የእስራኤል ፕሬዝዳንት የተቃዋሚ መሪው አይዘንካት መንግሥት እንዲመሰርቱ ኃላፊነት ሰጡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የእስራኤል ፕሬዝዳንት የተቃዋሚ መሪው ጋዲ አይዘንካት አዲስ ጥምር መንግሥት እንዲመሰርቱ ኃላፊነት እንደሰጡ ተናገሩ።
ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ቡድንም ሆነ የአይዘንካት ቡድን ክነሴት በሚባለው በእስራኤል ፓርላማ አብላጫ ድምፅ ማግኘት አለመቻላቸውን ተከትሎ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ሲመካከሩ ሰንብተዋል።
አይዘንካት አዲስ አስተዳደር ለመመስረት 28 ቀን ተቆርጦላቸዋል። የተሰጣቸው ቀነ ገደብ በ14 ቀናት ሊራዘም የሚችል ነው።
የቀድሞው የጦር አዛዥ ጋዲ አይዘንካት በኤክስ ገፃቸው "አስቸኳይ ብሔራዊ መንግሥት ለመመስረት አሁን ጊዜው ነው። ይህ እንደሚገባን ለማረጋገጥ ሁሉንም አደርጋለሁ" ብለዋል።
በእስራኤል ታሪክ አንድም የፖለቲካ ፓርቲ አብላጫ ድምፅ አግኝቶ አሸንፎ አያውቅም። ይህም ማለት ሁሉም የአገሪቱ መንግሥታት የጥምር መንግሥት ናቸው።
የኔታኒያሁ ቀኝ ዘመም ሊኩድ ፓርቲ እና አክራሪ እና ኦርቶዶክስ አይሁድ አጋሮቹ 120 ወንበሮች ካሉት ክነሴት 53 ወንበሮችን ሲያሸንፉ፤ የአይዘንካት ማዕከላዊ ያሸር ፓርቲ እና ሦስት ተቃዋሚ የአይሁድ ፓርቲዎች ጥምረት 48 ወንበሮችን አሸንፈዋል።
ሁለት የአረብ ጥምረቶች 'ዩናይትድ አረብ ሊስት' እና 'ጆይንት ሊስት' የአረብ መራጮች በገፍ ድምፅ መስጠታቸውን ተከትሎ በጋራ ያልተጠበቀ 19 ወንበሮችን በእጃቸው አስገብተዋል።
ይህም ፓርቲዎቹን ንጉስ አንጋሽ አድርጎ አስቀምጧቸዋል። ይሁን እንጂ ከአንድ የአይሁድ ፓርቲ በስተቀር ሁሉም ፓርቲዎች መንግሥት ለመመስረት አብረዋቸው እንደሚሰሩ ከምርጫው በፊት ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ሄርዞግ በሳምንቱ ውስጥ ከሁሉም ፓርቲዎች ጋር ከተመካከሩ በኋላ መንግሥት ለመመስረት የመጀመሪያውን እድል ለአይዘንካት እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
ከፕሬዝዳንቱ ቢሮ ይፋ የሆነ መግለጫ ሄርዞግ ውሳኔውን ለአይዘንካት እና ኔታኒያሁ ማስታወቃቸውን ጠቅሷል።
በክሰኔት አባል ሆነው የተመረጡ ተወካዮች ጋር በተደረገ ምክክር ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን አይዘንካት 67 የጥቆማ ድጋፍ ሲያገኙ፤ ኔታኒያሁ ደገሞ 46 ድጋፍ ማግኘታቸውን መግለጫው ገልጿል።
ፕሬዝዳንቱ ጥምር መንግሥት ለመመስረት የተሻለ እድል አለው ብለው የሚያምኑትን የመምረጥ ስልጣን አላቸው። አብላጫ ወንበር ያለውን ፓርቲ መሪ የመምረጥ ግዴታ የለባቸውም።
የእስራኤል የምርጫ ውጤት መንግሥት ለመመስረት ሦስት አማራጮችን አመልክቷል።
ኔታኒያሁ እና አይዘንካትን ያጣመረ ብሔራዊ የአንድነት አስተዳደደር፣ ኔታኒያሁ እና ከአይዘንካር አፈግፍገው ከሚወጡ ፓርቲዎች ጋር ቀኝ ዘመም ጥምረት ወይም በአይዘንካት የሚመራ እና በአረብ ፓርቲዎች የሚደገፍ መንግሥት አማራጮች ናቸው።
አይዘንካት እና ሁሉም የቡድናቸው አባላት ከዚህ ቀደም ከአረብ ፓርቲዎች ጋር መንግሥት ለመሆን አሻፈረኝ ብለዋል። ይሁን እንጂ በሁለቱ ቡድኖች መካከል ስምምነት መድረስ እንደሚቻል ጭምጭምታዎች አሉ።
አይዘንካት ከአክራሪ ኦርቶዶክስ አይሁድ ፓርቲዎች ጋር ስምምነት ለማሰር መሞከርም ይችላሉ። ነገር ግን ፈታኝ እንደሚሆን ይጠበቃል።
እአአ በ2020 ከሦስት መለያየት ያልቻሉ ምርጫዎች ከተደረጉ በኋላ ኔታኒያሁ እና ተቀናቃኛቸው ቤኒ ጋንትዝ መሪነትን በየተራ ለማድረግ የጋራ ሥልጣን ስምምነት ደርሰዋል።
































