ዓለም ሞቃዲሾን የሚመለከትበትን ዐይን እየቀየረች ያለችው ወጣቷ ሶማሊያዊት

የሶማሊያ የባህር ዳርቻ እና ዘንባባ
የምስሉ መግለጫ, ሶማሊያ የአፍሪካ ረጅሙ የባሕር ዳርቻ ባለቤት ናት
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ሶማሊያዊቷ ወጣት ዓለም አገሯን በአጥፍቶ ጠፊዎች እና ክላሽንኮቭ ባነገቱ ወጣት ወንዶች ምሥል ሳይሆን በሕንድ ውቅያኖስ ላይ በተነጠፈው ወርቃማው አሸዋ እና በዘንባባዎቿ እንዲያውቃት ትሻለች።

ሱሲዲ አብዱል ፈታህ አብዱል ኸድር ሞቃዲሾን ከዜና አርዕስት ባለፈ ከሚያስጎበኙ በርካታ አስጎብኝዎች መካከል አንዷ ናት።

የ23 ዓመቷ አስጎብኝ የጉብኝት መርሃ ግብሯ ለዓይን የሚማርኩ የባሕር ዳርቻዎችን ከማሳየት ያለፈ ነው። የቀድሞ ቅኝ ገዥዎች የኦቶማን እና የጣሊያን ተፅዕኖ ያለባትን ሞቃዲሾን ታሪካዊ ማንነት ለማሳየት ጎብኝዎችን የአሳ ገበያ፣ የግመል ስጋን ጨምሮ የሶማሌን ባህላዊ ምግቦች እንዲካፈሉ ታደርጋለች።

ሱሲዱ በርካታ ጎብኝዎች በዓመታት የደኅንነት እጦት ምክንያት የተቀረፀ አስተሳሰባቸውን ይዘው ስለሚመጡ ስለከተማዋ የሚጠብቁት ነገር እንዳለ ትናገራች።

"በአብዛኛው በአገሪቱ ውበት እና በሰዎች እንግዳ ተቀባይነት ይገረማሉ" ትላለች።

አስጎብኝነት በደሟ ውስጥ የሆነው ሱሲዲ፤ አባቷ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ጋዜጠኞች፣ የፎቶግራፍ ባለሙያዎች እና ጎብኝዎችን በመላው ሶማሊያ ሲያዘዋውሩ ቆይተዋል።

ከሦስት ዓመት በፊት እንደ የትርፍ ሰዓት ማሳለፊያ የጀመረችው አስጎብኝነት ዛሬ የምትወደው ሥራ ሆኗል።

ሱሲዲ አብዱል ፈታህ አብዱል ኸድር
የምስሉ መግለጫ, ሱሲዲ ጉብኝዎች "ውቢቷን እና እንግዳ ተቀባይ የሆነችውን" ሞቃዲሾን እንዲያጣጥሙ ትፈልግለች

አሁን ሱሲዲ ከአባቷ እና ሌሎች የአስጎብኝዎች ቡድን ጋር የምትሰራ ሲሆን፤ ሰፊ ተደራሽ ለመሆን እና የሶማሊያን ሊገመት የማይችል ውበት ለማሳየት ማኅበራዊ የትስስር ገፆችን ይጠቀማሉ።

ሱሲዲ በጣት የሚቆጠሩ አስጎብኝዎች ብቻ እንዳሉ በማመላከት ቱሪዝም ለሶማሊያ በአንፃራዊነት አዲስ የሚባል ዘርፍ ነው ትላለች።

ሥራውም ወቅቱን የሚጠብቅ ቢሆንም ሱሲዲ በሳምንት አምስት ጎብኝዎች ካሉ እንደስኬት እንደሚታይ ትናገራለች።

በርካታ ጎብኝዎች አሁንም ድረስ በአገሪቱ የደኅንነት ስጋት አላቸው።

ትላልቅ አሳዎች የተሸከመ ወንድ፤ ከጀርባው የባሕር ዳርቻ ላይ የቆሙ ሰዎች
የምስሉ መግለጫ, በሞቃዲሾ ገበያ የተለያዩ ዝርያ ያላቸው አሳዎች ይገኛሉ

