እስከ 160 ሺህ ብር የሚከፈልበት በኢትዮጵያ የሚደረገው የፀጉር ንቅለ ተከላ

የሳሳ ፀጉሩን በስልክ ላይ የሚመለከት ሰው
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

ከልጅነት ጀምሮ ቃለአብ ፀጉሩን ይወደው ነበር። ሉጫና የሚያምር ፀጉር እንደነበረው የሚናገረው ቃለአብ፣ 18 ዓመት ከሞላው በኋላ ፀጉሩ መሳሳት እና ወደ ኋላ መሸሽ መጀመሩን አስተዋለ።

ከዚያ ጀምሮ ፀጉሩን ወደ ግንባሩ በማምጣት የሳሳውን ክፍል ለመሸፈን ይሞክር እንደነበር ያስታውሳል። ከዓመት ወደ ዓመት ፀጉሩ እየሳሳና ወደ መመለጥ ደረጃ እያደገ ሲሄድ፣ የእሱም ጭንቀት በዛው ልክ ጨመረ።

የራስ ፀጉሩን ሙሉ በሙሉ መላጨት እየሳሳ የነበረውን ፀጉሩን አምኖ እንዲቀበል እንደሚያደርገው ያሰበው ቃለአብ ጫኔ፣ በመስታወት ያየው ገፅታ ግን ከጠበቀው ፈፅሞ የተለየ ነበር።

ራሱን በመስታወት ሲመለከት የሚያየው ፊት የራሱ መሆኑን ለማመን ተቸገረ።

". . . ሌላ ሰው፣ ሌላ ፊት፣ ሌላ ትልቅ ሰውዬ" ሲል ያንን ጊዜ ያስታውሳል።

ይህ ነገር ለቃለአብ የመልክ ለውጥ ብቻ አልነበረም። ፀጉር የፊት ገጽታን እንደሚቀይርና ከዕድሜው በላይ እንዳረጀ እንዲመስል እንደሚያደርገው ይናገራል።

"ከዕድሜዬ የሆነ የሆነ ዓመት ይጨምርብኛል በቃ፣ ያለዕድሜ ትልቅ ሰው ያስመስላል" ሲል የፀጉሩ መሸሽ ካለበት የ20ዎቹ አጋማሽ እድሜ በላይ እንዲገመት እንዳደረገው ይናገራል።

ይህንን ለመቀየርም ሽንኩርት እና ሌሎችን ፀጉር ያሳድጋሉ የተባሉ አትክልቶችን መቀባትን ጨምሮ የተለያዩ የተፈጥሮ መፍትሄዎችን ሞክሯል። ዘመናዊ የሚባሉ የፀጉር ማሳደጊያ ምርቶችም አልቀሩትም።

በተለይም በሚንቀሳቀስበት የማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሰዎችን አስተያየት መስማት ነገሩን ችላ እንዳይለው ማድረጉን ቃለአብ ይናገራል።

"ፀጉርህ ገብቶ ነው ወይስ ግንባርህ ወጥቶ ነው? ፣ 'ካፒታል M እየመሰልክ ነው' " የሚሉ አስተያየቶች በአስተያየት መስጫ በኩል እንደሚደርሱት ይገልፃል።

እንደዚህ ያሉ አስተያየቶች በሰዓቱ ስቆ ቢያልፋቸውም፣ በእሱ ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ግን ቀላል አልነበሩም።

ከዚያ አልፎም፣ ፀጉሩን እንዳይበላሽ በየደቂቃው ማስተካከል፣ እንደፈለገ ዋና መዋኘት አለመቻል እና ከጓደኞቹ ጋር ሲሆን ፀጉሩን እንዳይነኩት የሚያደርገው መጠንቀቅ የዕለት ተዕለት ስራ ሆኖበት ነበር።

"ከጓደኞችሽ ጋር ስትላፊ፣ ፀጉርሽን እንዳይነኩት የምትጠነቀቂው ጥንቃቄ፣ ልነግርሽ አልችልም" በማለት የነበረውን መሳቀቅ ይናገራል።

በመጨረሻ ግን እንዲህ ያለውን ጭንቀት ለማቆም ፀጉሩን መላጨት እና ራሱን አምኖ መቀበል እንዳለበት ወሰነ።

"ከዚያ የሆነ ሰዓት ላይ ወሰንኩኝ፤ በቃ መላጣ ነኝ፣ ይሄን አምኜ ልቀበል፤ ሙሉ ለሙሉ ልመለጠው፣ እንደዚህ ከምጨናነቅ ብዬ ወሰንኩኝ።" ይላል

ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ፀጉሩን ከተላጨ በኋላ ያየው መልክ የጠበቀው አልነበረም። ይህ ሙከራ የመጨረሻ ያለውን የፀጉር ንቅለ ተከላን መፍትሔ አድርጎ እንዲያወስድ አስገደደው።

