'ጦርነትም ሰላምም የሌለባት ትግራይ'፡ በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ጦርነት እውን አብቅቷል?

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

በመቀለ የውበት ሳሎን ላላት ፍሩት መኣር በአሁን ወቅት ደንበኛ መጠበቅ ቅንጦት ነው። "ሰዎች ከዕለት ተዕለት ፍጆታ ተርፏቸው ለውበታቸው አይጨነቁም። ልጆቻቸውን መመገብ ተቸግረው ባሉበት ወቅት ለበርካታ ነዋሪዎች ስለ ራስ ውበት መጨነቅ ቅንጦት ነው" ትላለች።

የ10 ዓመት ሴት ልጅ ላላት ፍሩት፣ መቀለ ከአጭር ጦርነት በኋላ በመከላከያ ቁጥጥር ሥር ብትሆንም፣ ሕይወት ከተለመደው እጅግ የራቀ ነው።

ድምጽዋ በሲቃ እየተቆራረጠ "በርግጥ ነገሮች ጦርነቱ ከነበረበት ጊዜ ይልቅ የተሻሉ ናቸው፤ ነገር ግን ሰዉ ገንዘብ እና ሞራል የለውም። ንግድም ቢሆን አለ ማለት ያዳግታል" ስትል ታክላለች።

ከሁሉም በላይ መጪው ጊዜ ምን ይዞ ይመጣል የሚለው የሁሉም ጭንቀት ነው። "ወደፊት ስለሚሆነው ማንም እርግጠኛ መሆን አይችልም።"

የትግራይ ክልል ግጭት መስከረም 13/2019 ዓ.ም. ዳግም ካገረሸ ከ10 ቀናት በኋላ መስከረም 23 ነበር የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ኃይሎች መዲናዋን መቀለን ለቅቀው የወጡት። በቀጣይ ቀናትም ጥሎ አብዛኛውን የክልሉን አካባቢዎች ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና ለአጋሮቹ ለቅቀው ወጥተዋል።

ህወሓት ከተሞችን ያለ ውጊያ ለቅቆ የወጣው እና ያፈገፈገው ስልታዊ በሆነ ወታደራዊ ውሳኔ ነው ቢልም፣ የፌዴራሉ መንግሥት ግን ጦርነቱን ማሸነፉን ገልጿል። በጦርነቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸው ይነገራል። በርካቶችም በሰው አልባ አውሮፕላን እና በተዋጊ ጄቶች ጥቃት ተገድለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እና ደጋፊዎቹ ጦርነቱ በይፋ ማብቃቱን በመግለጽ የሚቀረው ሥራ በተለያዩ ስፍራዎች ተበትነው የሚገኙ የህወሓት ታጣቂዎች "ማጽዳት" ነው ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፍሪካ ቀንድ አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ በትግራይ የሚካሄደው ጦርነት ማብቃቱን እና ቀጣዩ ቅድሚያ የሚሰጠው ሥራ ክልሉን ማረጋጋት መሆኑን ተናግረዋል።

በአፍሪካ ሰላም እና ደኅንነት ላይ ተንታኝ እና አማካሪ የሆኑት ካሜሮን ሃድሰን ለህወሓት ሽንፈት የተለያዩ ምክንያቶች አሉ ሲሉ ለቢቢሲ አብራርተዋል።

"ህወሓት በአገር ውስጥ ያለውን ሰፊ ድጋፍ አጥቷል፤ ተከፋፍሏል፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን መገዳደር የሚያስችል የላቀ ወታደራዊ ቴክኖሎጂም የለውም" ይላሉ።

"በመክዳት ወይም በመታሰር ምክንያት፤ በርካታ ጄኔራሎችን፣ ስትራቴጂካዊ አሳቢዎችን፣ ብቁ ዲፕሎማቶችን እና ተዋጊዎችን አጥቷል። በህወሓት አመራር ውስጥ የነበረው ውስጣዊ ክፍፍልም ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል።"

