ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ያለ ኢንተርኔት ጭምር ሐኪምና ሕሙማንን በማገናኘት ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኘችው በአምላክ
በኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ለማግኘት ታካሚዎች ረዥም ርቀት ከመጓዝ አንስቶ በሆስፒታሎች ለረዥም ጊዜ ወረፋ እስከመጠበቅ የሚደርሱ ተግዳሮቶች ያጋጥሟቸዋል።
በተለይም በገጠር የሚኖሩና በአቅራቢያቸው የጤና ተቋም ወይም የሕክምና ባለሙያ ማግኘት የማይችሉ ሰዎች ችግሩን በእጅጉ ይጋራሉ።
እነዚህን ችግሮች በቀጥታ በሙያዋ የተመለከተችው በአምላክ ዓለማየሁ፣ የጤና አገልግሎትን በቴክኖሎጂ በማዘመን ለሰዎች ተደራሽ ለማድረግ መነሳቷን ትናገራለች። እንደ አውሮጳውያኑ በ2022 የመሠረተችው 'መድኃኒት ዲጂታል ኸልዝ' የተሰኘው ድርጅትም የዚሁ ጥረት ውጤት ነው።
በዚሁ ስራዋም በጤና እና በማኅበራዊ ዘርፎች ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጡ ፈጠራዎችን ለሚያበለጽጉ ሴት ሥራ ፈጣሪዎች እውቅና የሚሰጠው ባየር ፋውንዴሽን የሴት ሥራ ፈጣሪዎች ሽልማት አሸናፊ ሆናለች።
በአምላክ ከዓለም ዙሪያ ካመለከቱ 2ሺህ ገደማ ከሚደርሱ ሰዎች መካከል፣ ከአፍሪካ፣ ከእስያና ከላቲን አሜሪካ ከተመረጡ 15 አሸናፊዎች አንዷ በመሆን ነው የ25ሺህ ዶላር ሽልማት የተበረከተላት።
በአምላክ ዓለማየሁ በአውሮጳውያኑ 2021 በክሊኒካል ነርሲንግ ተመርቃለች። በተጨማሪም በሶሻል ወርክ ሌላ ዲግሪ ይዛለች። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በለንደን ስኩል ኦፍ ቢዝነስ ኤንድ ፋይናንስ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቷን እየተከታተለች ነው።
ሆስፒታሎች ውስጥ በነርስነት ሙያዋ በምትሰራበት ወቅት ታካሚዎች ሕክምና ለማግኘት የሚያሳልፉትን እንግልት በየቀኑ መመልከቷ ለመድኃኒት ዲጂተል ኸልዝ መመስረት ምክንያት እንደሆነ ትናገራለች።
በአቅራቢያቸው የጤና አገልግሎት ባለማግኘታቸው ወይም በአፋጣኝ የሕክምና ባለሙያ ማማከር ባለመቻላቸው የጤና ችግራቸው ወደ ተወሳሰበ ደረጃ የሚደርስባቸውም አሉ ትላለች።
መድኃኒት እና ምርመራ እንዲያደርጉ ከታዘዘላቸው በኋላ አገልግሎቶቹን ለማግኘት ረጅም ጊዜ ይፈጅባቸዋል የምትለው በአምላክ፣ በተለይም ለምርመራና ለሪፈራል አገልግሎት ታካሚዎችን ይዘው በትራንስፖርት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ሲያንከራትቱ ማየት የተለመደ መሆኑን ትገልጻለች።
ይህንን እንግልት መመልከቷ "መድኃኒትን" መፍትሄ ለምድረግ እንዳነሳሳት ታስረዳለች።
