"ስድስት ዓመት የጠበቅነው ዘጠኝ ዓመት መፍጀቱ ያማል"፦ ጦርነቱን አልፈው በመቀለ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡት ዶክተሮች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

መቀለ ዩኒቨርሲቲ ጥቅምት 14፣ 2019 ዓ. ም. ለ17ኛ ዙር ካስመረቃቸው የሕክምና ዶክተሮች ውስጥ ሦስት ሴቶች በተከታታይ ከፍተኛ ውጤት አምጥተዋል።

ዶክተር መብርሂት ግርማይ 3.92 አጠቃላይ አማካይ ውጤት በማስመዝገብ የዩኒቨርሲቲውን የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከፍተኛ ውጤት ይዛለች። ዶክተር ኤደን ወርቅነህ 3.90፣ ዶክተር እመቤት በሪሁ ደግሞ 3.77 አስመዝግበዋል።

ሦስቱ ዶክተሮች ይህን ውጤት ያስመዘገቡት ከ2013 ዓ. ም. ጀምሮ ለሁለት ዓመታት ገደማ በጦርነት ትርምስ ውስጥ ከነበረችው መቀለ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው በግጭቱ ምክንያት ለሦስት ዓመታት ትምህርት መስጠት አቁሞ ነበር።

በወቅቱ በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና የትግራይ ጦርነት ምክንያት በመደበኛው ስድስት ዓመት ከግማሽ የሚወስደውን የሕክምና ትምህርት ለዘጠኝ ዓመታት እንዲከታተሉ ተገድደዋል።

የሦስቱም ትውውቅ የጀመረው ከ14 ዓመት በፊት መቀለ በሚገኘው ቀላሚኖ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ነበር።

ትምህርት ቤቱ ከመላው ትግራይ ክልል ተመርጠው የሚመጡ፣ በስምንተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችን አስፈትኖ ይቀበላል።

ዶክተር መብርሂት ከመቀለ፣ ዶክተር ኤደን ከአክሱም እና ዶክተር እመቤት ደግሞ ከአድዋ ነበር የተሰባሰቡት።

በዚያም ለአራት ዓመታት እስከ 12ኛ ክፍል ተምረው፣ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ወደ መቀለ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ለማጥናት ገብተዋል።

2010 ዓ. ም. የጤና ሳይንስ ኮሌጁን የተቀላቀሉት ተመራቂዎቹ የ4ኛ ዓመት ተማሪ እያሉ ጦርነቱ መቀስቀሱን አስታውሰው፤ ለሦስት ዓመታት ያህል ትምህርት አቋርጠው እንደነበር ተናግረዋል።

ዶክተር መብርሂት የሕክምና ትምህርታቸውን ለማጠናቀቅ የፈጀባቸው ጊዜ ከታቀደው በላይ መራዘሙ እንዳሳዘናቸው ትናገራለች። ዶክተር መብርሂት "ስድስት ዓመት የጠበቅነው 9 ዓመት መፍጀቱ ያማል" ትላለች።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት ለወራት ከተቋረጠ በኋላ ይቀጥላሉ ብለው በጠበቁበት ወቅት የትግራይ ጦርነት መቀስቀሱን የምታስታውሰው መብርሂት "ያለ መብራት፣ ኢንተርኔት እና ደኅንነት በሌለበት ቦታ መቀመጥ ከባድ ነበር" ስትል በጦርነቱ ወቅት የነበረውን አስቸጋሪ ሁኔታ ትገልጻለች።

በተለይም በ2013 እና 2014 ዓ. ም. በሕይወት ስለመቆየት ብቻ እያሰበች እንደነበር ትናገራለች።

ሁለተኛ ከፍተኛውን ውጤት ያመጣችው ዶክተር ኤደን፣ ወላጆቻቸው በክልሉ የተለያዩ ጦርነቶችን አሳልፈው የሚያውቁ ቢሆንም፣ ለእነርሱ ግን ጦርነቱ አዲስ እና ያልተጠበቀ ተሞክሮ እንደነበር ታስታውሳለች።