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አብርሃ ኃይለዝጊ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ። "ሠራዊቱ ግልጽ የሆነ ፖለቲካዊ ራዕይ የለውም። በቅርብ ዓመታትም ከግፍ፣ ከበደል፣ ከአስገድዶ ምልመላ እና ከዘፈቀደ ድርጊቶች ጋር ስሙ ተያይዟል። በዚህም ምክንያት፣ ብዙ ሰዎች የህወሓት ታጣቂዎችን ለጥቃታቸው የሚቆም ኃይል አድርገው ከመመልከት ይልቅ እንደ ጠላት ማየት ጀምረዋል" ይላሉ።

የህወሓት ቃል አቀባይ ሚካኤል አስገዶም፣ ካልታወቀ ስፍራ ሆነው በስልክ ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ ቡድኑ መሸነፉን ያስተባብላሉ።

ይልቁንም ይህ ሆን ተብሎ የተደረገ ስልታዊ እና ስትራቴጂካዊ ማፈግፈግ መሆኑን በመግለጽ "ይህ ሽንፈት አይደለም" ብለዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት ህወሓት "የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወደ ትግራይ ዘልቆ እንዲገባ ሆን ብሎ አድርጓል"። ይህም ሠራዊቱን ከሌሎች ኃይሎች ለይቶ ማጥቃት በሚያስችልና ለህወሓት ምቹ በሆነ የጦር ሜዳ ላይ ለመጋፈጥ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

"ለጠላት በሚጠቅም ሁኔታ መዋጋትን አልፈለግንም።"

ህወሓት ለግዙፍ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ እየተዘጋጀ መሆኑንም ተናግረው፤ በተጨማሪም የህወሓት ታጣቂዎች ከክልሉ ከተሞች ከወጡ በኋላ በተለያዩ ቦታዎች በኢትዮጵያ ጦር ላይ ጥቃቶችን መፈጸማቸውን ገልጸዋል። እነዚህ ዘመቻዎችም ቡድኑ አሁንም የወታደራዊ አቅሙን እንደያዘ ያሳያሉ ሲሉ ይከራከራሉ።

ከትግራይ የተረጋገጠ መረጃ ማግኘት አስቸጋሪ ሲሆን፣ ቢቢሲም በክልሉ ተገኝቶ በቀጥታ ዘገባዎቹን መስራት አልቻለም። ይሁን እንጂ ግጭቱ በተጀመረበት ወቅት የተቋረጡት የስልክ መስመሮችና የኢንተርኔት አገልግሎት አሁን ተመልሰዋል።

በትግራይ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ በማዕከላዊ፣ በሰሜናዊና በሰሜን ምዕራባዊ ትግራይ ግጭቶች እንደቀጠሉ ናቸው። በግጭቶቹም ከባድ መሣሪያዎች እና ድሮኖች ጥቅም ላይ ውለዋል።

ከኤርትራ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ሸራሮ ከተማና አካባቢዋ የሚገኙ የዐይን እማኞችም በቅርብ ቀናት በመድፍና በምድር ጦር ኃይሎች የታገዘ ከባድ ውጊያ መካሄዱን ተናግረዋል።

ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ አንድ ነጋዴ "ከሸራሮ አቅጣጫ ከባድ የመድፍ ተኩስ እንሰማ ነበር። የደኅንነት ስሜት ስለሌለ ሰዎች ተጨንቀዋል" ሲል ተናግሯል።

ነጋዴው ከሁለቱም በኩል ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ወደ ሸራሮ አቅጣጫ መጓዛቸውን ጨምሮ ተናግሯል። በደቡባዊቷ የጭላ ከተማ የሚገኝ አንድ የሞተር ሳይክል አሽከርካሪ በበኩሉ፣ ወታደራዊ የፍተሻ ኬላዎች አሁንም መኖራቸውን ለቢቢሲ ገልጿል።

