አሁናዊ ፎቶን የ1980ዎቹ መልክ የሚያላብሰው ቻትጂፒቲ ምን ያህል ለደኅንነት አስጊ ነው?

በሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) የተሰራ የ1980ዎቹ አለባበስ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ትልቅ ፀጉር። ግራጫ ያደላባቸው ፎቶግራፎች። ደማማቅ ቀለሞች። በንግድ መደብሮች የሚገኙ የፎቶ ስቱዲዮዎች።

ማኅበራዊ የትስስር ገፃችሁ የ1980ዎቹን የቤተሰብ የፎቶ አልበም ከመሰለ ብቻችሁን አይደላችሁም። ምንአልባት እናንተም የዚህ አዝማሚያ አካል ልትሆኑ ትችላላችሁ።

በመላው ዓለም ሚሊዮኖች ፎቶግራፎቻቸውን ወደ ኋላው ዘመን ለመውሰድ፣ መሳለቂያ የነበረውን የፀጉር አሠራር፣ ዘመን የማያልፍበትን ፋሽን እና ትዝታ ቀስቃሽ ምሥሎችን ለመፍጠር ቻትጂፒቲን እና ሌሎች በሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚሠሩ መሣሪያዎችን ይጠቀማሉ።

በሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) የተፈጠሩት ፎቶዎች በአብዛኛው በቻትጂፒቲ ምሥል ማመንጫ የተፈጠሩ፣ ተጠቃሚዎች የራሳቸውን ፎቶ እንዲጭኑ የሚያበረታቱ፣ በሚያስደንቅ ሁኔታ አሳማኝ እና በከፍተኛ ሁኔታ ሊጋሩ የሚችሉ ናቸው።

ይህ አዝማሚያም በኢንስታግራም፣ በቲክቶክ እና በኤክስ ላይ በፍጥነት እንዲሰራጭ ረድቷል።

ነገር ግን ከዚህ የትዝታ ናፍቆት ጀርባ ባለሙያዎች የሚጋራው መረጃ ተጠቃሚዎች ከሚያስቡት በላይ ነው ሲል ያስጠነቅቃሉ።

'ለመዝናኛ የሚሰጥ መረጃ'

በጎርጎሮሳዊያኑ 1980ዎቹ ዘመን የነበረውን የአለባበስ ዘይቤ እንደ አዲስ በኤአይ ያመጣው አካሄድ ተወዳጅነት በጄኔሬቲቭ ሰው ሠራሽ አስተውሎት (ይዘት ፈጣሪ) ላይ ሰፊ ለውጥ አሳይቷል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት የኤአይ ምሥል የማመንጫ መሣሪያዎች በአብዛኛው በአድናቂዎች እና ለቴክኖሎጂ እውቀት ባላቸው ተጠቃሚዎች ብቻ የተወሰነ ነበር።

ዛሬ ግን ከማኅበራዊ ሚዲያ አዝማሚያዎች እስከ የሥራ ቦታ መሣሪያዎች እና የሸማቾች መተግበሪያዎች ድረስ በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ እየተጋመዱ መጥተዋል።

የ1980ዎቹ የአለባበስ ዘይቤ በኤአይ ተኮር ተከታታይ አካሄዶች ውስጥ የቅርብ ጊዜው ነው።

አዲሱ አዝማሚያ የልጅነት ፎቶግራፎች፣ ምናባዊ የገጸ-ባህሪያት ለውጦች እና የበዓል ጭብጥ ያላቸውን ምሥሎች ተከትሎ የመጣ ነው።

እነዚህ በሰፊው የተዳረሱ (ቫይራል) ይዘቶች አዳዲስ ተጠቃሚዎችን ይስባሉ። ተጠቃሚዎች የግል መረጃዎቻቸውን እንዲያጋሩም ያበረታታሉ ሲሉ የሰው ሠራሽ አስተውሎት የሥነ ምግባር ባለሙያ ካትሪና ዶሪያ ተናግረዋል።

"እነዚህ አዝማሚያዎች የሚከሰቱት ለጄኔሬቲቭ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኩባንያዎች ጠቃሚ ስለሆኑ ነው" ይላሉ።

"ሰዎች የራሳቸውን እና የሌሎችን ምሥሎች በብዛት እንዲጭኑ ይበረታታሉ"።

ዶሪያ ይህን የግል መረጃን 'ለመዝናኛ የመለወጥ ክስተት' ብዙውን ጊዜ ሙሉ ለሙሉ አንድምታው ግምት ውስጥ ሳይገባ የሚደረግ ነው ብለው ይገልፁታል።

