በአንድ ዓመት ውስጥ ለ5ሺህ ያህል ታካሚዎች በነጻ ሕክምና የሰጠው ዶ/ር ዓለማየሁ እሸት

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 7 ደቂቃ

ዶ/ር ዓለማየሁ እሸት ከአንገት በላይ ስፔሻሊስት ነው። ጎንደር እና ጥቁር አንበሳ ነው የተማረው። ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ነበር የሚሠራው።

የሕክምና ትምህርቱን በጎንደር ዩኒቨርስቲ ሲከታተል አጋፔ የሚባል በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የተቋቋመ ማኅበር ነበር።

ማኅበሩ ከተማሪዎች ገንዘብ፣ ልብስ፣ ምግብ ሰብስቦ ለነዳያን ይሰጣል። ተማሪው ደም የሚለግስበትን መርሐ ግብር አዘጋጅቶ የተሰበሰበውን ደም ለቀይ መስቀል ያስረክባል።

የዚህ አጋፔ የተሰኘው ማኅበር የሐሳቡ ባለቤትም መሥራችም ዶ/ር ዓለማየሁ ነበር።

በዩኒቨርስቲው የሕክምና ተማሪ በነበረበት ወቅት ተማሪውን ሰብስቦ ብር በማዋጣት ፋሲካን ከነዳያን ጋር በማሳለፍ ጀመረ።

ከተማሪው ልብስ ሰብስቦ ጎንደር ለሚገኙ ነዳያን በመስጠት አገልግሎቱን አሰፋ። እያለ እያለ አንድ ነገር መጣለት። የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ብዙ ባዶ መሬት አለው። ለእኛ መሬቱን ቢሰጠን፣ እኛ ደግሞ ቤት ገንብተን በየጎዳና ያሉ አባቶች እና እናቶችን እንዲሁም ሕፃናትን እናኖርበታለን ብሎ አሰበ።

አሥተዳደር ቢሮ ገባ። ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ቢሮ ገባ። ዕቅዱን አቀረበ። በብዙ ትግል ሐሳቡ ተቀባይነት አገኘ።

በወቅቱ የነበረው የጎንደር ከተማ አስተዳደር የአጋፔን ጥንካሬ ተመልክቶ በከተማዋ መሃል የመሥሪያ ቦታ ለማኅበሩ ሰጠ።

ዶ/ር ዓለማየሁ እና ጓደኞቹ የሚደግፏቸው ሰዎች በቋሚነት እገዛ እንኳን ማግኘት ባይችሉ ማረፊያ አግኝተው የሥራ ዕድል ተመቻችቶላቸው ከጥገኝነት ወጥተው ራሳቸውን እንዲችሉ 36 ቤቶች ሰርተው ልጆቻቸውን ጨምሮ ከ100 በላይ ቤተሰቦች የመኖሪያ መንደር መሥርተው እዚያው እየኖሩ ይገኛሉ።

የጎንደር ዩኒቨርስቲ ተማሪ ሆኖ የጀመረው አጋፔ ተመርቆ ሲወጣ እንዳይቋረጥ፣ ቀጣይ ተማሪዎች ሃሳቡን እንዲያስቀጥሉት በሚል ሥራዎች መስራታቸውን ዶ/ር ዓለማየሁ ይናገራል።

ይህንንም ለማድረግ የመጨረሻ ዓመት ተማሪዎች በመሪነት ሲያገለግሉ አንድ ዓመት የሚቀራቸው ደግሞ ከሥር በመሆን የመረከብ ሥራዎችን እንዲሰሩ በማድረግ ቀጣይነቱን ያረጋግጣሉ።

በዚህም አሁን ድረስ በተመራቂ ተማሪዎች የበላይ ክትትል አዲስ የሚተኩ ተማሪዎች ድርጅቱን እያስቀጠሉ ይገኛሉ።

እጅግ ጊዜን በሚጠይቅ የሕክምና ተማሪ ሕይወት ውስጥ ሆኖ ሌሎችን ለመርዳት፣ ቤት ሰርቶ በቋሚነት ማረፊያ እንዲያገኙ ለማድረግ እና ከዓመት ዓመት የማይቋረጥ የድጋፍ ሰንሰለት ያለው ድርጅት መምራት የቻለው "በሕይወቴ ዓላማ መር በመሆን ማሳካት የምፈልገውን በማወቄ ነው" ይላል።

