በዩኬ በተመሳሳይ ወቅት ለአምስት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እየሠራ የነበረው ግለሰብ በማጭበርበር ክሶች ጥፋተኛ ተባለ

ካሺም ቾውዱሪ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በተመሳሳይ ወቅት በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሲሠራ የነበረው ግለሰብ በዘጠኝ የማጭበርበር ክሶች ጥፋተኛ ተባለ።

በምሥራቅ ለንደን የሚኖረው ካሺም ቾውዱሪ በአውሮፓውያኑ 2023 በአምስት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በተመሳሳይ ወቅት እየሠራ ደመወዝ ሲከፈለው ነበር።

የ56 ዓመቱ ግለሰብ በአምስቱ ሥራዎች 284,000 ፓውንድ ተከፍሎታል።

ዐቃቤ ሕግ "ሆነ ብሎ በመዋሸት እና የመንግሥት ሥርዓትን በመበዝበዝ" ከስሶታል።

በስምንት የማጭበርበር እና ራስን በሐሰተኛ መንገድ በማቅረብ ክሶች ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል።

ከፋይናንስ ጋር የተያያዙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ሳራ ሜሎ "በተመሳሳይ ወቅት በሁሉም መሥሪያ ቤቶች መቀጠር እንደማይችል እያወቀ ድርጊቱን ፈጽሟል" ብለዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም የአካባቢ፣ ምግብ እና የገጠር ጉዳዮች መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ "እንደ ሕዝብ አገልጋይ የተጣለበትን እምነት አጉድሏል" ብለዋል።

ካሺም ቾውዱሪ ከ2020 እስከ 2023 ባሉት ዓመታት ስምንት የሙሉ ጊዜ ሥራዎች ነበሩት።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አንደኛው ሥራ ከሌላኛው ጋር የሚጋጭ ቢሆንም በአጠቃላይ 350,000 ፓውንድ አግኝቷል።

የቅጥር ቅጽ ላይ የሥራ ሁኔታውን በተመለከተ ለቀረበት ጥያቄ የሰጠው ምላሽ ሐሰተኛ መሆኑን ዐቃቤ ሕግ ገልጿል።

በሌላ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ተቀጣሪ መሆኑን ሳያሳውቅ በተለያዩ ተቋማት መሥራት ቀጥሏል።

ዳይሜንሽያ (የመርሳት ሕመም) እና ካንሰር ያለባቸው እናቱን እያስታመመ እንደሆነ ስለተናገረም ከቤት እንዲሠራ ተፈቅዶለታል።

እናቱን ለመንከባበከብ ጊዜ ከመመደብ ይልቅ ግን በሥራ ላይ ሥራ መደራረቡን ዐቃቤ ሕግ አመልክቷል።

እናቱ በ2023 ሊሞቱ ወራት ሲቀራቸው በአካባቢ፣ ምግብ እና የገጠር ጉዳዮች፣ በጤና እና ማኅበራዊ አገልግሎት፣ በጤና ደኅንነት ቁጥጥር፣ በቢዝነስ እና ንግድ እንዲሁም በምግብ ጥራት ቁጥጥር መሥሪያ ቤቶች እየሠራ ነበር።

በቅጥሩ መሠረት በሳምንት እስከ 183 ሰዓታት እንዲሠራ ይጠበቅ ነበር። ይህም አንድ ሳምንት ካሉት ሰዓታት በላይ ነው።

ካሺም ቾውዱሪ በ2013 ከትምህርት ሚኒስቴር ሥራው ከተቀነሰ በኋላ በተፈጠረበት ጭንቀት ምክንያት የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች መሥራት መጀመሩን ተናግሯል።

ትኩረት ማጣት (ፒቲኤስዲ) ያለበት ካሺም "በጭንቀት፣ በፍርሃት እና በስሜት ቀውስ ውስጥ ስለነበርኩ ለሥራዎቹ ሳመለክት በትክክል አላሰብኩም" ብሏል።

ዐቃቤ ሕግ ሉሲ ኦርጋን ግን "ቃለ መሐላ ፈጽሞ ዋሽቷል፤ የማታለል መጠኑን ያሳያል" ብለዋል።

ለፍርድ ቤት ቃላቸውን የሰጡት አለቆቹ በሥራው ላይ ውጤታማ መሆን አለመቻሉን ተናግረዋል።

የአካባቢ፣ ምግብ እና የገጠር ጉዳዮች መሥሪያ ቤት ኃላፊ ዳን ማካትኒ "ምን መሥራት እንዳለበት ይነገረው ነበር" ብለዋል።

በቪዲዮ ሲደወልለት የቴክኒክ ችግር እንደገጠመው በመግለጽ ፊቱን አያሳይም ነበር። ለሁለት ዓመት በዚህ መሥሪያ ቤት ቆይቷል።

የሥራ ጫና መወጣት በማይችልበት ወቅት የሐኪም ፈቃድ ያስገባ ነበር። በአራቱ መሥሪያ ቤቶች የሐኪም ፈቃድ አስገብቶ በአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥራውን ቀጥሏል።

በጤና ደኅንነት ቁጥጥር መሥሪያ ቤት አለቃው የነበሩት አሊሻ አዳምስ እንዳሉት ለሦስት ወራት የሕክምና እረፍት ከወሰደ በኋላ ወደ ሥራ እንዲመለስ ለማድረግ ሞክረዋል።

በቪድዮ ሲደወልለት ጭምብል ለብሶ እያሳለ እንደነበርም ተናግረዋል። የታመመ ለመምሰል ነጭ ሜካፕ ተቀብቶ ነበር ሲሉም ገልጸዋል።

"የቪድዮ ስብሰባው ሲቀጥል እያላበው ነበር። ሲያልበው ሜካፑ መልቀቅ ጀመረ" ብለዋል።

ካሺም ግን ሜካፕ ተቀብቶ እንዳልነበረ ለፍርድ ቤት ቃሉን ሰጥቷል።

ካሺም የቪዲዮ ስብሰባውን የተቀላቀለው በአካባቢ፣ ምግብ እና የገጠር ጉዳዮች አድራሻው መሆኑን እንዳስተዋሉ አለቃው ተናግረዋል።

የቴክኒክ ችግር ነው የሚል መልስ ቢሰጣቸውም አላመኑትም።

ካሺም በስተመጨረሻ የተደረሰበት በየሁለት ዓመቱ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ላይ ፍተሻ የሚያደርገው ብሔራዊ የፀረ ማጭበርበር ክፍል በ2024 ምርመራ ሲያደርግ ነበር።

ወንድም እና እህቶቹ እንዳሉት እናታቸው ከመሞታቸው በፊት የቤቱን ድርሻ መጠን እንዲጨምሩለት ጫና ያሳድር ነበር።

ከእናቱ ቤት ግማሹን ለመውረስ በሚል እናቱን አስገድዶ ሰነዶች ማስፈረሙን በመግለጽም ከስሰውታል።

ባለ አራት ሕንጻው ቤት 2.1 ሚሊዮን ፓውንድ ያወጣል።

ዐይናቸው የደከመው እና እንግሊዘኛ የማይናገሩት እናቱ ምን ሰነድ ላይ እየፈረሙ መሆኑን እንደማያውቁ እህት እና ወንድሞቹ ተናግረዋል።

ካሺም የቀረበበትን ክስ አስተባብሏል። ፍርድ ቤት በቤተሰቡ ጉዳይ ብይን አልሰጠም።