የጣሊያን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የግል ሰነዶቻቸው በመረጃ መንታፊዎች መሰረቁን ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ታጃኒ አገራቸው ለዩክሬን በምታደርገው ድጋፍ ምክንያት በ"ሳይበር ወንጀለኞች" ዒላማ መሆናቸውን እና የግል መረጃዎቻቸው መጋራታቸውን ተናገሩ።
ታጃኒ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባጋሩት መልዕክት፣ "ለቀናት የሳይበር ወንጀለኞች የግል መረጃዎቼን በዳርክ ዌብ (Dark Web) ላይ እያሰራጩ እና ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት እየፈለጉ ነው፤ ይህም ለአዳዲስ ዛቻዎችና ማስፈራሪያዎች እንድጋለጥ አድርጎኛል" ብለዋል።
ሚኒስትሩ የደረሱባቸውን ዛቻዎች ዝርዝር ባይገልጹም፣ የመረጃ መዝባሪዎቹ ቤተሰባቸውንም ዒላማ ለማድረግ እየሞከሩ መሆኑን አስታውቀዋል።
ዳርክ ዌብ በጉግል እና በሌሎች መደበኛ የመፈለጊያ መንገዶች የማይገኝ ስውር የኢንተርኔት ክፍል ሲሆን፣ ልዩ ሶፍትዌር መጠቀምን ይጠይቃል።
"በዩክሬን ጉዳይ በያዝነው አቋም ነው ዒላማ ያደረጉኝ" ሲሉ ታጃኒ ተናግረዋል።
"የአንድ ሉዓላዊ አገርን ነፃነት መከላከል፣ እንዲሁም ለአንድ አገር ዴሞክራሲና ነፃነት ግልጽ ድጋፍ መስጠት በእነዚህ ወንጀለኛ ቡድኖች ዐይን አደገኛ ተግባር ሆኖ ተገኝቷል" ብለዋል።
የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ክስተቱን ሩሲያን ከሚደግፉ የሳይበር መዝባሪዎች ጋር በማያያዝ፣ ለታጃኒ ያላቸውን ሙሉ ድጋፍ ገልጸዋል።
ሜሎኒ ባወጡት መግለጫ "የመንግሥት ኃላፊዎች ሚስጥራዊ የግል መረጃዎች ለሽያጭ መቅረባቸው ከፍተኛ ስጋት የሚፈጥር ጉዳይ ነው፤ በተቻለ ሁሉ በርትተን ልንታገለው ይገባል" ብለዋል።
ሩሲያ ለቀረቡባት ውንጀላዎች በይፋ ምላሽ አልሰጠችም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በተጨማሪም "ሐሰተኛ ምስሎች መሰራጨታቸውን" በተመለከተ ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል። እነዚህ ምስሎች በጣሊያን ተቃዋሚ ፓርቲ አባላት መጋራታቸውን ቢናገሩም፣ የምስሎቹን ይዘት በዝርዝር አልገለጹም።
የጣሊያን መንግሥት በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ውስጥ ለዩክሬን ሰብዓዊና ወታደራዊ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።
የጣሊያን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርም የሆኑት አንቶኒዮ ታጃኒ በበኩላቸው፣ መንግሥት ያሉትን ስጋቶች በከፍተኛ ትኩረት እየተከታተለ መሆኑን ገልጸዋል።
