በተጨማሪም ቀደም ሲል በሕክምና ቱሪዝም ዘርፍ በሠራችበት ወቅት ወደ ሕንድ፣ ቱርክና ዱባይ ባደረገቻቸው የሕክምና ጉዞዎች እነዚህ ችግሮች በሞባይል መተግበሪያዎች፣ በስልክ ጥሪ እና በሌሎች ዲጂታል አማራጮች ሲፈቱ መመልከቷ በኢትዮጵያም ተመሳሳይ መፍትሔ ለመተግበር አነሳስቷታል።
በዚህም መሠረት የመድኃኒት ዲጂታል ኸልዝ ፕላትፎርም በማቋቋም የጤና አገልግሎትን በቴክኖሎጂ ለማዘመን ሥራ ጀመረች።
መድኃኒት በሞባይል አፕሊኬሽን፣ በድረ ገጽ እና በአጭር የስልክ መስመር አማራጭ አገልግሎት የሚያቀርብ ሲሆን፣ ዘመናዊ ስልክም ሆነ የበይነ መረብ አገልግሎት የሌላቸው ሰዎችም በስልክ ጥሪ አገልግሎቱን ማግኘት እንዲችሉ አድርጓል።
ፕላትፎርሙ የኦንላይን ህክምና፣ የሐኪም ቀጠሮ ማስያዝ፣ የመድኃኒት ማድረስ፣ የአእምሮ ጤና ምክክር እንዲሁም የጤና አገልግሎት የሚገኙባቸውን ቦታዎች ማመላከትን በአንድ ሥርዓት ያካተተ ነው።
በየኦንላይን ሕክምና (ቴሌሜዲስን) አገልግሎቱ ሰዎች ካሉበት ቦታ ሆነው ከሕክምና ባለሙያዎች ጋር መመካከር ይችላሉ። ይህም በተለይ በገጠር የሚኖሩና ሕክምና ለማግኘት ረጅም ሰዓታት መጓዝ የሚጠበቅባቸውን ሰዎች ችግር ለመቅረፍ ያለመ ነው።
በመድኃኒት ማደረስ ደግሞ ታካሚዎች የሐኪም ማዘዣቸውን በፕላትፎርሙ ላይ በመጫን ወይም በስልክ በመደወል የታዘዘላቸውን መድኃኒት ማግኘትም እንደሚያስችል ነው በአምላክ የምትገልጸው።
በሐኪም ቀጠሮ ማስያዣ አገልግሎቱ ከ500 በላይ ስፔሻሊስት ሐኪሞች እንደሚገኙ በአምላክ ትናገራለች።
ከአጋር ሆስፒታሎች ጋር በመተባበር ታካሚዎች በሕክምና ባለሙያ ለመታየት ሰዓታትን፣ ቀናትን እና ወራትን ከመጠበቅ ይልቅ በአቅራቢያቸው ባለ የጤና ተቋም ሐኪምና የቀጠሮ ሰዓት መርጠው አገልግሎት እንዲያገኙ ያመቻቻል ተብሏል።
በአእምሮ ጤና ዘርፍም ከ17 በላይ የአእምሮ ጤና እንክብካቤ ባለሙያዎችን በማሳተፍ የኦን ላየን አገልግሎትም ይሰጣል።
"አሁን ላይ ከ300 ሺህ በላይ ሰዎች በአራቱም አገልግሎቶች ተጠቃሚ አድርገናል" የምትለው በአምላክ በየዕለቱም ሰዎች የሕክምና እና የአእምሮ ጤና ምክክር ለማግኘት በስልክ ይደውላሉ።
አገልግሎቱ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከአገር ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ቋንቋና ባህልን ያገናዘበ የአእምሮ ጤና እንክብካቤ ለማግኘት ከኢትዮጵያውያን የአእምሮ ጤና ባለሙያዎች ጋር በኦንላየን አገልግሎት እንዲያገኙ ዕድል መፍጠሩን ትገልጻለች።
ይህ የሥራ ውጤት ዓለም አቀፍ እውቅናም አስገኝቷል። ከተቋቋመ ከ100 ዓመታት በላይ ያለፉት ባየር ፋውንዴሽን በ2026 በጤና እና በአየር ንብረት ለውጥ ዘርፎች ፈጠራዊ መፍትሔዎችን ለሚያቀርቡ ሴት ስራ ፈጣሪዎች ባዘጋጀው የሽልማት ውድድር መድኃኒት ተሳትፎ አሸንፏል።
