በአሜሪካ ለረጅም ጊዜ ከአከራዩ ጋር አለመግባባት ውስጥ የነበረ ዶክተር የሕንጻውን አስተዳዳሪ ገደለ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኝ የመኖሪያ አፓርታማ ውስጥ በሻጋታ እና ሌሎች ጉዳዮች ከአስተዳዳሪው ጋር አለመግባባት ውስጥ የነበረ አንድ ዶክተር፤ የሕንጻውን አስተዳዳሪ ተኩሶ ሲገድል፣ ሌሎች አራት ሰዎችንም አቁስሎ ራሱን መግደሉን ፖሊስ አስታወቀ።

የ46 ዓመቱ የሕንጻው አስተዳዳሪ ጄምስ ስቱዋርት ጥቃቱ እንደደረሰበት ወዲያውኑ ሕይወቱ ማለፉ የተረጋገጠ ሲሆን፣ ሌሎች አራት ሰዎች ደግሞ ለሕክምና ወደ አካባቢው ሆስፒታሎች ተወስደዋል።

ተኩስ የተከፈተው ሐሙስ ጠዋት ከዋይት ሐውስ በስተሰሜን 1.6 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ላይ በሚገኘው ሎጋን ሰርክል ሰፈር ውስጥ በሚገኝ የመኖሪያ ሕንጻ ውስጥ በሚገኝ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዕከል (ጂም) ውስጥ ነው።

ፖሊስ እንደገለጸው ማት ዋድ ላምበርት የተባለው የ55 ዓመቱ ዶክተር፣ በአንድ አፓርታማ ውስጥ ራሱን ከሸሸገ በኋላ ራሱን አቁስሎ ሕይወቱ አልፏል።

ተጠርጣሪው ራሱን በሕንጻ ውስጥ ከልሎ እያለ "ቢያንስ ሁለት ጊዜ በበሩ በኩል በፖሊሶች ላይ ተኩሷል" ሲሉ የሜትሮፖሊታን ፖሊስ መምሪያ ጊዜያዊ አዛዥ ጄፈሪ ካሮል ተናግረዋል።

ካሮል እንደገለጹት ተደራዳሪዎች ከተጠርጣሪው ጋር በስልክ ሲነጋገሩ የነበሩ ቢሆንም እርሱ ግን የነበረውን የስልክ ንግግር አቋርጧል።

ፖሊሶች ወደ አፓርታማው በኃይል ሲገቡ ተጠርጣሪው "ራሱን ማቁሰሉን" ተመልክተዋል።

ባለሥልጣናት ትክክለኛውን የጊዜ ሰሌዳ፣ የተጠርጣሪውን ምክንያት እና ሌሎች የክስተቱን ዝርዝሮች ለመረዳት ምርመራ እያደረጉ ነው።

ካሮል "በዚህ ጉዳይ የተጠረጠረው ግለሰብ እና በሕንጻው ወይም በኮንዶሚኒየሙ የባለቤቶች ማኅበር አስተዳደር መካከል፤ በጥገና ጉዳዮች እና መሰል ጉዳዮችን በተመለከተ ለረዥም ጊዜ የቆየ አለመግባባት እንደነበር እናውቃለን" ብለዋል።

"እሱ በአስተዳደሩ ላይ የመሠረተው የፍትሐ ብሔር ክስም ነበር፤ ስለዚህ ጉዳዩ ከዚህ ጋር የተያያዘ እንደሆነ እናምናለን።"

ፖሊስ ተጠርጣሪው በስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ውስጥ ተኩስ ከከፈተ በኋላ ከቦታው መሸሹን እና ከዚያም በሕንጻው ሰባተኛ ፎቅ ላይ ከሚገኘው በረንዳ ሆኖ በታችኛው ወለል ላይ የነበሩትን ሌሎች አራት ተጎጂዎች ተኩሶ መምታቱን አስታውቋል።

ከተጎጂዎቹ አንዱ ከባድ ጉዳት እንደደረሰበት ፖሊስ ገልጿል።

ከሌሎች ተጎጂዎች ጋር ግንኙነት ነበረው ወይ የሚለው እስካሁን ድረስ አልታወቀም።

ባለሥልጣናት ከተጠርጣሪው መኖሪያ ቤት ሦስት የጦር መሳሪያዎችን ያገኙ ሲሆን፣ እነዚህንም በሐሙስ ዕለት በተፈጸመው ድርጊት ተጠቅሞባቸዋል።

ካሮል ሲናገሩ፣ "ይህ ድርጊት የተወሰነ ደረጃ ያለው ዝግጅት ወይም ዕቅድ የነበረበት ይመስላል" ብለዋል።

ፖሊስ አክሎም በዋሽንግተን ዲሲ በእሱ ስም የተመዘገበ ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ ስለሌለ፣ መሳሪያዎቹን እንዴት እንዳገኘ ግልጽ አይደለም ብሏል።

በተጨማሪም ተጠርጣሪው በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ተቀጣጣይ ፈሳሽ የያዙ እቃዎች ተገኝተዋል።