ቡና አንዳንዶችን ሲያነቃቃ ሌሎች ላይ ምንም ተጽዕኖ የሌለው ለምንድን ነው?

"ቡና እኔ ላይ ምንም ተጽዕኖ የለውም" ትላች የ20 ዓመቷ ኤምሊ። "ብዙ ጊዜ ሁለት ኩባያ ቡና እንዲሁም ተጨማሪ ሃይል ሰጪ መጠጦች እጠጣለሁ። በተጨማሪም በየምሽቱ ኮካ የምጠጣ ሲሆን ምንም ተጽዕኖ የለውም።"
እንደ ኤምሊ ዓይነት ሰዎች በየአካባቢያችን አሉ። ሁለት ስኒ ቡና ጠጥተው ወይንም በምሽት የሚያነቃቃ መጠጥ ወስደው ያለ ሃሳብ እንቅልፍ የሚወስዳቸው ሰዎች አሉ።
ለበርካታ ሰዎች ግን የካፌን ተጽዕኖ ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ነው።
አንዳንዶች በምሽት ቡና ጠጥተው እንደ ሕጻን ልጅ ክልትው ብለው ሲተኙ ሌሎች ግን ዐይናቸው ፈጥጦ በሃሳብ ሲናውዙ የሚያድሩት ለምንድ ነው?
ካፌይን ምንድን ነው?
ካፌይን በዓለም ላይ በጣም ታዋቂው አነቃቂ ንጥረ ነገር ነው።
ከሁለት ቢሊየን ስኒ በላይ ቡና በዓለማችን በየዕለቱ የሚጠጣ ሲሆን ይህም ኮላ፣ ኃይል ሰጪ መጠጦች፣ ቸኮሌት፣ ማስቲካ፣ ለስፖርት የሚታዘዙ ተጨማሪ መድሃኒቶችን ከመውሰዳችን በፊት ነው።
ካፌይን ንቁ እንድንሆን፣ ትኩረታችንን እንድንሰበሰብ፣ ድካማችንን ለማባረር ያገለግለናል። የምንወስደው የካፌይን መጠን በጨመረ ቁጥር ግን ራስ ምታት፣ የልብ ምት መፍጠን፣ እረፍት አልባ ሌሊት እና መረበሽ ያስከትልብናል።
ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ካፌይን ለሰውነታችን ተጨማሪ ኃይል አይሰጥም፤ ይልቁንም ድካምን ለመሸፈን ይረዳል።
ይህንን የሚያደርገውም፣ ቀኑን ሙሉ በአንጎል ውስጥ በመከማቸት እንቅልፍ እንዲሰማን የሚያደርገውን 'አዴኖሲን' (adenosine) የተባለ ኬሚካል ተግባር በመግታት ነው።
ሰዎች ላይ ያለው ተጽዕኖ ለምን ተለያየ?