በትግራይ ነዋሪዎች ለሁለት ዓመት የተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ትውስታ አሁንም ትኩስ ነው።

በወቅቱ ግጭቱ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ በምዕራብ ትግራይ ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃት ተመዝግቦበታል።

በጦርነቱ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሞቱም ይገመታል።

ከዚህ ቀደም በነበረው ጦርነት የተለያዩ ወንጀሎችን መፈጸማቸው የሚነገርላቸው የኤርትራ ወታደሮች እንዲሁም የኢትዮጵያ ወታደሮች በትግራይ ከተሞች ላይ ሲታዩ ነዋሪዎች ለመርሳት የሚታገሉትን ትውስታ ዳግም የሚቀሰቅስ እና ፍርሃት የሚለቅ ስሜት እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ።

ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ቅርብ የሆኑ ወታደራዊ ምንጮች በህወሓት ላይ የሚወሰደው እርምጃ እንደቀጠለ መሆኑን ገልጸዋል። በሰሜን ለኤርትራ ድንበር ቅርብ በሆኑ ከተሞች እና በማዕከላዊ ትግራይ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ይታያሉ። የህወሓት ተዋጊዎች አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ መሆኑን እነዚህ ምንጮች ጨምረው ተናግረዋል።

የደኅንነት ተንታኞች እና ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ሰዎች ለተወሰነ ጊዜ አለመረጋጋቱ ሊቀጥል እንደሚችል ይስማማሉ።

"በትግራይ ለረዥም ጊዜ ሊቆይ የሚችል ጦርነት ሊኖር የሚችልበት ሁኔታ ይታየኛል" ሲሉ በአሜሪካ የሚኖሩት እና በክልሉ የሚካሄደውን ግጭት በቅርበት የሚከታተሉት ያሬድ ጥበቡ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ያሬድ ህወሓት ለረዥም ጊዜ የሚዘልቁ የትጥቅ ትግሎችን የማካሄድ ታሪክ እንዳለው በመጥቀስ፣ ቡድኑ አሁንም ለተራዘመ ግጭት እየተዘጋጀ ነው ብለው ያምናሉ።

ቡድኑ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ መዋቅሮቹን እንደገና ካደራጀ በኋላ፣ ጥቃቶችን ለመጀመር ሊሞክር እንደሚችልም ይገምታሉ።

ሆኖም በውስጣዊ ክፍፍሎች ምክንያት ይህ ወዲያውኑ ላይሆን እንደሚችል ቢጠቅሱም የህወሓት ቃል አቀባይ ሚካኤል ግን ውድቅ አድርገውታል።

ሃድሰን ትግራይ ወደ ተራዘመ ጦርነት እያመራች ነው የሚለውን ሀሳብ ውድቅ አድርገው ክልሉ ለተወሰነ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ሰላም ላያገኝ እንደሚችል ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።

"ህወሓት ዝቅተኛ ደረጃ ያለው አመጽ እና የሽምቅ ውጊያ ዘመቻ ሊቀጥል ይችላል፤ ነገር ግን ይህ ጦርነት አይደለም። በፌዴራል ኃይሎች እና በህወሓት መካከል ሰፊ ግጭት ይፈጠራል ብዬ አላስብም።"

በቅርብ ዓመታት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመሩ የመጡትን እና ዘመናዊ የሆኑትን የፌዴራል ኃይሎች የጦር መሣሪያዎች፣ ህወሓት በብቃት ለመመከት የሚያስችል በቂ ቁጥር፣ ጥንካሬ ወይም ወታደራዊ አቅም እንደሌለውም ይገልጻሉ።

"ህወሓት ከሕዝብ ያገኘውን ድጋፍ በከፍተኛ ሁኔታ አጥቷል፤ እንዲሁም አዳዲስ አባላትን በመመልመል አሰላለፉን በቀላሉ መልሶ ማደራጀት አይችልም" ሲሉ ይናገራሉ።

