠባበቁ ማድረግ ሌላው እርምጃ ነው።

መስከረም 2025 ላይ ኤች1-ቢ ቪዛ ለማግኘት 100,000 ዶላር መክፈል እንደሚያስፈልግ ተገልጿል። ይህ ቪዛ በብዛት ሕንዳውያን በአሜሪካ ለመሥራት የሚገለገሉበት ነበር።

በዚህ ውሳኔ ምክንያት ቪዛውን የሚጠይቁ ሰዎች ቁጥር 40% ቀንሷል።

የአሜሪካ መንግሥት ባወጣው መግለጫ "ቁጥሩ የሚያሳየው በአነስተኛ የሙያ አቅም የአሜሪካን መርሃ ግብር ለመበዝበዝ የሚደረግ ጥረት ማክተሙን ነው" ብሏል።

መርሃ ግብሩ የተዘረጋው "የላቀ የሙያ ብቃት" ላላቸው የውጭ አገራት ዜጎች መሆኑ ተገልጿል።

ይህም "ከአሜሪካውያን ሥራ የሚቀማ" መሆን እንደሌለበት ተመልክቷል።

ፍርድ ቤት 100,000 ዶላር ክፍያው ላይ እገዳ ቢጥልም ለቪዛው የሚያመልኩ ሰዎች ቁጥር መቀነሱ አልቀረም።

የአሜሪካውያንን የሥራ ዕድል ለመጠበቅ የሚወሰዱ እርምጃዎች ውጤታማነት ላይ ተንታኞች ጥያቄ ያነሳሉ።

ዋሀርቶን ስኩል ኦፍ ቢዝነስ የሠራው ጥናት እንደሚያሳየው፤ ኤች1-ቢ ቪዛ በአሜሪካውያን የሥራ ዕድል ላይ "ጉልህ ጫና" የሚያሳድር አይደለም።

ትራምፕ በሌላ በኩል "ወርቃማ ቪዛ" ይፋ አድርገዋል። 1 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣው ቪዛ ባለ ሃብቶችን ለመሳብ ያለመው ነው። ይህም የአሜሪካን ምጣኔ ሃብት እንደሚያሳድግ ትራምፕ ተናግረዋል።

ለቪዛው የሚያመለክቱ ሰዎች የማይመለስ 15,000 ዶላር ማስያዝ ይጠበቅባቸዋል።