ዓላማችን ጠንካራ ስለነበር የማየው ይህንን ዓላማ መስዋዕትነት ከፍሎ፣ የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን ተጋፍጦ ማለፍ ብቻ ነበር የሚለው ዶ/ር ዓለማየሁ፣ ፈተናዎች ቢኖሩም፣ የጊዜ መጣበብ ቢገጥምም፣ የገንዘብ ችግር ቢያሰናክልም "ዓላማችን እና ሕብረታችን ጠንካራ ስለነበር አሳክተነዋል" በማለት በተማሪነታቸው 36 ቤቶችን ሰርተው ለማስረከብ የበቃበትን ምስጢር ይናገራል።

ከተማሪነት በኋላ የቀጠለው የነጻ አገልግሎት

ዶ/ር ዓለማየሁ በ2008 ዓ.ም. ከጎንደር ዩኒቨርስቲ ከተመረቀ በኋላ በደሴ ሆስፒታል ተመድቦ አገልግሏል።

በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሕክምና ኮሌጅ የከአንገት በላይ የስፔሻላይዝድ ትምህርቱን ሲከታተልም ሆነ በጳውሎስ ሆስፒታል የቀዶ ሕክምና ባለሙያ ሆኖ ሲሠራ ራቅ ካሉ የአገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ ታካሚዎች ሲቸገሩ ይመለከታል።

በጳውሎስ ሆስፒታልም ኾነ በግል ሆስፒታል የሕክምና አገልግሎት ሲሰጥ አብዛኛው ታካሚ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚመጡ መሆናቸውን ያስተውላል።

እነዚህ ታካሚዎች ለብዙ እንግልት ሲጋለጡም ይመለከታል። ከቀዶ ሕክምና በኋላ እስኪያገግሙ የሚጠይቃቸው ዘመድ የለም። አስታማሚን የሚቀይር ሌላ አስታማሚ የለም።

ሁሌም እነዚህን ሕሙማን ቀረብ ብሎ ማየት እና ማገዝ የልቡ መሻት እንደነበር ዶ/ር ዓለማየሁ ያስታውሳል።

"ያለምንም ወጪ ትንሽ እንኳን አስተዋጽኦ ባደርግ" በሚል ወደ አንቆርጫ የጤና ጣቢያ ሲያመራ የተመለከተው ጉዳይ "በጣም የሚያሳስብ" መሆኑን ይገልጻል።

አዲስ አበባ በሚገኙ የሕክምና ተቋማት ላይ "ይህን ያህል ጫና አለ ወይ?" ብለን እንድንጠይቅ ነው ያደረገን የሚለው ዶ/ር ዓለማየሁ "በገንዘብ እጦት የሚቸገሩ፣ የተጻፈላቸውን መድሃኒት መግዛት የማይችሉ ብዙ ታካሚዎች ያጋጥሙናል"ሲል ያስታውሳል።

ለሙከራ ብሎ በዚያው በአዲስ አበባ ከተማ የነጻ አገልገሎት መስጠት ጀመረ። በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ በሚገኘው እንቆርቻ ጤና ጣቢያ የነጻ ሕክምና አገልግሎት በመስጠት ሞከረ።

ከ70 በላይ የሚኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ከአንገት በላይ (ጆሮ፣ አፍንጫ እና ጉሮሮ) ምርመራና ሕክምና አደረገ። ጥናቱን ሲጨርስ ምክረ ሃሳብ አዘጋጀ።

በቅዱስ ጳውሎስ እና አዲስ አበባ ያሉ የግል የሕክምና ተቋማት የሚሰጠውን አገልግሎት በመተው የነጻ አገልግሎት መስጠቱን ገፋበት።

በዚህም በሚዛን አማን፣ ሆሳዕና፣ ነቀምት፣ አርባምንጭ፣ ባሌ፣ መቱ ... በዙር በዙር እየሄደ ለብዙዎች ጤና መመለስ ምክንያት እንዲኾን የበኩሉን አደረገ።

