ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአሜሪካ ከመስከረም 11ዱ የሽብር ጥቃት በኋላ ትልቁ የተባለ አገር አቀፍ የበረራ መስተጓጎል አጋጠመ
የአሜሪካ የፌደራል አቪየሽን አስተዳደር ከመስከረም 11ዱ የሽብር ጥቃት ወዲህ ረጅሙ ነው የተባለው አገር አቀፍ የበረራ ማቆም ችግር መፈታቱን አስታወቀ።
አስተዳደሩ አርብ ዕለት ለአራት ሰዓታት የዘለቀው የበረራ ማቆም የተከሰተው፣ የአየር መቆጣጠሪያ ማዕከሎች ላይ በተፈጠረ የግንኙነት ችግር ምክንያት ባጋጠሙ "ከአቅም በላይ የሆኑ ሁኔታዎች" ነው ብሏል።
የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መስሪያ ቤት ማርክዌይን ሙለን ጥቃት ስለመፈፀሙ ምንም ምልክት እንደሌለ እና በሰው ላይ ጉዳት አለመድረሱን ተናግረዋል።
ችግሩ አርብ ዕለት 8,500 በረራዎች እንዲዘገዩ እና 8,000 የሚሆኑ በረራዎች ደግሞ እንዲሰረዙ አደርጓል።
የፌደራል አቪየሽን አስተዳደር (ኤፍኤኤ) ከአሜሪካ የሚነሱ ሁሉም በረራዎች ላልተወሰነ ጊዜ እንዳይበሩ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
አስተዳደሩ ይህን ትዕዛዝ ሲሰጥ ከ3,500 በላይ አውሮፕላኖች አየር ላይ ነበሩ። አንዳንዶች ወደ ሌሎች አየር ማረፊያዎች እንዲያርፉ ሲደረግ ሌሎች ደግሞ ወደ መጀመሪያ ማረፊያቸው እንዲበሩ ተደርጓል።
ከሰዓታት በኋላ አንዳንድ በረራዎች ከሳን ፍራንሲስኮ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ እንዲነሱ ተፈቅዷል።
'ከዩሮኮንትሮል' አባል አገራት ተነስተው ወደ አሜሪካ የሚደረጉ በረራዎችም በአቪየሽን አስተዳደሩ ጥያቄ መሰረት መሰረዛቸው ተነግሯል።
በርካታ የአውሮፓ ሕብረት አገራት፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ዩክሬን፣ ቱርክ፣ እስራኤል እና ሞሮኮን ጨምሮ 42 የዩሮኮንትሮል አባል አገራት አሉ።
የአውስትራሊያ ትልቁ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲድኒ ወደ አሜሪካ የሚደረጉ ሁሉንም በረራዎች ሁኔታዎች እስከሚቀየሩ ድረስ አግዷል።
'ኤር ካናዳ' በአሜሪካ እና ካናዳ መካከል የሚደረጉ በረራዎችን ሰርዟል።
የአሜሪካ ትራንስፖርት ሚኒስትር ሿን ደፊ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ችግሩ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ድረስ ተፅዕኖ ያስከትላል ብለዋል።
"ዛሬ ከሰዓት የተፈጠረውን እስክንፈታ ድረስ የወሰነ ጊዜ ይወስድብናል" ብለዋል።
በመላው አገሪቱ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ መንገደኞች በአየር ማረፊያዎች የተጉላሉ ሲሆን፣ በርካቶች ምሽቱን የት እንደሚያሳልፉ እንኳ እንደማያውቁ ተናግረዋል።
ዴልታ አየር መንገድ እና ዩናይትድ አየር መንገድ አገልግሎታቸውን ዳግም ማስጀመራቸውን አስታውቀዋል።
የአሜሪካ አየር መንገድ በተቻለው መጠን ሌሊቱን ሙሉ የቀሩ በረራዎችን ማካሄድ ላይ ማተኮሩን ገልጿል።
ጄትቡሉ በበኩሉ በረራዎቹን ቅዳሜ ጠዋት እንደሚጀምር አስታውቋል።
የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ችግሩ የተፈጠረው የአየር ቁጥጥር የግንኙነት ስርዓት ከአቅሙ በላይ ሆኖበት እንደሆነ ተናግረዋል።
ችግሩ የግንኙነት መስመር እና ራዳር ላይ ተፅዕኖ ማድረሱንም ገልፀዋል።
ሚኒስትሩ ስርዓቱ ሙሉ ለሙሉ እንደገና መገንባት እንዳለበት እና ለዚህም 50 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። "ችግሩ መከሰቱን ይቀጥላል" ብለዋል።
የአርቡ የበረራ መቆም ችግር እ.አ.አ መስከረም 11/2001 በአልቃይዳ የአውሮፕላን ጠለፋን ተከትሎ የተከሰተ ሁለተኛው ግዙፍ አገር አቀፍ ክስተት ነው።
በክራንፊልድ ዩኒቨርስቲ የአቪየሽን ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ጋይ ግራተን "ከመስከረም 11 በኋላ ይህ የባሰ ይመስላል፤ ነገር ግን በተመሳሳይ መልኩ አይደለም" ብለዋል።
እ.አ.አ በ2023 አንድ ሰዓት ከ53 ደቂቃ የዘለቀ የበረራ ማቆም 9,500 በረራዎች እንዲዘገዩ እና 1,300 በረራዎች ደግሞ እንዲሰረዙ ማድረጉን ገልፀዋል።
የ2023ቱ የበረራ ማቆም የአየር ትራፊክ ደኅነንት ማስታወቂያዎች መታተም ባለመቻላቸው ስርዓቱ ዳግም እስኪመለስ ደረስ በረራዎች እንዲቆሙ ተደርጓል።
ይሁን እንጂ አርብ ዕለት የተፈጠረው ክስተት ከ2023ቱ ክስተት ለረጅም ጊዜ የቆየ ነው።