ያሬድ ደግሞ ህወሓት ከዚህ ቀደም ያጋጠሙትን መሰናክሎች በማለፍ ያሳየውን ታሪክ በመጥቀስ፣ ቡድኑ እንደገና ተደራጅቶ ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ትግል ማድረግ እንደሚችል ይከራከራሉ።

"ህወሓት ከዚህ በፊት ብዙ ትላልቅ ተግዳሮቶችን አልፏል። ከሕዝብ ምንም ዓይነት ድጋፍ የለውም ብሎ መደምደም ስህተት ነው። ይህ ከ50 ዓመታት በላይ ታሪክ ያለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ነው፣" ይላሉ።

ያሬድ እንደ ጥንካሬ የሚመለከቱትን ሃድሰን እንደ ድክመት ይቆጥሩታል።

ህወሓት "በኋላ ታሪክ ተተብትቦ ተይዟል" የሚሉት ሃድሰን አሁንም በትግራይ ገዢው ፓርቲ እንደሆነ ያስባል በማለት ሁኔታዎች መቀየራቸውን ይጠቅሳሉ።

"ምንም ያልተለወጠ፣ ራሱን ያላዘመነ ወይም ያላሰፋ እንቅስቃሴ ነው"

ሃድሰን ህወሓት መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ለማካሄድ የሚያስችል ዘመናዊ ጦር መሣሪያ አልታጠቀም ብለው ሲከራከሩ ቃል አቀባዩ ግን ቡድናቸው ወታደራዊ ቁሳቁሶችን እና መሣሪያዎችን የሚያገኘው ከጦሩ በመማረክ መሆኑን ይናገራሉ።

"ከጠላታችን መሣሪያዎችን ማርከናል። ወደ ትግራይ የገባ ጦር መሣሪያ ይፍጠንም ይዘግይ የእኛ ይሆናል።"

በመስከረም ወር መጨረሻ አካባቢ የዐይን እማኞች በትግራይ አንዳንድ ከተሞች የኤርትራ ወታደሮችን ማየታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ነገር ግን ወታደሮቹ ወደ ድንበራቸው የሄዱ ሲሆን ሃድሰን ኤርትራ በዚህ ጦርነት ውስጥ እንዳትዘፈቅ መፍራቷ አይቀርም ይላሉ።

"በመጀመሪያ፣ ኤርትራ ያልተገደበ ሀብት የላትም። በሁለተኛ ደረጃ ህወሓት ከአሁን በኋላ ውጤታማ ወታደራዊ ኃይል አይደለም፤ የኤርትራ መሪዎችም በዚህ ወቅት ለህወሓት ድጋፍ መስጠት ትርጉም ያለው ወታደራዊ ጥቅም እንደማያስገኝ ደምድመው ሊሆን ይችላል፣" ይላሉ።

"በሦስተኛ ደረጃ፣ ኤርትራ ህወሓትን በግልጽ የምትደግፍ ከሆነ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ግጭት የመፍጠር አደጋን ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባታል።"

በኢትዮጵያ መከላከያ ውስጥ ያሉ ምንጮች ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ የህወሓት ከፍተኛ የፖለቲካ አመራር አባላት ለተወሰነ ጊዜ ኤርትራ ውስጥ ቆይተው ነበር።

ነገር ግን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከሩሲያ ከተመለሱ በኋላ፣ በኅዳር ወር መጀመሪያ ላይ የኤርትራ ባለሥልጣናት ከአገሪቱ እንዲወጡ አዘዋቸዋል።

ምንጮቹ እንደሚሉት፣ ይህ እርምጃ የተወሰደው ኢትዮጵያ የእነሱን መኖር እንደ ምክንያት በመጠቀም ወረራ ልትፈጽም ትችላለች ከሚል ስጋት በመነሳት ነው።