በዚህ መሐል ግን አንድ ነገር አስተዋለ። አዲስ አበባ ድረስ መጥተው ለብዙ ወጪ እንዳይዳረጉ መቀነስ ቢችልም ብዙዎች ግን እዚያ በአቅራቢያቸው ባሉ የሕክምና ተቋማት እንኳ ከፍለው መታከም የማይችሉ ሰዎች እንዳሉ ተመለከተ።

ስለዚህ ከአዲስ አበባ ርቀው የሚኖሩ ታካሚዎች በነጻ አገልግሎት እንዲታከሙ ማድረግ የሚችልበትን መንገድ ሲያጠና ቆየ።

በገጠሩ የአገራችን ክፍል የሚገኘው የማኅበረሰብ ክፍል ከአንገት በላይ ሕክምናን ያለአንዳች ክፍያ በነጻ እንዲያገኝ የሚያስችለውን መርሐ ግብር ቀረጸ።

ከዩኒቨርሰቲ ተማሪነቱ ጀምሮ ከማኅበረሰቡ ጋር በቅርበት የሚሰራው ዶ/ር ዓለማየሁ በአንቆርጫ ከሰጠው የነጻ ሕክምና ባሻገር ከአንገት በላይ ስፔሻሊስት ከሆኑ በኋላ ደግሞ በገጠሪቱ የአገሪቱ ክፍል የሚገኙ ሰዎችም ይህ የነጻ ሕክምና ማግኘት አለባቸውን የሚለውን ሃሳብ አጠናክሮ ቀጠለበት።

ስለዚህ ወደተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች መሄድ እንዳለበት አመነ። እናም ሞከረ። እንደገመተው በቀላል ቀዶ ሕክምና ሊድኑ የሚችሉ ሕጻናት፣ ወጣት፣ ጎልማሳ፣ ሽማግሌ በየአካባቢው እንዳሉ ተመለከተ።

በክፍለ አገር ካሉ የሕክምና ተቋማት ጋር በመነጋገር አንድ ሁለት ከተማ ላይ ሀሳቡን ለመተግበር ሥራ ጀመረ።

እንደ አንስቴዢያ፣ ነርሶች እና የተለያዩ የሕክምና ባለሙያዎችን ይዞ ሄደ። ሰዎች አዲስ አበባ ድረስ እየመጡ ከሚንገላቱ እና ለከፍተኛ ወጪ ከሚዳረጉ ባሉበት ኾነው በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎቱን ሰጠ። እሱም ነፍሱ ረካች።

በዋና ከተሞች የሚሰጠው ዘመናዊ ሕክምና ተደራሽ የሚያደርገው በጣም ጥቂት ሰዎችን ነው የሚለው ዶ/ር ዓለማየሁ በአብዛኛው ግን ረዥም መንገድ በእግሩ ተጉዞ፣ በትራንስፖርት ወደ አዲስ አበባ ይመጣ እና አቅጣጫ ለማወቅ ሲታገል፣ በዚህም በርካታ ጊዜውን የሚያጠፋ ነው ይላል።

ሆስፒታልም ከመጣ በኋላ ቢሆን የሚታከምበትን፣ በእርሱ ሙያ ከአንገት በላይ የሕክምና ክፍልን ለማግኘት በጣም ፈተና ነው የሚሆንበት ሲል ትዝብቱን ያጋራል።

ከዚያ በኋላም ቢሆን ወደ ላብራቶሪ ሲላክ፣ አልጋ ያዝ ተብሎ ሲነገረው፣ መድሃኒት ግዛ ሲባል አቅጣጫ ለማወቅ የበለጠ ፈተና እንደሚሆንበት ዶ/ር ዓለማየሁ ማስተዋሉን ይጠቅሳል።

"ተንገላተው ሳይታከሙ የሚመለሱ ታካሚዎች አሉ" የሚለው ዶ/ር ዓለማየሁ ይህንን አገልግሎት በተቻለ መጠን ወደ እነርሱ ቀረብ ማድረግ ብንችል በሚል በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ለሚገኙ ታካሚዎች ባለበት ሕክምናውን በነጻ ለመስጠት አቅዶ መጀመሩን ይናገራል።