በውድድሩ ወደ 2ሺህ ገደማ አመልካቾች የተሳተፉ ሲሆን፣ በተለያዩ የውድድር ሂደቶች እና ግምገማዎች አልፈው ለየዘርፉ ባለሙያዎች ሥራቸውን ካቀረቡ በኋላ ማሸነፋቸውን ትናገራለች።
ይህ እውቅና ከሽልማት ባለፈ ለድርጅቱ በርካታ ዕድሎችን ከፍቷል። ዓለም አቀፍ ታዋቂነትን ከማስገኘቱ በተጨማሪ በኢንቨስትመንት እና በአጋርነት ሥራዎች አዳዲስ ዕድሎችን ፈጥሯል።
በተለይም ከባየር ፋርማሲዩቲካልስ ጋር በመተባበር በእናቶችና በሕፃናት ጤና ላይ በማተኮር በገጠር የሚኖሩ ማኅበረሰቦች የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል የገጠር ተደራሽነት ሥራ ለመሥራት ዕድል እንደተፈጠረላቸው ትገልጻለች።
ከዚህ ባለፈም ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በአካል ተገናኝተው ሥራቸውን እንዲያቀርቡ ዕድል ተመቻችቷል። ለድርጅቱም 25 ሺህ ዶላር የገንዘብ ሽልማት ተሰጥቷል።
ከገንዘብ ድጋፉ በተጨማሪ ድርጅቱ የሥራ ስትራቴጂውን ለማሻሻል፣ ኢንቨስትመንት ለማግኘት እና የአገልግሎቱን ተደራሽነት ለማስፋት የሚያግዙ ቴክኒካዊ ድጋፎችን እና ሥልጠናዎችን እያገኘ ነው።
ድርጅቱ የሴቶችን ተሳትፎ እና አቅም ለማጎልበትም ትኩረት መስጠቱን የምትናገረው በአምላክ በአሁኑ ወቅት 22 ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ አብዛኞቹ ሴቶች ናቸው።
በአገሪቱ በሕክምናም ሆነ በቴክኒክ ዘርፎች ብቃት ያላቸው ሴቶች እንዳሉ የምትገልጸው በአምላክ፣ "እኔ አጥቼ የነበረውን ዕድል ለሌሎች ማመቻቸት እፈልጋለሁ" ትላለች።
"አንድም ሰው ቢሆን ሕክምና አገልግሎት ሊያገኝ በሚገባው ሰዓት ባለማግኘቱ ሕይወቱ እንዳያልፍ ማድረግ ነው ህልሜ። ያንን ማድረግ ከቻልኩ የሕይወቴ ትልቁ ስኬት ይሆናል"ትላለች።
በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የኢትዮጵያን ከግማሽ በላይ ሕዝብ ማገልገል የድርጅቱ ትልቅ ዓላማ እንደሆነ በአምላክ ትናገራለች። በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ደግሞ ቋንቋ፣ የዲጂታል እውቀት ወይም የገንዘብ አቅም ሳይገድበው በመላ ኢትዮጵያ ዘመናዊ የዲጂታል ጤና አገልግሎት ማዳረስ እንደምትፈልግ ትገልጻለች።
"የአዲስ አበባ ላይ ያለ ሐኪም ትግራይ ላይ ያለችን እናት፣ ኦሮሚያ ላይ ያለን ገበሬ ሕክምና መስጠት የሚችልበትን ተደራሽነት ማምጣት ነው" ስትል የረጅም ጊዜ ራዕይዋን ታስረዳለች።
ድርጅቱ ከኢትዮጵያ ባለፈም ወደ ዛምቢያ እና ሩዋንዳ የማስፋፋት ሥራዎችን እንደጀመረ እና በተጨማሪም በቅርቡ በተገኙ ዕድሎች መሠረት ወደ ካናዳ እና አሜሪካ ለመስፋፋት እና ዓለም አቀፍ የዲጂታል ጤና ፕላትፎርም ለመሆን እየሠራ እንደሚገኝ በአምላክ ትገልጻለች።