አንድ ሰው የቻትጅፒቲ አርማ በስልኩ ይዞ
የምስሉ መግለጫ, የ'ቻትጂፒቲ' ባለቤት የሆነው ኦፕንኤአይ እምነት እና ግላዊነት የምርቶቹ መሠረት እንደሆኑ ይናገራል

በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የኤአይ ሥነ ምግባር ኢንስቲትዩት የፍልስፍና ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ካሪሳ ቬሊዝ፣ ተጠቃሚዎች የግል መረጃዎችን በኤአይ ሥርዓቶች ላይ ከማጋራታቸው በፊት በጥንቃቄ ማሰብ እንዳለባቸው ይስማማሉ።

"ፎቶዎችን ወደ ኤአይ ስትጭኑ፣ ይህ ልትሰጡት ከምትችሉት በጣም ምሥጢራዊ መረጃዎች ውስጥ አንዱ ነው" ይላሉ።

"ፎቶዎቹ ብዙውን ጊዜ እንደ አካባቢ ያሉ ምሥጢራዊ ሜታዳታዎችን ያካትታሉ። ነገር ግን ባዮሜትሪክስን አሳልፋችሁ እየሰጣችሁ ነው።"

የፊት ገጽታዎችን ጨምሮ የባዮሜትሪክ መረጃ በዋናነት ምሥጢራዊ ነው። ምክንያቱም ከእጅ ከወጣ በቀላሉ መቀየር አይቻልም።

"የይለፍ ቃል ከተሰረቀ መቀየር ትችላላችሁ" የሚሉት ቬሊዝ "ነገር ግን ፊታችሁን መቀየር አትችሉም" ይላሉ።

ዶሪያ ደግሞ አደጋዎቹ እንደ ኢንስታግራም ወይም ፌስቡክ ካሉ ተራ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች እና የፍቅር ጓደኝነት መፈለጊያ መተግበሪያዎች ሊበልጡ ይችላሉ ይለሉ።

ምክንያቱም ተጠቃሚዎች በአብዛኛው ፊታቸውን በግልጽ ለማሳየት በርካታ ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ምሥሎች ይጭናሉ።

ከዚህ በተጨማሪም ተጠቃሚዎች ስለ ሥራቸው፣ ግንኙነታቸው እና ፍላጎቶቻቸው ሲወያዩ ሰፊ የግል መረጃዎችን ለኤአይ እንደሚያጋሩ ጠቁመዋል።

እነዚህ መረጃዎች ከፎቶግራፎች ጋር ተዳምረው የአንድን ግለሰብ ዝርዝር መረጃ ለመያዝ ትልቅ መሣሪያ ይሆናሉ።

ለማስታወቂያ ዒላማ ማድረግ

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ነገር ግን ስጋቱ የግላዊነት ጉዳይ ብቻ አይደለም። ባለሙያዎች ዛሬ የተጋራው መረጃ ወደፊት እንዴት ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል በተመለከተ ያላቸው ጥርጣሬም ይገልጻሉ።

"የዲጂታል ዘመን አንዱ ችግር የእናንተ መረጃ ወደፊት እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚውል ምንም አለማወቃችን ነው" ይላሉ ቬሊዝ።

"የት እንደሚደርስ እንኳን አናውቅም፤ ምክንያቱም ብዙ ኩባንያዎች በግዴለሽነት እየሸጡት ነው።"

ዶሪያም ሆኑ ቬሊዝ ቴክኖሎጂዎች ከጥቂት ዓመታት በፊት ለመገመት አስቸጋሪ በሆነ መንገድ እንዴት ሊዳብሩ እንደሚችሉ የሚያሳይ ፈጣን የኤአይ የውሸት ፈጠራዎች (ዲፕፌክ) እድገትን ለአብነት ይጠቅሳሉ።

ዛሬ ጉዳት ለሌላቸው ዓላማዎች የተጫኑ ምሥሎች ነገ የበለጠ ለተራቀቁ የኤአይ ሥርዓቶች አበርክቶ ሊኖራቸው ይችላሉ።

ዶሪያ "ከአምስት ወይም ከስድስት ዓመታት በፊት ይህ እንደሚሆን አላሰብንም ነበር" ሲሉ በቅርቡ እውነት የሚመስሉ በኤአይ የመነጩ ምሥሎችን እድገት ያመላክታሉ። "ፎቶዎችን በበይነ መረብ ላይ በደስታ እየለጠፍን ነበር" ይላሉ።

ማንነትን ዒላማ ያደረጉ ማስታወቂያዎችም ላይ ስጋቶች አሉ። በቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የተሰበሰበው መረጃ የተጠቃሚዎችን ፍላጎቶች፣ ልማዶች እና ባህሪያት ዝርዝር ምሥሎችን ለመገንባት ይረዳል።