አንደኛው ቁልፍ ምክንያት ካፌይን በሰውነታችን ውስጥ ምን ያህል ይቆያል የሚለው ነው።
አንድ ስኒ ቡና ከጠጡ በኋላ፣ ቡናው ወደ ደም ዝውውር ስርዓት ውስጥ ገብቶ በፍጥነት ወደ አንጎል ይደርሳል።
በዚህ ሂደት ውስጥ፣ በጉበት ውስጥ በሚገኝ ኢንዛይም አማካኝነት ይከፋፈላል (ወይም ሜታቦላይዝ ይደረጋል)፤ በመጨረሻም በሽንት አማካኝነት ከሰውነት ይወገዳል።
በቺካጎ በሚገኘው የኖርዝዌስተርን ዩኒቨርሲቲ የአመጋገብ ጥናት ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ማሪሊን ኮርኔሊስ እንደገለጹት፣ ይህ ሰውነትን የማጽዳት ሂደት እንደየግለሰቡ ሁኔታ ከስድስት እስከ 20 ሰዓታት ሊወስድ ይችላል።
"አንድ ሰው የመጀመሪያውን ቡና ሲጠጣ ውጤቱን ላያስተውል ይችላል" ሲሉ ይናገራሉ።
"ነገር ግን ከሁለት ወይም ከሦስት ሰዓታት በኋላ ካፌይኑ አሁንም በሰውነት ውስጥ ይቆያል፤ በዚህ ጊዜ ሁለተኛ ስኒ ቡና ከተጨመረ፣ መጠኑ ሚዛኑን በማዛባት ትንሽ የጭንቀት ስሜት እንዲሰማዎት ሊያደርግ ይችላል።"
ጉበት ካፌይንን ምን ያህል በፍጥነት እንደሚያጣራ የሚወሰነው ሲዋይፒ1ኤ2 (CYP1A2) የተባለ ዘረ መል ነው።
የሚገርመው ነገር፣ ይህ ሂደት ቢያንስ በተወሰነ ደረጃ በዘር ግንድዎ ተጽዕኖ ሊደረግበት ይችላል።
በዚህ ዓመት የታተመ አንድ ጥናት እንዳመለከተው፣ በአማካይ የአውሮፓ እና የደቡብ አሜሪካ ሰዎች ካፌይንን በፍጥነት የማስወገድ (የመሰባበር) ዝንባሌ አላቸው።
ምን ምን ጉዳዮች ከግምት ይገባሉ?
ዲኤንኤ የጉዳዩን ኢምነት ብቻ ነው የሚነግረን። ሲጋራ ማጨስ ጉበት ካፌይንን በፍጥነት እንዲሰባብር በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፤ ይህም ሂደቱን እስከ 65 በመቶ ያህል ያፋጥነዋል።
ይህም አጫሾች ለምን ብዙ ቡና እንደሚጠጡ፣ እንዲሁም ማጨስ ያቆሙ ሰዎች ለምን የለመዱት ቡና ከበፊቱ ይልቅ በጣም ጠንካራ ሆኖ እንደሚሰማቸው ለማብራራት ይረዳል።
አንዳንድ አንቲባዮቲኮች፣ የእርግዝና መከላከያ ክኒኖች እና ሌሎች በሐኪም የሚታዘዙ መድኃኒቶች ግን ተቃራኒ ውጤት ሊኖራቸው ይችላል፤ እነዚህም ካፌይን በሰውነት ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ እንዲቆይ በማድረግ ውጤቱ እንዲራዘም ያደርጋሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በእርግዝና ወቅትም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው፤ በዚህ ጊዜ የሚከሰቱ የሆርሞን ለውጦች ካፌይንን የሚሰባብረውን የጉበት ኢንዛይም እንቅስቃሴ ያዳክማሉ።
በተጨማሪም፣ ሰውነት ለካፌይን የሚኖረው መላመድ አለ።
ሰውነት ይህንን ኬሚካል ሲላመድ፣ አዘውትረው ቡና የሚጠጡ ሰዎች ለካፌይን ያላቸው ስሜት ይቀንሳል።
ከዚያም ለጥቂት ሳምንታት ቡና ሳትጠጡ ከቆያችሁ፣ በአንጎል ውስጥ የተፈጠሩት እነዚያ የመላመድ ለውጦች ወደነበሩበት ሁኔታ መመለስ ይጀምራሉ፤ ይህም ማለት፣ ከእረፍቱ በኋላ የምትጠጡት የመጀመሪያው ቡና ያልተለመደ የመነቃቃት ወይም የመረበሽ ስሜት ሊፈጥርባችሁ ይችላል።
ባለሙያዎች ምን ይመክራሉ?