የፀጉር ንቅለ ተከላ ሲካሄድ

"በቃ መላጣ ነኝ፤ ብሎ ራስን መቀበል ኖርማል ነው"

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የፀጉር ንቅለ ተከላ የሚያደርጉ ሰዎችንና በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚለቀቁ ቪዲዮዎችን ካየ በኋላ ይህ ትክክለኛው አማራጭ መሆኑን አምኖ ለመሞከር ወሰነ። ውሳኔው ቀላል መስሎ አልታየውም፤ ከጭንቅላቱ ጀርባ ያለው ፀጉር ተነቅሎ ወደ ፊት መተከሉ አስፈሪ ሆኖበት ነበር።

ከዚያም የት እንደሚሠራ ከተመለከተና ከዶክተሩ ጋር ከተነጋገረ በኋላ ውሳኔውን አጸና። ከንቅለ ተከላው ከሦስት ወር በኋላ ያየው ለውጥም ከጠበቀው በላይ እንደነበር ይገልጻል፤ ሙሉ ውጤቱ ግን ከአንድ ዓመት በኋላ እንደሚታይ ይጠቅሳል።

ለቃለአብ፣ የንቅለ ተከላው ለውጥ ፀጉሩን ብቻ ሳይሆን ራሱን የሚመለከትበትን መንገድም የቀየረ ሆኗል።

በፊት ፀጉሩን ለማስተካከልና ለመውጣት ለመዘጋጀት የሚወስደው ጊዜ አሁን እንደሌለ ይናገራል። "አሁን ታጥቤ ነው የምወጣው ደስተኛ ነኝ፤ ገፅታዬ ላይ በጣም ልዩነት አምጥቷል" ይላል።

ከንቅለ ተከላው በኋላ የፀጉሩ ለውጥ ሌሎችም እንዲያስተውሉት ማድረጉን የሚገልፀው ቃለአብ፣ ብዙ ሰዎች ለውጡን ካዩ በኋላ ለንቅለ ተከላ ለመወሰን መነሳሳት ጀመሩ ይላል።

"ሰዎች መንገድ ላይም ሲያገኙኝ ጥሩ አስተያየት ይሰጡኛል፣ የቲክቶክ ላይቭ ላይ፣ 'ፀጉርህ አምሮበታል' ይሉኛል" ሲል ይናገራል።

በሦስት ወር ያየው የፀጉሩ ለውጥም እሱንም እንዳስደሰተው ይገልጻል።

የፀጉር ንቅለ ተከላው የቀድሞ መልኩን ይመልስለት እንጂ ከዚህ ለውጥ በኋላ ቃለአብ የተረዳው ግን ፀጉር በራሱ ላይ እንዳሰበው ያህል ተፅዕኖ እንደሌለው ነው።

"የገባኝ ነገር ከተሠራሁ በኋላ፣ ሰው በራሱ ያለው መተማመን ነው እንጂ፣ ፀጉር ፊት ላይ ያን ያህል እኛ እንደምንጨነቀው፣ እንደምናስበው፣ ሰው ላይም ራሳችንም ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ የለውም" ይላል።

"አሁን ግን ምንም አይመስለኝም፣ በቃ ምንም ስሜት አይሰጠኝም።" ሲል ፀጉር መኖሩም ሆነ አለመኖሩ በራሱ ላይ ያለውን መተማመን እንደማይወስን ይገልጻል።

"በቃ መላጣ ነኝ፤ ብሎ ራስን መቀበል ኖርማል ነው ሌሎች ነገሮች ላይ መስራት ይቻላል" ይላል።

ራሱን በመስታወት የሚመለከት ወንድ

ናስር አህመድ በበኩሉ ፀጉሩ በመሳሳቱ ወይም በመርገፉ ሳይሆን፣ የግንባሩ መስመር በተፈጥሮ ወደ ኋላ በመሄዱ ብቻ የፀጉር ንቅለ ተከላ ማድረጉን ይናገራል።

ናስር የፀጉር ንቅለ ተከላውን ከማድረግ ባለፈ በቱርክ አገልግሎቱን ለማግኘት የሚመጡ ሰዎችን የሕክምና ተቋማትን እና ሌሎች አገልግሎቶችን እንዲያገኙም የማመቻቸት ስራ ይሰራል።

ብዙም ሳያስብበት ንቅለ ተከላውን እንዳደረገ የሚናገረው ናስር ከሂደቱ በኋላ በመልኩ ላይ የመጣው ለውጥ እንደጠበቀው ትልቅ እንዳልሆነ ይገልጻል።