ይህም ማስታወቂያ አስነጋሪዎች እና ሌሎች ድርጅቶች ግለሰቦችን በበለጠ ለይተው እንዲያነጣጥሩ ያስችላቸዋል።

በርካታ ትላልቅ የኤአይ ኩባንያዎች የግላዊነት መቆጣጠሪያዎች ለተጠቃሚዎች ክፍት እንደሆኑ ይናገራሉ። ይህም የወደፊት የኤአይ ሞዴሎችን ለማሻሻል የሚያጋሩት መረጃ ጥቅም ላይ እንዳይውል መገደብን ያካትታል።

ኦፕንኤአይ እምነት እና ግላዊነት ለምርቶቹ መሠረታዊ እንደሆኑ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ተጠቃሚዎች በመረጃዎቻቸው ላይ ቁጥጥር አድርገው ውይይቶቻቸውን የመሰረዝ አማራጭ አላቸው።

ወደ 'ጊዜያዊ ውይይት' በመቀየር ውይይቶቻቸው ተመዝግበው እንዳይቀመጡ፣ እንዳይታወሱ ወይም ሞዴሎችን ለማሻሻል ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ማድረግ ይችላሉ።

'ግላዊነት ኃይል ነው'

ዶሪያ እንደ 1980ዎቹ የአለባበስ ዘይቤ አዝማሚያዎች ያሉ ሰፊ ተደራሽ ይዘቶች ውስጥ ሰዎች ባይዘፈቁ ይመርጣሉ።

ነገር ግን በርካታ የግላዊነት ባለሙያዎች ሰዎች የኤአይ መሣሪያዎችን ሙሉ በሙሉ እንዲያስወግዱ ከመንገር ይቆጠባሉ።

በአንፃሩ ተጠቃሚዎች ምን መረጃ እንደሚያጋሩ እና እንዴት እንደሚያጋሩ በጥንቃቄ እንዲያስቡ ያበረታታሉ። ከእነዚህም ውስጥ፡

  • የልጆችን ፎቶዎች ከመጫን ተቆጠቡ- ልጆች ትርጉም ባለው መልኩ ፈቃድ መስጠት አይችሉም። ወላጆች በእነሱ ምትክ ቋሚ ዲጂታል ማኅደር ከመፍጠቸራው በፊት በጥንቃቄ ማሰብ አለባቸው።
  • በተቻለ መጠን ዝቅተኛ ጥራት ያላቸውን ምሥሎች ተጠቀሙ- ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ፎቶግራፎች የበለጠ እና ዝርዝር የባዮሜትሪክ መረጃ ሊያሳዩ ይችላሉ።
  • የተጠናከሩ መድረኮችን ምረጡ- ታዋቂ አገልግሎቶች ብዙውን ጊዜ በሰፊ ተደራሽነት (ቫይራል) አዝማሚያዎች ወቅት ከሚታዩ ግልጽ ያልሆኑ መተግበሪያዎች በበለጠ ግልጽ የግላዊነት ፖሊሲዎች እና ጠንካራ አስተዳደር አላቸው።
  • የግላዊነት አስተዳደሮችን ተመልከቱ- በርካታ የኤአይ አገልግሎቶች ተጠቃሚዎች የወደፊት ሞዴሎችን ለማሻሻል ይዘታቸው ጥቅም ላይ እንዳይውል ምርጫ ያስቀምጣሉ። እነዚህ የአስተዳደር ማስተካከያዎች መኖራቸውን አረጋግጣጡ እና አስተካክሉ።
  • የማያስፈልጉ የማኅደረ ትውስታ ማስተካከያዎችን አጥፉ- አንዳንድ የኤአይ ቻትቦቶች ምላሾችን ለየግለሰቦች በሚስማማ መልኩ ለመስጠት ከቀደሙት ውይይቶች የተገኙ መረጃዎችን ያከማቻሉ። እነዚህን ማስተካከያዎችን መዝጋት የሚያዘውን የግል መረጃ መጠን ሊቀንስ ይችላል።

የኤአይ መሣሪያዎች በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ እየተጋመዱ ሲሄዱ፤ ባለሙያዎች እንደሚሉት ችግሩ እነርሱን በመጠቀም የምናጣውን ወይም የምንለውጠውን መረዳት ነው።

"ግላዊነት ኃይል ነው ምክንያቱም ሥልጣንን ያላግባብ ከሚጠቀሙት ይጠብቃችኋል" ይላሉ ቬሊዝ።