የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ላይ ተቃውሟቸውን በማሰማት "የፈጣሪን ሥራ እየተከላከልን ነው" የሚሉት መነኮሳት

በመደዳ የተቀመጡ መነኩሴዎች
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በርካታ ሰዎች የካቶሊክ መነኮሳትን ሲመለከቱ የሚያስቡት አለ፤ ሲስተር ሱዛን ፍራንሷ ግን እንደዚያ አይደሉም።

እርሳቸው እንደተለመደው የመነኮሳቱን አልባሳት አይለብሱም። በቲክ ቶክ ላይ ንቁ ተሳትፎ ያደርጋሉ።

በቲክቶክ ገጻቸው ላይ የሚታየው አብዛኛው በዩናይትድ ስቴትስ ኒው ጀርሲ ውስጥ በሚገኝ የኢሚግሬሽን ማቆያ ማዕከል ውጭ የተቀረጹ ቪዲዮዎች ናቸው። በዚያም ለስደተኞች እና ለቤተሰቦቻቸው ይሟገታሉ።

ሲስተር ሱዛን በተለየ ዓይነት እንቅስቃሴም ትኩረት እያገኙ መጥተዋል።

እርሳቸው እና በዩናይትድ ስቴትስ እና በዩናይትድ ኪንግደም 88 እህቶች ያሉት የቅዱስ ዮሴፍ የሰላም እህትማማቾች ጉባኤ ውስጥ ያሉ መነኮሳት ራሳቸውን ባለአክሲዮኖች ተሟጋቾች በማለት ይጠራሉ።

ያላቸውን ተቀባይነት እንደ ዕድል በመጠቀም እንደ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የነባር ተወላጆች የመሬት መብቶች እና ዘርን መሠረት አድርገው የሚፈጸሙ ኢ- ፍትሃዊነቶች እንዲፈቱ ይታገላሉ።

"የመነኮሳቱ ገንዘብ ያዥ እንደመሆኔ የጋራ ጥቅምን የሚያስከብሩ ነገሮች እንዲያስፋፉ ስንጠይቅ ፍላጎታችንን በመወከል የምቀርበው እኔ ነኝ" ይላሉ።

የቅዱስ ዮሴፍ የሰላም እህቶች ሰላምንና ፍትህን ለማስፈን እንዲሁም ችግር ላይ ያሉ ሰዎችን ለመርዳት ራሳቸውን የሰጡ የካቶሊክ መነኮሳት ቡድን ነው።

ቡድኑ በተለያዩ ኩባንያዎች ውስጥ የአክሲዮን ባለቤት ድርሻ አለው። 'ሲስተርስ ኦፍ ሴንት ጆሴፍ ኦፍ ፒስ' እና 'በፓላንቲር ቴክኖሎጂስ' ውስጥ አክሲዮኖች ያሉት ሲሆን ይህም ትርፍ ማግኘትን ያለመ ሳይሆን ኩባንያው ፍትሃዊ የሆኑ አካሄዶችን መከተሉን መከታተል እና ጥያቄ ማንሳት ላይ ያተኮረ ነው።

በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እድገት ላይ የሚያተኩረው የሊቀ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ የኢንሳይክሊካል ደብዳቤ፣ ማግኒፊካ ሂውማኒታስ
የምስሉ መግለጫ, የሊቀ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ የኢንሳይክሊካል ደብዳቤ፣ ማግኒፊካ ሂውማኒታስ፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እድገት ላይ ያተኮረ ነው
Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በቅርቡ ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ፓላንቲር ቦርድ ስጋታቸውን እንዲፈታላቸው ለማድረግ ሞክረዋል።

መነኮሳቱ የኩባንያውን ሰው ሠራሽ አስተውሎት ሶፍትዌር በአሜሪካ የኢሚግሬሽን እና የጉምሩክ አስፈጻሚ (አይስ) እና በሌሎች የግዛት ቢሮዎች "ስደተኞችን ለማሰር እና ለማባረር ክትትል እና ዒላማ ለማድረግ" እየተጠቀሙበት እንደሆነ ያምናሉ።

ይህም የሰብዓዊ መብቶችን ሊጥስ የሚችል መሆኑን ተከራክረዋል።

በተለይም መነኮሳቱ ፓላንቲር የሰብዓዊ መብቶች ተጽዕኖ ግምገማ እንዲያካሂድ ፈልገው ነበር። ይህም ምርቶቹ እና አገልግሎቶቹ እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚውሉ በማየት ማንኛውንም አሉታዊ ተጽእኖ ለመቀነስ ይረዳል በሚል ነው።

የባለአክሲዮኖች ምክረ ሃሳብ በመባል የሚታወቀውን የተወሰነ እርምጃ እንዲወሰድ የሚጠይቅ ረቂቅንም ተጠቅመዋል፤ ከዚያም በኩባንያው ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ድምጽ ይሰጣል።

