ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ግዙፉ የክሪፕቶከረንሲ ኩባንያ ባይናንስ በታሪክ ትልቅ የተባለ የገንዘብ ምንተፋ ተፈፀመበት
እውቅ የክሪፕቶከረንሲ ኩባንያ የሆነው ባይናንስ ሐሙስ ዕለት "በታሪክ ትልቁ ምንተፋ" የተባለ እና 6.3 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የዲጂታል ገንዘብ ላይ ተጽዕኖ ያሳደረ ስርቆት ተፈጸመበት።
የዓለማችን ግዙፉ የክሪፕቶከረንሲ መገበያያ ከሌሎች መድረኮች ጋር ባደረገው ትብብር ጥቃት የደረሰበት ግማሽ የሚሆነው ገንዘብ መታገዱን ገልጿል።
የተደረጉ ቅድመ ምርመራዎች እንደሚያሳዩት የአንድ የድርጅቱ ሠራተኛ ላፕቶፕ ለጥቃቱ ሳያጋልጥ አልቀረም። አጥቂዎቹ በላፕቶፑ ላይ ያልተፈቀደ ወጪ እንዲያደርጉ መፍቀዱን ባይናንስ አስታውቋል።
'ትሬደር ትሬተር' በተባለ የሰሜን ኮሪያ መንታፊ ቡድን የተፈፀመውን ታሪካዊ የ1.5 ቢሊዮን ዶላር ምንተፋ ያረጋገጡ ሁለት የትንተና ድርጅቶች ስለ ባይናንስን ምንተፋ ገልፀዋል።
በሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ምርመራውን የሚያከናውነው 'ቲአርኤም ላብስ' በሪፖርቱ እንደገለፀው በርካታ የባይናንስ ጥቃት ሁኔታዎች ከሰሜን ኮሪያ ጋር የተያያዘውን የመንታፊዎች ቡድንን ይመስላል።
የድርጅቱ ዓለም አቀፍ የፖሊሲ ኃላፊ አሪ ሬድቦርድ የባይናንስ ጥቃት ኢንደስትሪው አይቶት የሚያውቅ አይደለም ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል ።
አጥቂዎቹ የዘረፉት ከፍተኛ ገንዘብ አሁንም በእጃቸው ይገኛል። ይህም ማለት ገንዘቡን ለመከታተል እና ለማስመለስ የሚደረገው ጥረት አለማብቃቱን ሬድቦርድ አክለው ተናግረዋል።
ሌላኛው የክሪፕቶ ገንዘብ ተንታኝ ድርጅት 'ቼንአናሊስስ' የሰሜን ኮሪያው መንታፊ ቡድን ከጥቃቱ ጀርባ እንዳለ "እጅግ እርግጠኛ" መሆኑን ገልጿል።
የድርጅቱ የምርምር ኃላፊ ኤሪክ ኮርዲን እያንዳንዱ የክሪፕቶከረንሲ መለዋወጫ መድረኮች ለጥቃት ተፈላጊ ስለሆኑ ደኅንነታቸውን እንዲጠብቁ አሳስበዋል።
ቢቢሲ ጥቃቱ ከሰሜን ኮሪያ መንታፊዎች ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ባይናንስን ማብራሪያ ቢጠይቅም በቀጥታ ምላሽ አላገኘም።
ኩባንያው "ወንጀለኞችን ለመለየት እና ለፍትህ ለማቅረብ ከሕግ አስፈፃሚ አጋሮቻችን ጋር በቅርበት እየሰራን ነው" ብሏል።
የባይናንስ የጋራ ሥራ አስፈፃሚ ይ ሂ በማኅበራዊ የትስስር ገፆች በርካታ የክሪፕቶ ከረንሲ ኩባንያዎች ገንዘቡ እንዳይዘዋወር በማገዳቸው አመስግነዋል።
'ቲዘር' እና 'ሰርክል' የተባሉ ትላልቅ የክሪፕቶ ከረንሲ መገበያያ መድረኮች የባይናንስን ጥቃት ተከትሎ ምላሽ ለመስጠት በአጠቃላይ 2.7 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ማገዳቸውን አስታውቀዋል።
የሰርክል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጀርሚ አሌር ድርጅታቸው ባይናንስን በሚመለከት ምዝበራዎች እንዳይፈፀሙ በቅርበት እየተከታተሉ እንደሆነ እና ከጥቃቱ ጋር የተያያዘ 800 ሚሊዮን ዶላር ማገዳቸውን ተናግረዋል።
የቴዘር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፓውሎ አሪዶኒዮ በበኩላቸው የባይናንስን ጥቃት ተከትሎ 1.6 ቢሊዮን ዶላር ማገዳቸውን ገልፀዋል።
ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ቤተሰባቸው ጋር ግንኙነት ያለው 'ወርልድ ሊብርቲ ፋይናንሺያል' የተባለው የክሪፕቶ ኩባንያም የተዘረፈውን ገንዘብ ለማገድ ከአጋሮቹ ጋር መስራቱን አስታውቋል።
እ.አ.አ በ2017 በቻይና የተመሠረተው ባይናንስ በመላው ዓለም የተመዘገቡ ከ300 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች እንዳሉት ይገመታል።