በግብፅ ሁለት ባቡሮች ተጋጭተው በደረሰ አደጋ ሰባት ሰዎች ሲሞቱ ከ100 በላይ ጉዳት ደረሰባቸው

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
በግብፅ ከተማ ጊዛ አቅራቢያ ትናንት በደረሰ የባቡር አደጋ ቢያንስ ሰባት ሰዎች ሲሞቱ ከ100 በላይ ሰዎች ጉዳት ደረሰባቸው።
የአገሪቷ የባቡር ትራንስፖርት ባለሥልጣን እንደገለጸው አደጋው የደረሰው ከካይሮ እና ከጊዛ ከተማ ተነስተው ወደ ደቡባዊ አቅጣጫ የሚጓዙ ሁለት ባቡሮች በመጋጨታቸው ነው።
የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች የሕይወት አድን ጥረት እያደረጉ ሲሆን ነዋሪዎች የተጎዱ ሰዎችን ለማውጣት የተገለበጡትን ፉርጎዎች ሲያስሱ ከሥፍራው የወጡ ምስሎች አሳይተዋል።
የግብፁ ፕሬዚደንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ፣ ባለሥልጣናት "የአደጋውን መንስኤ እንዲመረምሩ እና ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘውን ተጠያቂ እንዲያደርጉ" ትዕዛዝ ሰጥተዋል።
የሕዝብ አቃቤ ሕግ ጽ/ቤት የሟቾቹ ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል አስጠንቅቋል።
በአካባቢው የሚገኙ ሆስፒታሎች በርካታ ተጎጂዎችን እያስተናገዱ በመሆናቸው በከፍተኛ ተጠንቀቅ ላይ እንደሚገኙም መንግሥት ገልጿል።
የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር ኻሊድ አብደል ጋፋር በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች የአጥንት ስብራት እና የጭንቅላት ጉዳት ሕክምና እየተደረገላቸው ነው ብለዋል።
በአደጋው ከሞቱት መካከል የአንደኛው ባቡር ሹፌር እንደሚገኝበትም ሚኒስቴሩ አሳውቋል።
የግብፅ ቀይ ጨረቃም በሥፍራው ለተጎጂዎች እና ለተጎጂ ቤተሰቦች ድጋፍ እና የሥነ ልቦና እገዛ እያደረኩ ነው ብሏል።
ከተጋጩት ባቡሮች አንደኛው፣ ከካይሮ ተነስቶ ወደ አስዋን እያመራ ከነበረው ባቡር ጋር ሲጋጭ ከጊዛ ከተማ ወደ በደቡባዊ ካይሮ ወደምትገኘው ፋዮም እየተጓዘ ነበር።
አደጋውን ተከትሎ ፍርስራሽ ለማፅዳት ከጊዛ ተነስቶ ወደ ላይኛው የግብፅ አካባቢ የሚደረግ የባቡር ጉዞ ተከልክሏል። ክልከላው እስከመቼ ጊዜ እንደሚቆይ የባቡር ትራንስፖርት ባለሥልጣኑ ያለው ነገር የለም።
በካፍር አማር እና በአልራቅ የባቡር ጣቢያዎች መካከል በሚገኘው አል አያት አካባቢ የባቡር አደጋ ሲያጋጥም ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። እአአ የካቲት 2022 በዚያው አቅራቢያ ከካይሮ ወደ ሉክሶር እየተጓዘ በነበረ ባቡር ላይ የእሳት አደጋ ተነስቶ በርካታ ሰዎች የሞቱበት አደጋ አጋጥሟል።
በዚህ አደጋ ከ370 በላይ ሰዎች መሞታቸው በመንግሥት የተመዘገበ ሲሆን አንዳንዶች ቁጥሩ ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችል ይገምታሉ።
በ2009 እንዲሁ በዚያው አካባቢ በደረሰ ሌላ የባቡር አደጋ በርካቶች ሞታዋል።
የአሁኑን አደጋ ተከትሎ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ሥልጣናቸውን እንዲለቁ እየተጠየቀ ነው።
የውጭ መሪዎች እና ተወካዮች በአደጋው የተሰማቸውን ሐዘን እያገለጹ እና ለተጎጂዎች ድጋፋቸውን እያሳዩ ሲሆን ከእነዚህ መካከል የሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በግብፅ የቱርክ አምባሳደር ይገኙበታል።
