ይህ ጥረታቸው 13 በመቶ ድምጽ ብቻ አግኝቷል። ነገር ግን ሲስተር ሱዛን አሁንም እንደ ድል አድርገው ይመለከቱታል። የኩባንያው መስራቾች የአክስዮኖቹን 49.9 በመቶ ድምጽ ይቆጣጠራሉ ብለው ያስረዳሉ።

"ከጠቅላላው ድምጽ ውስጥ 56 በመቶ የሚሆኑት ከመነኮሳቱ ጋር ተስማምተዋል" በማለት የሚያስረዱት መነኩሴዋ "ብዙ ባለአክሲዮኖች ከእኛ ጋር እንዲስማሙ ማድረግ ራሱ የሚያስረዳው ነገር አለ።"

ቢቢሲ ከፓላንቲርን ምላሽ ለማግኘት ቢጥርም ኩባንያው ግን ምላሽ አልሰጠም።

ይሁን እንጂ ኩባንያው ቀደም ሲል ለባለአክሲዮኖች በሰጠው መግለጫ፣ የመነኮሳቱ ድርጊት "በፓላንቲር ሥራ ላይ በተፈጠሩ አለመግባባቶችና ስህተቶች ላይ የተመሰረተ" እንደሆነ እና ፓላንቲር የዳታ ኩባንያ እንዳልሆነ፣ የግል መረጃዎችን እንደማይሸጥና እንደ የመረጃ ሃሰሳ አገልግሎት እንደማያቀርብ ተናግሯል።

አይስን የሚቃወም ሰልፍ ላይ መፈክር የያዙ ሰዎች
የምስሉ መግለጫ, የአይስ እርምጃዎች በመላው አሜሪካ የሚገኙ ማኅበረሰቦችን ከፋፍሏል። በሐምሌ ወር አንድ ሰው በአይስ ሠራተኞች ከተተኮሰበት በኋላ በሜይን የሚገኙ ነዋሪዎች ተቃውሟቸውን አሰምተዋል

ምርጫው የተካሄደው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በግንቦት ወር የመጀመሪያውን የአስተምህሮት ሰነዳቸውን ወይም ኢንሳይክሊካል ካቀረቡ ከሁለት ሳምንታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ነው።

ይህ ሰነድ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሰብዓዊነትን ከመቆጣጠር "መታቀብ" እንዳለበት አስጠንቅቋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የሰው ልጅ ሰብዓዊነት "ለጋራ ጥቅም" ተግባራዊ መሆን እንዳለበት እና የሰው ልጅ ክብር መጠበቅ እንዳለበት ተከራክረዋል።

የድምፅ መስጫው ጊዜ ከሊቀ ጳጳሱ ሰነድ ጋር መግጠሙ አጋጣሚ እንደነበር የሚናገሩት መነኩሴዋ "የኢንሳይክሊኩን ጽሑፍ ብዙ ጊዜ አንብቤዋለሁ፤ ይህም ከጥረታችን ጀርባ ያለውን ሁሉ ያረጋግጣል።" ብለዋል።

የፓለንቲር አርማ
የምስሉ መግለጫ, መነኮሳቱ በፓላንቲር ውስጥ የአክሲዮን ድርሻ ስላላቸው የኩባንያውን የንግድ አሠራር በተመለከተ በይፋ የመጠየቅ መብት አላቸው

መነኮሳቱ ፓላንቲር ባለአክሲዮኖች ወይም የቦርድ አባላቱ ሥነ ምግባራዊ ሲሉ የጠሯቸውን ጉዳዮች እንዲፈቱ ጫና ለማድረግ የሚከታተሉት ብቸኛው ኩባንያ አይደለም።

በዓለም ላይ ካሉት ትላልቅ የባንክ ተቋማት አንዱ የሆነውን ሲቲግሩፕን በአማዞን ተፋሰስ ውስጥ የነዳጅ ማውጣት ፕሮጀክቶችን በገንዘብ በመደገፉ ተቃውመውታል።

መነኮሳቱ በአካባቢው ያሉ ነባር ሕዝቦች ጉዳት ስላሳሰባቸው ሲቲግሩፕ በጉዳዩ ላይ ሪፖርት እንዲያወጣ ጠይቀው ነበር።

ባንኩም እንደ አውሮፓውያኑ በሚያዝያ ወር 2024 መግለጫ አውጥቷል።

ሲስተር ሱዛን እንዲህ ያሉ ምክረ ሃሳቦች ብዙ ድምጾች ማግኘት ሳትችሉ ስትቀሩ በውጤቶች ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ውጤታማ መንገድ ናቸው ወይ ተብለው ሲጠየቁ ስኬት በምትለካበት መንገድ ላይ የተመሰረተ ነው ሲሉ ይመልሳሉ።