"አንዱ አሸናፊ አንዱ ተሸናፊ ሆኖ የሚያልቅ ነበር የሚመስለን፤ ነገር ግን ሁኔታው ሲቆይ በሥነ ልቦና እና ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ነበረው" በማለት የጦርነቱ ለረዥም ጊዜ መዝለቅ በሕይወታቸው ላይ ያሳደረውን ጫና ታስረዳለች።

"እኛ ያሰብነው እና የተገኘንበት ሁኔታ ለየቅል ነው" ትላለች።

ሦስተኛውን ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችው እመቤትም ትምህርት ባቋረጡበት ወቅት ከቤተሰቦቿ ጋር አገሯ አድዋ ተመልሳ እንደነበር ትገልጻለች።

በወቅቱ የነበረው አስቸጋሪ ሁኔታ ለከፍተኛ ጭንቀት እንደዳረጋትም ትናገራለች። ከነበረችበት ጭንቀት ለመውጣት በማሰብም በሆስፒታሎች ነጻ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት እንደተነሳሳች ትገልጻለች።

በዚያ ወቅት በጦርነቱ ምክንያት የተጎጂዎች ቁጥር እየጨመረ ነበር። ብዙ ሆስፒታሎች በቂ የሰው ኃይል እጥረት አጋጥሟቸው እንደነበር ተመራቂዎቹ ያስረዳሉ።

ለሆስፒታሉ የሕክምና ተማሪዎች መሆናቸውን እና በፈቃደኝነት ለመሥራት እንደሚፈልጉ የሚገልጽ ደብዳቤ አቅርበው ፈቃድ ጠየቁ። በመቀለ፣ አክሱም እና አድዋ የሚገኙት ሆስፒታሎቹም ተቀበላቸው።

መቀለ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለተጠለሉ ተፈናቃዮች የሕክምና አገልግሎት በመስጠት የጀመረችው መብርሂት በወቅቱ የታካሚዎች ቁጥር እና ያለው የሕክምና ባለሙያ ብዛት እንደማይመጣጠን ትገልጻለች።

በዚህም ምክንያት በአጠቃላይ ሐኪሞች እና በስፔሻሊስቶች ብቻ ታካሚዎችን ማከም አዳጋች በመሆኑ የአራተኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አሠልጥኖ ወደ ሥራ ማስገባት የተሻለው አማራጭ እንደነበር ታነሳለች።

ለሕፃናት የአልሚ ምግብ እጥረት ምርመራ እንዲሁም የደም ግፊት ላለባቸው ታካሚዎች የክትትል አገልግሎት ይሰጡ እንደነበር ትናገራለች።

በዚያ ወቅት ባላቸው ውስን እውቀት እና አቅም እንኳን ለሰዎች ጠቃሚ መሆን እንደቻሉ መመልከታቸው፤ በቀጣይ የበለጠ እውቀት እና ክህሎት ቢያገኙ የተሻለ ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ እንዲያስቡ አድርጓቸዋል።

በመጀመሪያ የሚከናወኑ የሕክምና ሒደቶችን እና ቀላል የሕክምና ተግባራትን ከመመልከት እንደጀመሩ የሚገልጹት ተመራቂዎቹ፤ ከዚያም እያንዳንዱ ተግባር ለምን እና እንዴት እንደሚፈጸም መረዳት፣ ቀጥሎም በባለሙያዎች እገዛ ሕክምና መስጠት እንደጀመሩ ይናገራሉ።

ከታካሚዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት፣ የሕክምና ታሪክ አወሳሰድ እና የታካሚዎችን ሁኔታ የመረዳት ክህሎት እንዳዳበሩ ይገልጻሉ።

ዶክተር ኤደን በአንድ ወቅት የነበረውን የጦርነት ጫና አሁን ሲያስቡት እንደ ትልቅ የመማሪያ ዕድል እንደወሰዱት ትናገራለች።

በግጭቱ ምክንያት በትግራይ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ተማሪዎች ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተመድበው ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ ተደርገዋል።

ተመራቂዎቹ እንደሚናገሩት፣ በ2010 ዓ. ም. ከእነርሱ ጋር የሕክምና ትምህርትን ከተቀላቀሉት 110 ተማሪዎች ውስጥ 50ዎቹ ዘንድሮ ተመርቀዋል።