ሃድሰን በተጨማሪም፣ ኤርትራ ከአሜሪካ ጋር ያደሰችው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አሜሪካ ከህወሓት ጋር የነበራት ግንኙነት ለረዥም ጊዜ የሻከረ መሆኑን ከግምት በማስገባት፣ አሥመራ ለህወሓት ጉልህ ድጋፍ እንዳትሰጥ ሊያደርጋት እንደሚችል ይከራከራሉ።

በመስከረም ወር፣ በህወሓት የሚመሩ ሰባት የኢትዮጵያ አማጺ ቡድኖች፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን መንግሥት ለማስወገድ ያለመ "ጥምረት ለኅልውና" የተሰኘ አዲስ ቡድን መመስረታቸውን አስታውቀው ነበር።

ያሬድ ይህ ጥምረት ለህወሓት ትግሉን ለመቀጠል የሚያስችል አቅም ሊሰጠው እንደሚችል ያምናሉ። "አባላቱ ጥንካሬያቸውን ማዋሃድ ይችላሉ። የትግራይ ኃይሎች የህወሓት ወታደራዊ ክንፍ የአመራር ልምድ እና ድርጅታዊ አቅም አለው፤ በሌላ በኩል ፋኖ (የአማራ ሚሊሻ ቡድን) ከ70,000 እስከ 80,000 የሚገመቱ ታጣቂዎች እንዳሉት ይታመናል።"

"እነዚህ ኃይሎች በብቃት ተቀናጅተው እንዲሰሩ የሚያስችሉ ሁኔታዎች ከተፈጠሩ፣ የህወሓት አሁን ያሉበት ችግሮች ለረዥም ጊዜ ላይቆዩ ይችላሉ፣" ሲል ተስፋውን ይናገራል።

በሌላ በኩል ሃድሰን ይህንን መከራከሪያ ውድቅ ያደርጋሉ። ጥምረቱ የኃይል ሚዛኑን የመቀየር ዕድሉ አነስተኛ እንደሆነም በመግለጽ "በዚህ ጥምረት ህወሓት ያንሰራራል ብዬ አላስብም። የብሔር ሚሊሻዎች፣ ለብቻቸውም ሆነ በጋራ፣ ለፌዴራል ኃይሎች ከባድ ስጋት የመፍጠር አቅም እንዳላቸው አላሳዩም። የፌዴራል ጦርን ጥንካሬ አሳንሰን መመልከት የለብንም" ብለዋል።

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲው አብርሃ በበኩላቸው በትግራይ ያለው ግጭት በእውነት የሚያበቃው ፌዴራል መንግሥቱ ለክልሉ ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጥ ብቻ እንደሆነ ይከራከራሉ። ክልሉ በአሁኑ መንግሥት በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲካ ረገድ ተገልያለሁ የሚል ስሜት አለው።

ሆኖም፣ ብዙ የትግራይ ምሁራን እና የፖለቲካ ታዛቢዎች በፌዴራል መንግሥቱ ዓላማ ላይ ጥርጣሬ አላቸው። በአዲስ አበባ የሚገኙት ባለሥልጣናት የትግራይን ችግሮች ለመፍታት በቅንነት እየሰሩ ነው ወይስ የክልሉን ድክመት በመጠቀም ተጽዕኖአቸውን ለማስፋት እየሞከሩ ነው? የሚለውን ጥያቄ ያነሳሉ።

በሌላ በኩል፣ በትግራይ የሚገኙ ብዙ ተራ ሰዎች ቅድሚያ የሚሰጡት ለሰላም እንደሆነ ይናገራሉ።

በመቀሌ የውበት ሳሎን ባለቤት የሆነችው ፍሩት "ሰላም ለመምጣት የዘገየ ይመስላል። አብዛኛው ሰው ፖለቲካ ሰልችቶታል። ምንም ይሁን ምን፣ እኛ የምንፈልገው ሰላምን እና ሕይወታችንን መልሰን ለመገንባት የሚያስችል ዐዕድል ብቻ ነው" ትላለች።