የግንባሩ መስመር ቢስተካከልም፣ በአጠቃላይ የፊቱ ገጽታ ላይ ያን ያህል ለውጥ እንዳላመጣም ጨምሮ ያስረዳል።

የፀጉር ንቅለ ተከላ ለሚያስቡ ሰዎች የሚኖረው ተፅዕኖ ከሰው ወደ ሰው ሊለያይ እንደሚችል የሚናገረው ናስር አብዛኞቹ በስራ ያገኛቸው ሰዎች ግን ከተሰሩ በኋላ የሚኖራቸውን ገፅታ እንደሚወዱት እና በራስ መተማመናቸውንም እንደጨመረላቸው ይገልፃል።

የፀጉር ንቅለ ተከላ ከውበት ባሻገር ያለው ሥነ-ልቦናዊ ተፅዕኖ

ፀጉር የሰውን ገጽታ ከማሳመር ባለፈ በራስ የመተማመን ስሜትና በማኅበረሰብ ውስጥ ሰዎች ስለራሳቸው በሚፈጥሩት ምስል ላይ ተፅዕኖ እንዳለው የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

አጠቃላይ ሐኪምና የሥነ ልቦና አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ቤዛዊት ንጉሴ እንደሚሉት አንድ ሰው ስለራሱ ያለው ምልከታ እና በመስታወት የሚያየው ገጽታ ሲለያይ የሥነ ልቦና ተፅዕኖ ሊፈጥር ይችላል።

ፀጉርም በማኅበረሰብ ውስጥ ከወጣትነት፣ ከጉልበት እና ከውበት ጋር የተያያዘ ገጽታ እንዳለው ዶ/ር ቤዛዊት ያስረዳሉ።

በተለይም በወንዶች ላይ ሙሉ ፀጉር ያለው ሰው የበለጠ ወጣት፣ ጠንካራና ንቁ እንደሆነ የሚታሰብበት ሁኔታ እንዳለ ዶ/ር ቤዛዊት ይገልፃሉ።

በአንፃሩ ፀጉር መመንመን ወይም መመለጥ ሲጀምር አንዳንድ ሰዎች በራሳቸው ገጽታ ላይ የነበራቸውን መተማመን ሊያጡ ይችላሉ።

ይህም በራስ መተማመን፣ በፍቅር ግንኙነቶች፣ በሥራ እና በሌሎች ማህበራዊ ግንኙነቶች ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ዶ/ር ቤዛዊት አንስተዋል።

እንደ ዶ/ር ቤዛዊት ገለጻ፣ አንዳንድ ሰዎች የፀጉር ንቅለ ተከላን የሚመርጡት በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ቦታ ለማስጠበቅ ወይም ስለራሳቸው የፈጠሩትን ምስል ከሚያዩት ገጽታ ጋር ለማቀራረብ ነው።

ማኅበራዊ ሚዲያም በዚህ ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሆነ ያነሱት ዶ/ር ቤዛዊት ቀደም ሲል ስለፀጉር ንቅለ ተከላ በግልጽ መናገር የተለመደ ባይሆንም፣ ታዋቂ ሰዎች ስለሚያደርጉት የፀጉር ንቅለ ተከላ በይፋ መናገር መጀመራቸው ሂደቱን እንደ መደበኛ የውበት አማራጭ እንዲታይ እያደረገው መሆኑን ይጠቁማሉ።

እንደ ዶ/ር ቤዛዊት ሀሳብ፣ የፀጉር ንቅለ ተከላ ለሁሉም ሰው ተመሳሳይ የሥነ-ልቦና ውጤት አያመጣም። ንቅለ ተከላው የሚጠበቀውን ውጤት ካላመጣ ቅር መሰኘትና ተጨማሪ የሥነ ልቦና ጫና ሊፈጠር ይችላል። እንዲሁም የሰውየው ዋና ዓላማ የሌሎችን ተቀባይነት ማግኘት ከሆነ፣ ንቅለ ተከላው ብቻ የሚሰማውን የግሉን የሥነ-ልቦና ክፍተት ላይሞላ እንደሚችል ይገልፃሉ።

በመሆኑም የፀጉር ንቅለ ተከላ ለማድረግ የሚወስኑ ሰዎች ከሂደቱ የሚጠብቁትን ውጤት በቅድሚያ በግልጽ ማወቅ፣ ውጤቱ በግልፅ እስኪታይ ጊዜ እንደሚወስድ መረዳትና ውሳኔውን በሌሎች ተቀባይነት ላይ ብቻ ሳይመሰርቱ ለራሳቸው የሚፈልጉትን ነገር በመገንዘብ መወሰን እንዳለባቸው ዶ/ር ቤዛዊት ይመክራሉ።

እስከ 160 ሺህ ብር የሚከፈልበት የፀጉር ንቅለ ተከላ

ራሰ በራነት በተለይም በወንዶች የሚታይ ሲሆን፣ ይህን ለመቅረፍ የፀጉር ንቅለ ተከላን የሚመርጡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የቆዳና የአባላዘር ስፔሻሊስት እና የጸጉር ንቅለ ተከላ ባለሙያ ዶክተር ደባስ ታደሰ ይናገራሉ።

