የእስራኤል ተቃዋሚዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ የምርጫውን "ቅቡልነት ለማሳጣት" እየሞከሩ ነው ሲሉ ከሰሱ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የእስራኤል ዋነኛ ተቃዋሚ መሪ ጋዲ አይዘንኮት እና የአረብ መር ፓርቲ መሪዎች ቤኒያሚን ኔታንያሁ ጥምረታቸው አብላጫ ድምፅ አለማሸነፉን ተከትሎ በምርጫው የውጭ ጣልቃ ገብነት አለ ብለው መክሰሳቸውን አወገዙ።

የኔታንያሁ ሊኩድ ፓርቲ የአረብ መሪ ፓርቲዎች ምርጫውን "ሰርቀዋል" ሲል ከስሷል።

የአገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስትር ሺን ቤት ፓርቲዎቹ ሕገ ወጥ የገንዘብ ድጋፍ ከኳታር እና ቱርክ መቀበላቸውን እየመረመሩ ነው።

የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "አስቂኝ እና አደገኛ" ያለውን ክስ ያስተባበለ ሲሆን፤ የእስራኤል ፖለቲከኞች ዶሃ ላይ ሀሰተኛ መረጃ እየነዙ ነው ሲልም ወንጅሏል።

የእስራኤል ምርጫ የመጨረሻ ውጤት የኔታንያሁ ቡድንም ሆነ የአይሁድ ተቃዋሚዎች በፓርላማ አብላጭ ወንበር አለማሸነፋቸውን አረጋግጧል።

ሁለቱ የአረብ ፓርቲዎች 'የጆይንት ሊስት' እና 'ራም' የተሰጣቸውን ግምት አልፈው 120 ወንበሮች ካሉት የእስራኤል ፓርላማ (ክሴኔት) 19 ወንበሮችን አሸንፈዋል። ይህም የአረብ መራጮች በስፋት ድምፅ በመስጠታቸው እንደሆነ ታምኗል።

ፓርቲዎቹ 'መሪ አንጋሽ' ያደረጋቸውን ድምፅ በእጃቸው አስገብተዋል።

የኔታንያሁ ጥምረት 52 መቀመጫዎችን ሲያሸንፍ፤ የተቀናቃኛቸው ጋዲ አይዘንኮት ትብብር ደግሞ 48 ወንበሮችን አሸንፏል።

የእስራኤል ማዕከላዊ የምርጫ ኮሚቴ የውጭ ጣልቃ ገብነትን በሚመለከት ያደረውን "ከባድ ጥርጣሬ" እንዲመረመር የአገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስቴርን ከጠየቀ በኋላ፤ የኔታንያሁ ሊኩድ ፓርቲ መራጮች ለአረብ ፓርቲዎች ድምፅ እንዲሰጡ የእጅ መንሻ ተሰጥቷቸዋል ሲል ከስሷል።

ሁለቱም የአረብ ፓርቲዎች ክሱን ውድቅ አድርገዋል። ትልቁ የአረብ ጥምረት ክሱን መሠረተ ቢስ ብሎታል።

ውዝግቡ በኔታንያሁ ተቺዎች ዘንድ የአረብ ፓርቲዎችን ቅቡልነት ለማሳጣት የተደረገ ሙከራ ተደርጎ ታይቷል። ይህ ክስ የአይዘንኮት ጥምረት ሥልጣን ላይ መውጣት ከፈለገ ብቸኛ አማራጩ የሆነውን ከአርብ ፓርቲዎች ጋር ትብብር መፍጠርን የሚከለክል ነው።

የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን የምርጫ ኮሚቴው፣ ኳታር መራጮች በስፋት ድምፅ እንዲሰጡ ለአረብ ማኅበረሰቦች ገንዘብ አቅርባለች የሚል ክስ እንደቀረበለት ዘግበዋል።

ኔታንያሁ እና ሊኩድ ፓርቲው ክሱን "የፖለቲካ ርዕደ መሬት" እና "ዲሞክራሲ ላይ የተፈፀመ ጥቃት" አድርገው የተመለከቱት ሲሆን፤ የቀኝ ዘመም የሆነውን የእስራኤል መንግሥት ለማባረር ዓላማ ያለው ነው ብለዋል።

የአገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስትር ሺን ቤት በኋላ ላይ ማብራሪያ ሲሰጡ ምርመራቸው በሕጋዊ መንገድ ድምፅ የሰጠን አንድን ማኅበረሰብ በሙሉ እንደማይመለከት ተናግረዋል።

የእስራኤል ማዕከላዊ የምርጫ ኮሚቴ ኃላፊ ዲን ሊቪን "በምርጫ ታማኝነት ላይ ስልታዊ ጥሰት ስለመፈፀሙ ምንም መሠረት የለም" ብለዋል።

ስለምርመራው ማብራሪያ የተሰጣቸው ጋዲ አይዘንኮት ምን እንደተፈጠረ ለመደምደም ጊዜው ገና እንደሆነ ጠቅሰው፤ ኔታኒያሁ የምርጫው ውጤት ቅቡልነት እንዳይኖረው ለማድረግ የተቀናጀ ዘመቻ ከፍተዋል ሲሉ ወቅሰዋል።

አረብ እስራኤሎች ራሳቸውን በእስራኤል የሚኖሩ የፍልስጤም ዜጎች አድርገው የሚያዩ ሲሆን፤ ከእስራኤል ጠቅላላ ሕዝብ አንድ አምስተኛውን ይይዛሉ።