ዶ/ር ዓለማየሁ በጳውሎስ ሆስፒታል በሚሰራበት ወቅት ያጋጠመችውን ታካሚ አይረሳትም።

በአፏ ውስጥ ካለው እብጠት ጋር ለ25 ዓመት የኖረችው ይህች ታካሚ የወለደችው አንድ ልጅ ብቻ ነው። ሌላ ልጅ መውለድ ያልቻለችው ደግሞ በጤናዋ እክል ምክንያት በወሊድ ወቅት ለሌላ ውስብስብ የጤና ችግር እጋለጣለሁ በሚል ፍራቻ ነው።

ግለሰቧ ከዚህ በፊት የሕክምና ክትትል በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጀምራ እንደነበር እና ሊፍት መጠቀም በመፍራት ብቻ ሳትታከም መመለሷን ነግራዋለች።

በቀላሉ መታከም የምትችለውን ነገር ለረዥም ዓመታት አብሯት አንዲኖር አድርገዋለች። በአቅራቢያዋ ይህንን የሚያስረዳት የሕክምና ባለሙያ ቢኖር፣ ሕክምና ተቋሙ በባለሙያዎች የተሟላ ቢሆን አፏ ውስጥ ያለውን እብጠት ለማስወገድ 25 ዓመት መጠበቅ አያስፈልጋትም ነበር።

ይህ ለእኔ ታካሚዎቹ ባሉበት ሄዶ ለማገልገል ካነሳሱኝ ምክንያቶች መካከል አንዱ ነው ሲልም ይጠቅሳል።

በየክፍለ አገሩ በተንቀሳቀሰበት ወቅት ለዓመታት በእውቀት ማነስ፣ በገንዘብ እጦት ወይንም የሕክምና ተቋም ተደራሽ ባለመሆኑ የተነሳ ችግራቸውን ይዘው የሚኖሩ ታካሚዎች እንደሚያጋጥሙት ያስታውሳል።

በዚህም የተነሳ በአቅራቢያቸው ከአስታማሚያቸው ሳይርቁ ሕክምና እንዲያገኙ መስራት ጀመረ።

ይህ ስራውም ለሕክምናው የሚያስፈልገውን ወጪ ሙሉ በሙሉ ሌሎች በጎ አድራጎት ድርጅቶች እንዲሸፍኑ ለማስቻል በሚል ለሁሉም የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት አቋቋመ።

ታካሚዎች ያለምንም ተጨማሪ ወጪ ሙሉ በሙሉ ሕክምናቸውን እንዲያገኙ በሚል ለሁሉም መቋቋሙን ዶ/ር ዓለማየሁ ይናገራል።

ለሁሉም የተመሰረተው በዩኒቨርስቲ ከእርሱ ጋር የተማሩ እና ጊዜያቸውን እና ጉልበታቸውን በመስጠት አብረውት የነበሩ ጓደኞቹን በማካተት ነው።

እነዚህ ጓደኞቹ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሕክምና ሙያዎች ላይ ስፔሻላይዝድ ያደረጉ ሲሆን፣ ሰብ ስፔሻሊቲም የሰሩ ይገኙበታል።

በዩኒቨርስቲ ተማሪነታቸው የጀመሩትን ሰፋ አድርጎ በሙያቸው ማኅበረሰቡን ለማገልገል በመወሰን "በተሻለ መልኩ" አገልግሎቱን ለመስጠት ለሁሉም ፓን አፍሪካ ሄልዝ (lehulum pan african health support) ተቋቋመ።

ለሁሉም ከተመሰረተ በኋላ በአንድ ዓመት ውስጥ 36 ዘመቻዎችን አድርጓል። ከ4900 በላይ ታካሚዎች አክሞ 700 የሚያህሉ ዋና ዋና ቀዶ ሕክምናዎች ሰርተዋል።

እነዚህ ሕክምናዎች የሚሰሩት ከአንገት በላይ ዶክተር በሌለበት እና ሕክምናውን ከፍለው መታከም ለማይችሉ ማኅበረሰቦች መሆኑን ጨምሮ ያስረዳል።