"የመጀመሪያው ምክረ ሃሳባችን የቀረበው ኮልጌት-ፓልሞሊቭ ለሚባል ኩባንያ እአአ በ1976 ነው። ይህ ኩባንያ በማስታወቂያ ላይ ስላሳየው ጾተኛነት [ሴቶችን ያሳየበትን መንገድ] ነበር የተከላከልነው።"

ባለአክሲዮኖች ኩባንያው የጾታ መድልዎ እንዲፈታ ጫና አሳድረዋል። ኩባንያው ምክረ ሀሳቡን አላስፈላጊ ነው በማለት ውሳኔውን ተቃውሞ ውድቅ አድርጓል።

ይህ ቢሆንም ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላም ሲስተር ሱዛን ተስፋ አልቆረጡም።

"የጾታዊነት ዝንባሌ ከማስታወቂያ ተወግዷል? አልተወገደም። አሁን ከ1970ዎቹ ከነበረው የተለየ ነው? ከሆነ ጥያቄው አዎ።"

"ለእነዚህ መነኮሳት እንዲሁም ውሳኔዎቻቸው በእሴቶቻቸው እና በእምነታቸው በሚመሩ አብዛኛዎቹ ባለሀብቶች ዘንድ፣ ስኬት ማለት አስፈላጊ ጥያቄዎች በኩባንያው የዳይሬክተሮች ቦርድ እና በከፍተኛ አመራሮች እንዲነሱና እንደሚወያዩባቸው ማረጋገጥ ነው።"

ሲስተር ሱዛን ንግግር ሲያደርጉ
የምስሉ መግለጫ, ሲስተር ሱዛን ጥያቄዎችን በአደባባይ መጠየቅ እና ችግር አለባቸው ስለሚባልባቸው ኩባንያዎች በይፋ መናገር አንዳንዴ በቂ ይሆናል ብለው ያምናሉ

ስለዚህ እንደ ባለአክሲዮኖች፣ መነኮሳቱ ገንዘብ የሚያገኙት ከተተቹባቸው ኩባንያዎች ነው? አዎ ይላሉ ሲስተር ሱዛን የሚጣረስ መሆኑን በመግለጽ።

ነገር ግን ከእነዚህ ኢንቨስትመንቶች የሚያገኙት ትርፍ ለአረጋውያን መነኮሳት የጤና እንክብካቤ ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን፣ አነስተኛ መጠን ያለው አክሲዮን ብቻ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ሲስተር ሱዛን በተጨማሪም የጦር መሳሪያ አምራቾችን እና ነዳጅ ማምረትን ጨምሮ ጨርሶ ኢንቨስት የማያደርጉባቸው አንዳንድ ኩባንያዎች እንዳሉ አጥብቀው ይናገራሉ።

ነገር ግን ከትላልቅ ኮርፖሬሽኖች ጋር መተባበር እና ውሳኔዎቹን በሚያሳልፉበት ወቅት መገኘት እንዳለባቸው ይከራከራሉ። "ራሳችንን ከሥልጣን ማዕከላት ብናርቅ. . . ነገሮች እንዴት እንደሚከናወኑ ምንም ዓይነት አስተያየት መስጠት አንችልም።"

መነኮሳት በለምለም ሳር ላይ ሆነው
የምስሉ መግለጫ, ሲስተር ሱዛን እና ሌሎች መነኮሳት ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ዓላማ እንደሌላቸው፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ፍጥረትን እንደሚከላከሉ ይናገራሉ

የቅዱስ ዮሴፍ የሰላም እህቶች ጉባኤ የተቋቋመው እአአ በ1884 በሊቀ ጳጳስ ሊዮ 13ኛ ሥር ሲሆን ሥራቸውም የአሁኑን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ስሙን እንዲወርሱ አነሳስቷቸዋል።

ሲስተር ሱዛን እንደሚሉት የመጀመሪያው ሊዮ ስለ ጉልበት ብዝበዛ የካቶሊክ ማኅበራዊ ትምህርት የመጀመሪያውን ሰነድ የጻፉ ሲሆን ሁለቱም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በሰዎች ሕይወት ውስጥ አስፈላጊ በሆኑ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ተሰማርተዋል።

ስለዚህ አንዳንዶች የመነኮሳት ቡድን የንግድ አካሄዶችን እንደ ፖለቲካዊ ሊቆጠር በሚችል መልኩ ተጽዕኖ ለማሳደር መሞከር አለባቸው ወይ የሚለውን ጥያቄ ሲያነሱ ሲስተር ሱዛን ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ግብ የለንም ሲሉ ይመልሳሉ።

"የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሃሳብ አናስተጋባም። የእግዚአብሔርን ፍጥረት እና የሰብዓዊ መብቶችን ሁሉ እንደግፋለን። እና ያ ፖለቲካዊ ከሆነ ይሁን።"