እንደ አውሮፓውያኑ በ1991 የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት ከወደቀ በኋላ ሞቃዲሾ ለአስርት ዓመታት በእርስ በእርስ ጦርነት፣ ውድመት እና መፈናቀል ታምሳለች።

አብዛኛው የከተማዋ ክፍል ወደ ፍርስራሽ የተቀየረ ሲሆን፤ መሠረታዊ አገልግሎቶች እና መሠረተ ልማቶች በአብዛኛው ተቋርጠዋል።

እአአ በ2011 አልሸባብ አብዛኛውን የከተማዋን ክፍል ለቅቆ መውጣቱን ተከትሎ ሞቃዲሾ ቀስ በቀስ እየተሻሻለች ነው።

ዛሬ ሞቃዲሾ እያደገች ያለች የንግድ ማዕከል ስትሆን፤ አሁንም ግን የደኅንነት ስጋት እና የጦርነት ውርስ የዕለት ከዕለት ሕይወት ላይ ጥላውን ማጥላቱ አልቀረም።

እአአ በ2024 10 ሺ የሚሆኑ ጎብኝዎች ሶማሊያን ጎብኝተዋል። ይህም ቀድሞ ከነበረው ዓመት 50 በመቶ ብልጫ እንዳለው የአገሪቱ ቱሪዝም ቢሮ መረጃ ያሳያል።

በርካታ ጎብኝዎች ወደ ሶማሊያ ከማቅናታቸው በፊት ስለ ደኅንነታቸው ይጠይቃሉ። በቆይታቸውም በከተማዋ ዙሪያ የተዘረጉ የደኅንነት ፍተሻ ኬላዎች ይገጥሟቸዋል።

ባሕር ዳርቻ ላይ እየተዝናኑ ያሉ ሰዎች
የምስሉ መግለጫ, ሊዶ የባሕር ዳርቻ በሞቃዲሾ ሰዎች ለመዝናናት በአብዛኛው የሚመርጡት ነው

ሱሲዲ በአጠቃላይ በከተማዋ ጎብኝዎች የሚያደርጉት ቆይታ አዎንታዊ ነው ትላለች።

"ከዜናዎች እና ከየቦታው የሚሰሙት እና በአገሪቱ ውስጥ የሚያዩት አንድ አይደለም።"

ምንም እንኳ አንዳንዶች ሞቃዲሾ ወጣት ሴት አስጎብኝ ሆና እንድትሠራ አስተማማኝ መሆኑን ቢጠራጠሩም፤ ሱሲዲ ግን በሥራዋ ለመቀጠል ቁርጠኛ ናት።

ጎብኝዎች በአመዛኙ የማትታየውን ሶማሊያን እንዲጎበኙ ትፈልጋለች።

ሶማሊያ የአፍሪካ ረጅሙ የባሕር ዳርቻ ያላት አገር ስትሆን፤ ከሕንድ ውቅያኖስ እስከ ኤደን ባህረ ሰላጤ ድረስ 3 ሺ ኪሎ ሜትር የሚረዝም ዳርቻ ባለቤት ናት።

የባሕር ዳርቻዎች፣ የአሸዋ ክምሮች፤ እንደ ሞቃዲሾ ያሉ የክፍለ ዘመናት ባህል እና ጥንታዊ ንግድ ያላት ታሪካዊ የባሕር ዳርቻ ከተማ ለጎብኝዎች ቀልብን የሚስቡ ናቸው።

ለበርካታ ጎብኝዎች የአገሪቱ ዝና እና በጉብኝታቸው የሚያገኙት ለየቅል ናቸው። በጉብኝታቸው ደስተኞች እንደሆኑም ይናገራሉ።

ለሱሲዲ ሞቃዲሾን ማስጎብኘት ከሥራ በላይ ነው።

ለእርሷ እያንዳንዱ ጎብኝ የሞቃዲሾን ሙሉ ታሪክ ለመንገር እድል ነው።