ይህንን ሕክምና እርሱ እና ጓደኞቹ ከአዲስ አበባ ውጪ በመቱ፣ ነቀምት፣ ሚዛን፣ አርባ ምንጭ፣ ሆሳዕና፣ ባሌ፣ ሻሸመኔ፣ አሰላ፣ ጎዴ፣ ወልደያ ድረስ በመንቀሳቀስ ሰጥተዋል።

ዶ/ር ዓለማየሁ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተንቀሳቅሶ ሕክምና በነጻ ሲሰጥ "በጣም ጥቂት ችግር ይዘው ዓመታትን የሚቆዩ ታካሚዎች ያጋጥመኛል" በማለት ከመሃል ከተማ ርቀው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተደራሽ የሆነ የሕክምና አገልግሎት እንደሚያስፈልጋቸው ይናገራል።

"ለረዥም ጊዜ ጆሮዬ ተዘግቷል ብሎ የሚናገር ታካሚ በአጭር ደቂቃ ውስጥ በሚሰጠው ሕክምና ሲድን በቀላሉ መታከም የሚችል ነገር ግን ተደራሽነቱ ስለሌለ ብቻ ለረዥም ዓመታት ከሕመሙ ጋር አብረው መኖራቸውን ሳይ በየአካባቢው እየሄድኩ በሙያዬ እነዚህን ግለሰቦች ለማገልገል ምክንያት ይሆነኛል።"

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሲንቀሳቀስ ከሚያጋጥሙት ተደጋጋሚ የሕምም ዓይነቶች መካከል የጆሮ ታምቡር መበሳት፣ የአፍንጫ አለርጂ፣ የአፍንጫ እና የጉሮሮ ቶንሲል፣ አንገት እና የምራቅ እጢ ላይ የሚወጡ እብጠቶች እንደሚገኙበት ይጠቅሳል።

በሌሎች ዕይታ ውስጥ የገባው የነጻ አገልግሎት

የነጻ የሕክምና ድጋፍ ለመስጠት ከተለያዩ አገራት ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ። ዶ/ር ዓለማየሁ ከውጪ የመጡት እነዚህ ባለሙያዎች አንዳንዴ "ምን ሠርተው ሄዱ የሚለውን በተግባር የሚያውቀው አብሯቸው ያለው ባለሙያ ነው" ይላል።

በዚህም የተነሳ እነዚህ ባለሙያዎች የሚሰጡት ድጋፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ባለሙያ የተለየ ነገር ላያበረክቱ ይችላል ሲል ያስተዋለውን ያስረዳል።

ነገር ግን በአገር ውስጥ እነዚህ ባለሙያዎች የተለየ አገልገሎት እንደሚሰጡ አድርጎ የማሰብ "የመጡበትን ዓላማ ከመፈተሽ ይልቅ መምጣታቸውን ብቻ ማደናነቅ ተገቢ አይደለም ብለን እናስባለን" ሲል ያስረዳል።

ዶ/ር ዓለማየሁ በሥራ አጋጣሚ ካየቸው እና ከውጪ ከመጡት ባለሙያዎች እኛ ከምንሰራው የተለየ ላያበረክቱ ይችላሉ በማለት በአገር ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች አስፈላጊውን የሕክምና ድጋፍ ለማድረግ ብቁ መሆናቸውን ይመሰክራል።

ዋናው ነገር ይላል ዶ/ር ዓለማየሁ፣ እነዚህ ባለሙያዎች ብዙህ ሺህ ኪሎሜትሮች ተጉዘው የነጻ ሕክምና ለመስጠት ከመጡ "እኛ ጥቂት ኪሎሜትሮች ተጉዘን ለወገናችን፣ ተመሳሳይ ቋንቋ ለምናወራው እና በብዙ ነገር ለምንግባባው ለምን ትንሽ አናበረክትም በሚል እሳቤ ነው ይህንን አገልግሎት የጀመርነው" ሲል ያስረዳል።

እነ ዶ/ር ዓለማየሁ እኛ በራሳችን ለወገናችን በቂ ነን በማለት በሙያቸው የነጻ ሕክምና ለመስጠት እንደሚፈልጉ ሲናገሩ በተለይ በሕክምና ማኅበረሰብ ዘንድ "ብዙ ሰው ደስተኛ አልነበረም" በማለት ሁኔታውን ያስታውሳል።