ሌሎች 50 ተማሪዎች ደግሞ ጂማ ዩኒቨርሲቲ ተመድበው ባለፈው ዓመት አጠናቀዋል። ቀሪዎቹ 10 ያህሉ ግን በተለያዩ ምክንያቶች ትምህርታቸውን ያቋረጡ ናቸው።

ዶክተር መብርሂት እንደምትለው፣ አንዳንዶቹም በተፈጠረው ሁኔታ ምክንያት የትምህርት ዘርፋቸውን ለመቀየር ተገደዋል።

በተለይም የወጣትነት ዕድሜያቸውን በትምህርት ዘግይተው ማሳለፍ ያልፈለጉ፣ ለወላጆቻቸው ቀድመው መድረስ በመፈለግ ወደሌሎች ዘርፎች ፊታቸውን በማዞራቸው እና የቤተሰብ ድጋፍ በማጣታቸው ትምህርታቸውን ያቋረጡ ስለመኖራቸው ትናገራለች።

ለነርሱ ግን የቤተሰብ እና የጓደኞች ድጋፍ ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ ወሳኝ ሚና እንደነበረው ይገልጻሉ።

የሕክምና ትምህርት ከባድ ከሚባሉ የትምህርት ዘርፎች አንዱ ነው።

በትግራይ ጦርነት ወቅት ግን በዚህ ዘርፍ የነበሩ ተማሪዎች ከትምህርቱ ጫና በተጨማሪ የጦርነት፣ የመፈናቀል፣ የሥነ ልቦና ቀውስ እና የኢኮኖሚ ችግሮችን ለመቋቋም ተገደዋል።

ከጦርነቱ በኋላ ትምህርት ወደ መደበኛ ሁኔታው እንዲመለስ ተስፋ ቢኖራቸውም፣ የጠበቁት ሁኔታ በቀላሉ አልተፈጠረም።

ዶክተር መብርሂት፣ የፕሪቶሪያው ስምምነት ተፈርሞ ጦርነቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ትምህርት እንዲጀመር እና መደበኛ እንቅስቃሴዎች እንዲመለሱ ብትጠብቅም፣ ለወራት የሚቆይ ተጨማሪ ጊዜ እንዲጠብቁ መደረጋቸውን ታስታውሳለች።

ይህም በሥነ ልቦናዋ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳሳደረ ትገልጻለች። በወቅቱ የሕክምና ትምህርቷን አቋርጣ ሌላ የትምህርት ዘርፍ ለመምረጥ እስከማሰብ ደርሳ እንደነበር ትገልጻለች።

ከጦርነት በኋላ ያለው የሥነ ልቦና ቀውስ "12ኛ ክፍል እያለሁ ሕክምና እማራለሁ ብዬ መወሰኔን የተጠራጠርኩበት ነበር" ትላለች።

በቤተሰብ እና በጓደኞቿ ድጋፍ የዩኒቨርሲቲውን የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከፍተኛውን ውጤት እንዳስመዘገበች ትናገራለች።

ተመራቂዎቹ ሳያቋርጡ ጠንክሮ መሥራት እንዲሁም ከትምህርት ውጭ ያሉ ነገሮች ላይ መሳተፍ ለዚህ እንዳበቃቸው ይገልጻሉ።

ዶክተር እመቤት እንደምትለው ትግራይ ውስጥ ያለው ሁኔታ ተስፋ የሚያስቆርጥ በመሆኑ ጠንክሮ መሥራት ግድ ይላል።

መብርሂት በቀጣይ በዘርፉ የአመራር ሥራዎች ላይ የመሳተፍ ዕቅድ እንዳላት ስትገልጽ፣ ዶክተር ኤደን እና እመቤት ምርምሮች ላይ የበለጠ መሥራት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

መቀለ ዩኒቨርሲቲ በ2013 ዓ. ም. የትግራይ ኃይሎች መቀለን በተቆጣጠሩት በሳምንቱ ነበር ሥራውን ያቆመው።

መቀለ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በትግራይ የሚገኙት ራያ፣ አክሱም እና አዲግራት ዩኒቨርሲቲዎች የትግራይ ጦርነት ከተቀሰቀሰ አንስቶ የማስተማር ሥራቸውን በተለያየ ጊዜ አቋርጠው እንደገና ጀምረዋል።

ተማሪዎች በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ ተደርገው ተመርቀዋል።