የአውሮፓውያኑ 2026 ከመቼውም ጊዜ በላይ ሞቃታማው ዓመት እንደሚሆን ሳይንቲስቶች ተነበዩ
የዓለም የሙቀት መጠን ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍ ያለበት ዓመት የአውሮፓውያኑ 2026 ሊሆን እንደሚችል ሳይንቲስቶች አስጠንቅቀዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ እና የኤል-ኒኖ ክስተት ለሙቀት መጨመሩ እንደ ምክንያት ተጠቅሰዋል።
ይህ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው የተባበሩት መንግሥታት 31ኛው የአየር ንብረት ጉባኤ (COP31) በቱርክ በተጀመረበት ወቅት ነው።
ትንበያውን ይፋ ያደረገው በአሜሪካ የሚገኘው ገለልተኛው የበርክሌይ ኧርዝ የምርምር ተቋም፣ ዓመቱ ሊያበቃ ሁለት ወራት ቢቀሩትም 2026 እ.ኤ.አ. በ2024 የተመዘገበውን የሙቀት መጠን ክብረወሰን በመስበር ከመቼውም ጊዜ በላይ ሞቃታማው ዓመት እንደሚሆን 95 በመቶ እርግጠኛ መሆኑን ገልጿል።
የሙቀት መጨመሩ ተፅዕኖ በቅርብ ወራት በኮፕ ጉባኤው በሚሳተፉ አገራት ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ታይቷል።
በአውሮፓ ሰፊ የደን ቃጠሎዎች፣ በኔፓል ድንገተኛ የበረዶ ግግር በመደርመሱ ከ1,000 በላይ ሰዎችን ለሞት መዳረጉን ጨምሮ ከባድ ተፅዕኖዎችን አሳይቷል።
የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የሚቲዮሮሎጂ ድርጅት በበኩሉ ባለፈው ሰኞ ይፋ ባደረገው ሪፖርት፣ ከበርክሌይ ኧርዝ ትንበያ የበለጠ ጥንቃቄ የተሞላበት ግምት ቢያቀርብም፣ 2026 ከመቼውም ጊዜ በሙቀት ከፍተኛ ከተመዘገቡት አራት ዓመታት መካከል እንደሚሆን ተንብዮአል።
ድርጅቱ እ.ኤ.አ. በ2027ም የሙቀት መጨመሩ እንደማይቀንስ ገልጿል። ከወትሮው በበለጠ ኃይለኛ የሆነው የኤል-ኒኖ ክስተት ወደሚቀጥለው ዓመት የሚዘልቅ በመሆኑ የዓለም ሙቀት የበለጠ እንደሚጨምር አመልክቷል።