ሃሳቡን የማጣጣል፣ የማቃለል፣ አይቀጥልም የማለት ነገር ነበር የሚለው ዶ/ር ዓለማየሁ "ትልቁ ነገር ግን ከጎኔ የነበሩት ጓደኞቼ፣ በፊትም ተማሪ ሆነን ያን ያህል ተጽዕኖ መፍጠር ከቻልን ዛሬ ደግሞ ባለሙያ ሆነን ለምን ለውጥ አንፈጥርም የሚለውን ነገር ሙሉ በሙሉ ነው የተቀበሉት" ይላል።

ወደ ክፍለ ሃገር ስንወጣ ደግሞ ያሉት ሆስፒታሎች በጣም ደስተኞች ናቸው የሚለው ዶ/ር ዓለማየሁ፣ የሕሙማኑን ችግር በየዕለቱ የሚመለከቱ፣ የባለሙያ እጥረትን የሚገነዘቡ በመሆናቸው "ኑልን አብረን እንስራ" በማለት ያበረታቱን ነበር ሲል የገጠመውን ይመሰክራል።

በምዕራብ ጎጃም አዴት ከተማ ነው ተወልዶ ያደገው ዶክተር ዓለማየሁ እሸት። በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች እየተዘዋወረ 35 ከአንገት በላይ (ENT) የሕክምና ዘመቻዎችን ማካሄዱ በሙያ አጋሮቹ ዘንድ አድናቆትን እያገኘ መጣ።

4,391 ታካሚዎችን የጤና ምርመራ አድርገው 718 ዋና ዋና ቀዶ ሕክምናዎችን በመሥራት የአንገት በላይ ሕክምናን ተደራሽ ለማድረግ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በመዘዋወር የሰጠው አገልግሎት የበርካቶችን ምስክርነት አገኘ።

ኢትዮጵያውያን ሐኪሞች ለራሳቸው ማኅበረሰብ ቅርብ በመሆን ለማገልገል መልፋታቸው ፍሬ አፍርቶ ሽልማት አስገኘለት።

በዚህ ዓመት በመስከረም ወር ላይ ፒፕል ቱ ፒፕል አዋርድ በተሰኘ ሽልማት ላይ በምርጥ ድርጅት (Best Rising Star Organization award) ዘርፍ ተሸላሚ ሆነ።

ፒፕል ቱ ፒፕል የተሰነው ድርጅት የተመሰረተው ከአገር ውጭ በሚኖሩ የሕክምና ባለሙያዎች ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ በሕክምና እና በሰብዓዊ ድጋፍ ላይ ተጽዕኖ የፈጠሩ ባለሙያዎች ዕውቅና ይሰጣሉ።

ዶ/ር ዓለማየሁ "ሁሉም ባለበት መታከም እንዲችል ማድረግ ብችል ትልቁ ስኬቴ ነው" ሲል ከቢቢሰ ጋር ቆይታ ባደረገበት ወቅት ተናግሯል።

ዶ/ር ዓለማየሁ ተማሪ እያለ ኢትዮጵያዊ ሐኪም ስትሆኑ ሦስት ነገር ነው የምታክሙት የሚለውን የመምህራቸውን ንግግር ያስታውሳሉ።

ይህም "ድህነትን፣ አለማወቅን እና በሽታን" መሆኑን የነገራቸው የሕክምና ባለሙያ፣ ብዙዎቻችን እያከምን ያለነው በሽታን ነው፤ ነገር ግን አለማወቅን እና ድህንትን ከጨመርንበት ብዙ ነገር መቀየር እንችላለን ብዬ አስባለሁ ይላል።

ዶ/ር ዓለማየሁ ለሁሉም ፓን አፍሪካ ሄልዝ በተሰኘው ድርጅቱ በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የአንገት በላይ ሕክምና ማስተካከል ከቻልን ተመሳሳይ ችግር ወዳለባቸውን የአፍሪካ አገራት በመንቀሳቀስ ሕክምናውን የመደገፍ ዕቅድ እንዳለው ተናግረዋል።