ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሰሜን ኮሪያ ጠላፊዎች በሀሰተኛ የቪዲዮ ጥሪ 400 ሚሊዮን ዶላር ክሪፕቶ መዝረፋቸውን ኤፍቢአይ አስታወቀ
በሰሜን ኮሪያ በመንግሥት የሚደገፉ ጠላፊዎች የግለሰቦችን መረጃዎች ለመስረቅ የሀሰት የቪዲዮ ጥሪ በማድረግ ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ መውሰዳቸውን የአሜሪካ ባለሥልጣናት አስታወቁ።
የአሜሪካ ፌዴራል ፖሊስ (ኤፍቢአይ) 'ፌስ ስቲለር' ሲል በገለጸው እና የሌሎችን ቪዲዮ በመጠቀም በሚፈፀም ማጭበርበር ባለፉት 18 ወራት ብቻ ከ900 በላይ ሰዎች ተጎጂ ሆነዋል።
የኤፍቢአይ ሳይበር ዳይሬክተር ብሪት ሊተርማን ለድርጊቱ ሰሜን ኮሪያን ከስሰዋል።
"የጦር መሣሪያ ፕሮግራሙን በገንዘብ ለመደገፍ መጠነ ሰፊ የክሪፕቶከረንሲ ስርቆት ላይ ጥገኛ የሆነው የሰሜን ኮሪያ አገዛዝ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ቢሊዮን ዶላሮችን ሰርቋል" ብለዋል።
የአሁኑ ዝርፊያ የተሰማው በዓለም ትልቁ የሆነው ግዙፉ የክሪፕቶ መገበያያ ባይናንስ፣ ጠላፊዎች 6.3 ቢሊዮን ዶላር ለመስረቅ ሐሰተኛ የሥራ ቃለ መጠይቅ ማድረጋቸውን ካስታወቀ በኋላ ነው።
የአሜሪካ የሕግ አስፈፃሚ ተቋማት በባይናንስ ላይ የተፈፀመው ይህ ጠለፋ በሰሜን ኮሪያ በሚደገፉ ጠላፊ ቡድኖች እስካሁን ድረስ ከተፈፀመው ከፍተኛው መሆኑን ገልጸዋል።
ፒዮንግያንግ ግን ክሱን ውድቅ አድርጋለች።
ባለሥልጣናት እንዳሉት በአሁኑ ስርቆት 'ፌስ ስቲለሮች' በክሪፕቶከረንሲ እና ዌብ3 ዘርፎች ውስጥ የሚሰሩትን ዒላማ ማድረጋቸውን ተናግረዋል። በተለይም ደግሞ ማንኛውም ሰው ሊገለገልባቸው የሚችሉ ሶፍትዌሮችን በመስራት እና በመጠገን ላይ የሚሳተፉትን ዒላማ አድርገዋል።
ኤፍአቢይ እና የፍትሕ መሥሪያ ቤት እንዳስረዱት ጠላፊዎቹ ስርቆቱን ለመፈፀም ዒላማ ያደረጓቸው ግለሰቦች ጋር የቪዲዮ ጥሪ ለማድረግ ሀሰተኛ ወይም የተጠለፉ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾችን ተጠቅመዋል። ለዚህም ተመሳሳይ የሆነ ዙም፣ ማይክሬሶፍት ቲምስ እና ጉግል ሚት ተጠቅመዋል።
ከዚያም ጠላፊዎቹ ከዚህ በፊት የስርቆት ዒላማ የተደረጉ ግለሰቦችን ቀድሞ የተቀረጸ እና ድምጽ የሌለው ቪዲዮ በማጫወት የእውነት ስልክ የተደወለላቸው እንዲመስላቸው አድርገዋል።
የቪዲዮ መልዕክቱን ዒላማ ወደተደረገው ሰው በመላክ 'ክሊክ' በማድረግ ድምጹን እንዲያስተካክሉ ጠይቀዋቸዋል። ይህንን በሚጫኑበት ጊዜ ማልዌር የተባለ ሌላ ሶፍትዌር እንዲጫን ያደርጋል። ይህም ጠላፊዎቹ የዒላማዎቹን ኮንታክቶች እና መተግበሪያዎች እንዲጠልፉ የሚያስችላቸው ሲሆን ሌሎች ሰዎችንም ዒላማ ለማድረግ እድሉን ያሰፋላቸዋል።
ጠላፊዎቹ እነዚህን ጥሪዎች በምስጢር የሚቀዱ ሲሆን የድምጾቹን ቅጂዎች ሌሎች አዳዲስ ዒላማዎችን ለመጥለፍ እንደሚጠቀሙባቸው የአሜሪካ ባለሥልጣናት ገልጸዋል።
ኤፍአቢይ እንደገለጸው 'ፌስ ስቲለርስ' በማኅበራዊ ኢንጂነሪነግ ማጭበርበር በቴክኒክ እና ደኅንነት ዙሪያ በጣም ልምድ ያላቸውን ኮምፒዩተር ተጠቃሚዎች ጭምር ለማታለል በጣም ውጤታማ ነው።
በሎስ አንጀለስ የመስክ ቢሮ ረዳት ዳይሬክተር የሆኑት ፓትሪክ ግራንዲ በሰጡት መግለጫ " በቪዲዮ ስብሰባዎች በምናካሂድባቸው መድረኮች ላይ ያለንን እምነት እና ግለሰባዊ ግንኙነቶች ላይ ብዝበዛ እየተፈፀመ ነው" ብለዋል።