የእንቅልፍ ተመራማሪዎች ብዙውን ጊዜ ከመተኛታችሁ በፊት ቢያንስ ለስድስት ሰዓታት ያህል ካፌይን ከመውሰድ መቆጠብን ይመክራሉ።
የሥነ-ልቦና ባለሙያ እና የእንቅልፍ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ሊንሳይ ብራውኒንግ እንደሚሉት፣ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት ካፌይን እንቅልፍ እንዳይወስድዎ ከማድረግ ባሻገር የእንቅልፍዎን ጥራትም ሊጎዳ ይችላል።
"ሰዎች ከምሽቱ 4 ሰዓት አካባቢ ለመተኛት ካሰቡ፣ ከቀኑ 8 ሰዓት በኋላ ካፌይን ከመውሰድ እንዲቆጠቡ እመክራለሁ" ሲሉ ይናገራሉ።
"ነገር ግን፣ ሁሉንም ጉዳዮች በአንድ ዓይነት ጥብቅ ሕግ ማስተዳደር አዋጭ አይደለም፤ ምክንያቱም ይህ አካሄድ በጉዳዩ ላይ ያሉትን ውስብስብ ነገሮች እና የተለየ የግለሰቦችን ሁኔታ ግምት ውስጥ አያስገባም።"
የዩናይትድ ኪንግደም የጤና ተቋም እርጉዝ ሴቶች የካፌይን መጠን በቀን ከ200 ሚሊግራም በታች እንዲገድቡ ይመክራል፤ ምክንያቱም ጥናቶች ከመጠን በላይ የካፌይን አጠቃቀም ዝቅተኛ ክብደት ያለው እና ለሌሎች የጤና ችግሮች የተጋለጠ ልጅ እንዲወለድ ያደርጋል ብለዋል።
ለሌሎች አዋቂዎች ደግሞ ዋናው ምክር መጠነኛ አጠቃቀምን መከተል ነው፤ ምክንያቱም ለካፌይን የሚኖረው ስሜታዊነት ወይም ምላሽ ከሰው ወደ ሰው በእጅጉ ይለያያል።
"ካፌይን በአንጻራዊነት ደህንነቱ የተጠበቀ ነው" ይላሉ የብሪስቶል ዩኒቨርሲቲ የአመጋገብ ጥናት ኤሜሪተስ ፕሮፌሰር ፒተር ሮጀርስ።
"ከመጠን በላይ ከተወሰደ፣ ሰውነት ይንቀጠቀጣል እንዲሁም የመረበሽ እና መጥፎ ስሜት ይፈጠራል፤ በዚህም 'ይህንን ማቆም አለብኝ፣ ከዚህ በላይ መውሰድ ምንም ፋይዳ የለውም' የሚል ግንዛቤ ይፈጠርብዎታል።"
ከመጠን በላይ ካፌይን መውሰድ እጅግ አልፎ አልፎ የሚከሰት ሲሆን፣ ከባድ የመመረዝ አደጋዎች አብዛኛውን ጊዜ የሚከሰቱት በደረጃቸው ከፍተኛ በሆነ (concentrated) የካፌይን ምርቶች ምክንያት ነው። በእነዚህም መጠጦች ውስጥ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ብቻ በርካታ ግራም ካፌይን ሊወሰድ ይቻላል።
ለቡና አፍቃሪዎች መልካም ዜናው፣ ያ በየቀኑ ጠዋት የሚደረግ (ምንም እንኳን ዋጋው ትንሽ ከፍ ያለ ቢሆንም) ልማድ ከጤና መሻሻል ጋር የተያያዘ መሆኑ ነው።
ምንም እንኳን ተመራማሪዎች ቡና ለዚህ ብቸኛው ምክንያት መሆኑን ማረጋገጥ ባይችሉም፣ ለበርካታ አሥርት ዓመታት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ቡናን በመጠኑ የሚጠጡ ሰዎች ለተለያዩ ዋና ዋና በሽታዎች የመጋለጥ እድላቸው ዝቅተኛ ሲሆን፣ ከማይጠጡት ሰዎች ይልቅ ረዘም ላለ ጊዜ የመኖር እድልም ሊኖራቸው ይችላል።

































