ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ፣ ፑቲን እና ዢ ጂንፒንግ በሚቀጥለው ሳምንት ለታሪካዊ የጋራ ስብሰባ እንደሚገናኙ ዋይት ሃውስ አስታወቀ
ዶናልድ ትራምፕ፣ ቭላድሚር ፑቲን እና ዢ ጂንፒንግ በሚቀጥለው ሳምንት ቻይና ውስጥ ከሚካሄድ የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ለመገናኘት ማቀዳቸውን ዋይት ሃውስ ገለጸ።
የአሜሪካ፣ ሩሲያ እና ቻይና መሪዎች ያደርጉታል የተባለው ይህ ታሪካዊ ስብሰባ የሚከናወነው፣ ትራምፕ በደቡባዊቷ ሼንዠን ከተማ በሚካሄደው የእስያ-ፓሲፊክ የኢኮኖሚ ትብብር ጉባኤ ላይ በሚሳተፉበት ወቅት እንደሚሆን የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ኦሊቪያ ዌልስ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ቃል አቀባይዋ "ፕሬዝዳንቱ ከሌሎች አጀንዳዎች በተጨማሪ በዓለም ላይ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎችን ስለመቀነስ እንደሚወያዩ በግልጽ አስቀምጠዋል፤ ፕሬዚዳንት ትራምፕ [የኒውክሌር መሣሪያዎች] መስፋፋት እጅግ አደገኛ እንደሆነ ያምናሉ" ብለዋል።
ኒውክሌር የታጠቁ እነዚህ የዓለም ኃያላን በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ የኢራን ጉዳይ ሊነሳ እንደሚችል ቢገመትም፣ የዩክሬን ጉዳይ ግን በአጀንዳነት አልተያዘም። ሞስኮ እና ቤጂንግ ስለውይይቱ እስካሁን አስተያየት አልሰጡም።
ከውይይቱ በኋላ በሦስቱ አገራት መካከል ስምምነት ይፈረማል ተብሎ እንደማይጠበቅ ስማቸው ያልተጠቀሰ አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣን ለዜና ወኪሎቹ ኤፒ እና ሮይተርስ ተናግረዋል።
ትራምፕ በኢኮኖሚ ትብብር ዙሪያ 21 አባል አገራት ለሁለት ቀናት ወደሚሰበሰቡበት ሼንዠን የሚደርሱት በሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ ነው።
ትራምፕ ሐሙስ ዕለት ከዢ ጂንፒንግ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። ይህ ውይይት፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በአውሮፓውያኑ 2025 በድጋሚ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ከቻይናው መሪ ጋር የሚያደርጉት አራተኛው ስብሰባ ይሆናል።
የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይዋ ዌልስ፣ "ፕሬዝዳንት ትራምፕ የቻይና ጉብኝታቸውን የሚያጠናቅቁት፣ በአሜሪካ ፕሬዝዳንት፣ በቻይና ሕዝባዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት እና በሩሲያ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት መካከል በሚካሄድ የሦስትዮሽ ስብሰባ ነው" ብለዋል።
ትራምፕ ወደ ቀጣናው በሚያደርጉት ጉዞ፣ ማክሰኞ ዕለት በፊሊፒንስ በሚካሄደው የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገራት ማኅበር ጉባኤ ላይም እንደሚገኙ ተገልጿል።
ቃል አቀባይዋ ይህንን የትራምፕ ጉዞ "ለአሜሪካ ሕዝብ ታሪካዊ ድሎችን የሚያስገኝ እና በኢንዶ ፓሲፊክ የአሜሪካን ጥቅም የሚያስከብር" ሲሉ ገልጸውታል።
አሜሪካ እና ሩሲያ ከዚህ ቀደም ደርሰውበት የነበረው የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች ቁጥጥር ስምምነት ባለፈው ዓመት የካቲት ላይ የቆይታ ጊዜ አብቅቷል።
የስምምነቱ መጠናቀቅ፣ የዓለም ግዙፍ የኒውክሌር መሣሪያ ክምችቶች ዋነኛ የሚባል የቁጥጥር ገደብ እንዳይኖርባቸው ያድርጋል።
በተጨማሪም የቀዝቃዛውን ጦርነት ለመፍታት እገዛ ያደረገውን የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ትብብር ተግባራዊነት እንዲያበቃ ምክንያት ሆኗል።
የተባበሩት መንግሥታት ሁለቱም አገራት ሳይዘገዩ አዲስ የስምምነት ማዕቀፍ ላይ እንዲስማሙ አሳስቧል።
ትራምፕ በበኩላቸው፣ የቀድሞውን ስምምነት፣ የጦር መሣሪያ ክምችቷን ስታሳድግ የቆየችውን ቻይናን በሚያካትት የተሻለ ውል የመተካት እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል።
የቀድሞ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣናት እና ተንታኞች ግን፣ ቤጂንግን እና ሞስኮን እንዲተባበሩ የማድረግ ሙከራ ከባድ መሰናክሎች ሊያጋጥመው እና ዓመታትን ሊፈጅ እንደሚችል በወቅቱ ለቢቢሲ አስረድተዋል።