ዶክተር ደባስ ስለፀጉር ንቅለ ተከላ ሂደት ሲያብራሩ፣ ፀጉር በይበልጥ ከማይሳሳበት የራስ አካል ላይ የሚገኘው ፀጉር ተወስዶ ወደ የሸሸበት አካባቢ ይተከላል።

ንቅለ ተከላው እንደ ሰውየው የፀጉር መጠን እና እንደሚፈለገው ውጤት ልክ ከአራት እስከ ስድስት ሰዓት ሊወስድ ይችላል።

ከሂደቱ በኋላ የተተከለው ፀጉር ሙሉ በሙሉ ወደ ቀድሞ ይዞታው ለመመለስ ከዘጠኝ እስከ አስራ ወራት ያስፈልገዋል።

ዶክተሩ እንደሚገልጹት፣ አገልግሎቱን የሚጠቀሙት ወንዶች ብቻ አይደሉም። ሴቶችም የፀጉር ንቅለ ተከላ እያደረጉ ቢሆንም፣ በቁጥር ከወንዶች ያነሱ ናቸው።

በወንዶች የፀጉር መሸሸ በአብዛኛው ከፊት አካባቢ የሚጀምር ሲሆን፣ በሴቶች ደግሞ በራስ መሃል አካባቢ የሚታይ መሆኑን ያስረዳሉ።

የፀጉር ንቅለ ተከላ የሚፈልጉ ሰዎች ምክንያት የውበት ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነም ዶክተር ደባስ ይገልጻሉ።

የሰው ገጽታ መቀየር፣ እድሜው ከሚገባው በላይ እንደገፋ የሚሰማው ስሜት እና በማህበረሰቡ የሚሰጠው አመለካከት ሰዎችን ወደ ንቅለ ተከላው እንዲመጡ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል ናቸው።

በተለይም የፀጉር መሸሸ የራስ መተማመንን ሊቀንስ እንደሚችልና ንቅለ ተከላውን ካደረጉ በኋላ ደግሞ የራስ መተማመን መጨመር ከሚገለጹ ለውጦች አንዱ መሆኑን ዶክተሩ ይናገራሉ።

ሁሉም ሰው ግን የፀጉር ንቅለ ተከላውን እንዲያደርግ አይመከርም።

ንቅለ ተከላ ከመደረጉ በፊት ታካሚዎች የተለያዩ የጤና ምርመራዎችን እንደሚያደርጉ ዶክተር ደባስ ያስረዳሉ።

የደም ምርመራን ጨምሮ እንደ ስኳር፣ የደም ግፊት፣ የልብ፣ የጉበትና የኩላሊት ጤና ሁኔታ ይመረመራል። የምርመራዎቹ ውጤት ተስማሚ ከሆነ ብቻ ሂደቱ እንደሚቀጥል ይገልጻሉ።

ንቅለ ተከላው ረጅም ሰዓት ስለሚወስድና ማደንዘዣም ስለሚያስፈልግ፣ አንዳንድ የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች ሂደቱን እንዳያደርጉ ሊመከሩ ይችላሉ።

በተጨማሪም የንቅለ ተከላው ከተከናወነ በኋላ በሚሰራው ባለሙያው ብቃት፣ ፀጉር የሚወሰድበት አካባቢ (Donor Area) በቂ መሆን እና ከሂደቱ በኋላ ሊከሰት በሚችል ኢንፌክሽን ሊጎዳ እንደሚችል ዶክተሩ ይጠቁማሉ።

በአዲስ አበባ የጸጉር ንቅለ ተከላ ዋጋ እንደ ተቋሙና አገልግሎቱ ሁኔታ የሚለያይ ሲሆን ቢቢሲ ባደረገው ዳሰሳ መሰረት ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የፀጉር ንቅለ ተከላ ከ95 ሺህ ብር ጀምሮ እና እስከ160 ሺህ ብር ባለው ዋጋ ይሰጣል።

ዶክተር ደባስ ፣ ዋጋው ብቻ የአገልግሎቱን ጥራት እንደማይወስን በማስረዳት በተለይም የባለሙያው ብቃትና የሂደቱ አሰራር ወሳኝ መሆኑን ያመለክታሉ።

ከአምስት ዓመት በፊት ጀምሮ እየተስፋፋ ባለው በዚህ የአገልግሎቱ ዘርፍም የውጭ ባለሙያዎች ተሳትፎ እንዳለ ዶክተሩ ጠቅሰው፣ በተለይም ከቱርክና ሕንድ የሚመጡ ባለሙያዎች እንደሚሳተፉ ገልጸዋል። በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ባለሙያዎችም እየበዙ መምጣታቸውን ይናገራሉ።